ሪፖርት | አዳማ ከ11 ጨዋታ በኋላ አሸንፏል

በረፋዱ ጨዋታ ለ73 ያክል ደቂቃዎች በጎዶሎ የተጫዋች ቁጥር ያሳለፉት አዳማ ከተማዎች በውድድር ዘመኑ ለሁለተኛ ጊዜ ሦስት ግቦችን ባስቆጠሩበት ጨዋታ ከ11 ጨዋታዎች በኃላ ከድል ጋር ሲታረቁ በአንፃሩ ከሰሞኑ በሊጉ ለመቆየት ተስፋ ፈንጥቀው የነበሩት ሰበታዎች ዳግም ወደ ሊጉ ግርጌ ተመልሰዋል።

የአሰልጣኝ ለውጥ ያደረጉት አዳማ ከተማዎች በይታገሱ እንዳለ እየተመሩ በመጨረሻው ጨዋታ በባህር ዳር ከተረታው ስብስብ አራት ለውጥ አድርገዋል በዚህም ቶማስ ስምረቱ ፣ ዮሴፍ ዮሀንስ ፣ ታደለ መንገሻ እና አሜ መሀመድን አስወጥተው በምትካቸው አዲስ ተስፋዬ ፣ ዮናስ ገረመው ፣ ፀጋአብ ዮሴፍ እና አቡበከር ወንድሙ በመጀመሪያ ተመራጭነት ያስጀመሩ ሲሆን በአንፃሩ ወልቂጤ ከተማን ረቶ የመጣው የአሰልጣኝ ብርሃኑ ደበሌ ስብስብ ደግሞ ምንም ለውጥ ሳይደረግበት ወደ ዛሬው ጨዋታ ቀርበዋል።

አዳማ ከተማ ከተማዎች የተሻለ አጀማመር ባደረጉበት የመጀመሪያው አጋማሽ የጨዋታ ከፍለ ጊዜ ገና በ10ኛው ደቂቃ ነበር ቀዳሚ መሆን የቻሉት ፤ ከማዕዘን ምት በአጭር ቅብብል የጀመሩትን ኳስ አቡበከር ወንድሙ ከሳጥን ጠርዝ ወደ ውስጥ ያሻሙትን ኳስ አዲስ ተስፋዬ ተንሸራቶ አስቆጥሯል።

ከግቧ በኃላ በነበሩ ደቂቃዎች በተመሳሳይ አዳማዎች በተከታታይ ወደ ሰበታ ከተማ ሳጥን በመድረስ ሙከራዎዎችን ለማድረግ ጥረት አድርገዋል በዚህም ተደጋጋሚ የማዕዘን ምቶችን ማግኘት የቻሉበትንም አጋጣሚ መፍጠር ችለዋል።

ቀዝቃዛ በነበረው የመጀመሪያ አጋማሽ በ17ኛው ደቂቃ ከአማኑኤል ጎበና የደረሰውን ኳስ በቀጥታ ወደ ግብ ለመሞከር ጥረት ያደረገው ዳዋ ሆቲሳ ከወልደአማኑኤል ጌቱ ጋር ኳሱን ለመምታት ባደረገው ጥረት ንክኪ መፈጠሩን ተከትሎ ሜዳ ላይ የወደቀው ዳዋ ከበረከት ሳሙኤል እና ከዳኛው ጋር በተፈጠረ አለመግባባት በቀጥታ ቀይ ካርድ ከሜዳ ተሰናብቷል።

ባለፉት ጥቂት ጨዋታዎች የመሻሻል ምልክት በማሳየት ላይ የነበሩት ሰበታዎች በዚህኛው ጨዋታ ግን በተወሰነ መልኩ ተቀዛቅዘው አስተውለናል።

