የኢትዮጵያ ከ17 ዓመት በታች የሴቶች ብሔራዊ ቡድን በሜዳው ተሸንፏል

በዓለም ዋንጫ የመጨረሻ ዙር ማጣሪያ ከናይጄሪያ ጋር የተጫወተው የኢትዮጵያ ከ17 ዓመት በታች የሴቶች ብሔራዊ ቡድን 1-0 ተሸንፏል።

በሕንድ አስተናጋጅነት በሚደረገው የዕድሜ ዕርከኑ የዓለም ዋንጫ ላይ ለመሳተፍ በመጨረሻ ዙር ጨዋታ የተገናኙት ኢትዮጽያ እና ናይጄሪያ የመጀመሪያ ጨዋታቸውን 10:00 ላይ በአበበ ቢቂላ ስታዲየም አድርገዋል።

ጨዋታውን ፈጠን ባለ ጥቃት የጀመሩት ናይጄሪያዎች በመጀመሪያዎቹ 10 ደቂቃዎች ሁለት ከባባድ ሙከራዎች አድርገዋል። 3ኛው ደቂቃ ላይ አጃካዬ ኢስተር እንዲሁም 10ኛው ደቂቃ ላይ አዴባዮ ራህሞት በግራ በኩል ሰብረው በመግባት ያደረጉትን ሙከራ ግብ ጠባቂዋ አበባ አጂቦ ማዳን ችላለች። ቀስ በቀስ ኳስ መያዝ የጀመሩት የኢትዮጵያ ተጫዋቾች በተጋጣሚያቸው ሜዳ ላይ ቅብብሎችን መከወን ሲጀምሩ 17ኛው ደቂቃ ላይ ትንቢት ሳሙኤል ከመሀል ጥሩ ኳስ አድርሳት ቁምነገር ካሳ በቀኝ ገብታ ጠንከር ያለ ኳስ ብትሞክርም በግብ ጠባቂዋ ድኖባታል።

ኢትዮጵያዊያኑ በቀጣይ ደቂቃዎች የተጋጣሚያቸውን ፈጣን ጥቃቶች መገደብ ችለው የቆዩ ሲሆን በአንፃሩ የእነሱ ቅብብል እምብዛም ከሜዳቸው መውጣቱን ቀንሷል። 

ለመልሶ ማጥቃት የሚሆኑ አጋጣሚዎችንም ወደ ጥቃት መቀየር ያልቻለው ቡድኑ 36ኛው ደቂቃ ላይ ግብ አስተናግዷል። የጨዋታውን ቀዳሚ ሙከራ ያደረገችው አጃካዬ ኢስተር ከመሀል የደረሳትን ኳስ አበባ አጂቦ ቀድማ ደርሳ ለማውጣት ያደረገችው ጥረት ሳይሳካ አግኝታ ግብ አድርገዋለች።
ከዕረፍት በኋላ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የተሻለ መነቃቃት አሳይቷል። በአመዛኙ በቀኝ ያዘነበለው የቡድኑ ጥቃት ግን የመጨረሻ ቅብብሎች ጥራት አንሶት ወደ ሙከራነት ሳይቀየር ቆይቷል። ይልቁኑም ናይጄሪያዎች በተሻለ ወደ ግብ ሲቀርቡ 51ኛው ደቂቃ ላይ ቤሎ አሚና ከሳጥን ውጪ ሞክራ አግዳሚ ሲገጭባት 60ኛው ላይ ደግሞ የአፎላቢ ቲያዎ የሳጥን ውስጥ ሙከራ በአበባ ተይዟል።

የቀኝ ጥቃታቸው 61ኛው ደቂቃ ላይ ቁምነገር ባሻማቸው እና በወጣው ኳስ የተሻለ ለግብ በቀረበው ኢትዮጵያዊያኑ በኩል 76ኛው ደቂቃ ላይ ትንቢት ሳሙኤል ከሳጥኑ መግቢያ ላይ ያደረገችው ሙከራ በግቡ አግዳሚ ተመልሷል። በቀሪው የጨዋታ ጊዜ ናይጄሪያዎች የግብ ክልላቸውን ሳያጋልጡ ጨዋታውም ግብ ጠባቂዎችን የሚፈትን ሌላ ሙከራ ሳያስመለክት ተቋጭቷል።

የመልሱ ጨዋታ ግንቦት 27 በናይጄሪያ ይደረጋል።