ከመስመሮች በሚነሱ ኳሶች ለማጥቃት ፍላጎት የነበራቸው ሰበታ ከተማዎች ከቀይ ካርዱ በኃላ በነበሩ ደቂቃዎች ይህን ለመጠቀም በማሰብ በሚመስል እርጋታ የተላበሰ እንቅስቃሴ ለማድረግ ቢጥሩም ይህን መጠቀም ሳይችሉ ቀርተዋል ፤ በአጋማሹ ሳሙኤል ሳሊሶ በመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች ከርቀት ካደረገው እና ኢላማውን ካልጠበቀ ሙከራ ውጭ ሙከራ ለማድረግ የተቸገሩበት አጋማሽን አሳልፈዋል።

በሁለተኛው አጋማሽ ጅማሮ በሀይሉ ግርማ ምትክ አለምአንተ ካሳን በማስገባት የጀመሩት ሰበታ ከተማዎች ከመጀመሪያው በተሻለ የማጥቃት ፍላጎት አሳይተው የተጫወቱበት ነበር ፤ በዚህም ተደጋጋሚ ኳሶች ከመስመር ቢሻገሩም ኢላማውን የጠበቀ ሙከራን ግን ለማድረግ ብዙ ለመጠበቅ ተገደዋል።

በአንፃሩ ከዳዋ ሆቲሳ ቀይ ካርድ በኃላ ቀስ በቀስ ወደ ኃላ ተስበው መከላከል የጀመሩት አዳማ ከተማዎች ከ70ኛው ደቀቃ ወዲህ ግን በማጥቃቱ ረገድ የተነቃቃ ይመስላል ፤ በዚህም ተደጋጋሚ እድሎችን በፈጣን መልሶ ማጥቃቶች መፍጠር ቢችሉም በደካማ ውሳኔ አሰጣጥ ፍሬያማ መሆን ሳይችሉ ቀርተዋል።

በ81ኛው ደቂቃ ዮናስ ገረመው በግንባሩ የገጨውን ኳስ ዱሬሳ ሹቢሳ በእጅ በመንካቱ የተነሳ ያገኙትን የፍፁም ቅጣት ምት ኳስ ደስታ ዮሀንስ አስቆጥሮ የቡድኑን አሸናፊነት አረጋግጧል።

ሁለተኛ ግብ ካስተናገዱ በኃላ ዘግይተውም ቢሆን ወደ ጨዋታው ለመመለስ ጥቃቶች መሰንዘር የጀመሩት ሰበታዎች በ85ኛው ደቂቃ ሚሊዮን ሰለሞን ከሳሙኤል ሳሊሶ እግር በመጨረሻው ቅፅበት ተንሸራቶ ያዳነበት እንዲሁም በ87ኛው ደቂቃ በሰበታ ከተማዎች በኩል የመጀመሪያ ዒላማዋን የጠበቀች የነበረችው ሙከራ አብዱልሀፊዝ ቶፊቅ ቢያደርጉም ሳኩቡ ካማራ አድኖባቸዋል።

ታድያ አሁንም ቢሆን እንደ ቡድን በመከላከል በማጥቃት ረገድ ፍላጎት ያላባራው አዳማ ከተማዎች በ90ኛው ደቂቃ ሦስተኛ ግብ አግኝተዋል ፤ ደስታ ዮሀንስ በሜዳው የላይኛው ክፍል የነጠቀውን ኳስ ተጠቅሞ ሳጥን ውስጥ ያደረሰውን ኳስ ዮናስ ገረመው በማስቆጠር ቡድኑን በውድድር ዘመኑ ለሁለተኛ ጊዜ ሦስት ግቦችን አስቆጥሮ እንዲያሸንፍ አስችሏል።

ውጤቱን ተከትሎ ወደ ወራጅ ቀጠናው ተጠግተው የነበሩት አዳማዎች ነጥባቸውን ወደ 30 በማሳደግ ሌሎች እስኪጫወቱ ለጊዜው ወደ 8ኛ ደረጃ ከፍ ብለው ሲቀመጡ በአንፃሩ ሰበታዎች ደግሞ በ20 ነጥብ በጅማ አባ ጅፋሮች በጎል ልዩነት ተበልጠው ዳግም ወደ ሊጉ ግርጌ ተመልሰዋል።