የ2014 የሴቶች ከፍተኛ ሊግ በንፋስ ስልክ ላፍቶ አሸናፊነት ተጠናቋል

በአስራ አራት ክለቦች መካከል ከታህሳስ 16 ጀምሮ ሲደረግ የነበረው የሴቶች ከፍተኛ ሊግ ሁለት ክለቦችን ወደ ፕሪምየር ሊጉ በማሳደግ ተጠናቋል፡፡

በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን አዘጋጅነት ከታህሳስ 16 ጀምሮ ሲደረግ የነበረው የ2014 የኢትዮጵያ ሴቶች ከፍተኛ ሊግ ውድድር በትላንትናው ዕለት ፍፃሜውን አግኝቷል፡፡ ጅምሩን በባቱ ከተማ በማድረግ በሀዋሳ ፣ በመቀጠል ደግሞ በሰበታ ከተማ ያደረገው ይህ ውድድር አስራ አራት ክለቦችን ተካፋይ በማድረግ ሁለቱን ወደ 2015 የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ ማሳደጉን አሳውቆ ነው ሊጠናቀቅ የቻለው፡፡

ትላንት ውድድሩ ሲጠናቀቅ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌድሬሽን ዋና ፀሀፊ አቶ ባህሩ ጥላሁን እና የውድድር ዳይሬክቶሬቱ አቶ ከበደ ወርቁ በመዝጊያ ሥነ ስርአት ላይ ታድመዋል፡፡ በመዝጊያው ጨዋታ ቀደም ብሎ ወደ ፕሪምየር ሊጉ ማደጉን ያረጋገጠው ንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለከተማ ሀላባ ከተማን በፍፃሜ መርሐግብር 3-0 በመርታት የዋንጫ እና የወርቅ ሜዳሊያ ሲያገኝ ሌላኛው የመዲናይቱ ክለብ ልደታ ክፍለ ከተማ ሁለተኛ ሆኖ በማጠናቀቅ የብር ሜዳሊያ ሲሸለም ወደ ሊጉ ማደጉም አረጋግጧል፡፡ 

ሱሉልታ ከተማ ምንም እንኳን ማደግ ባይችልም ሦስተኛ ሆኖ በመፈፀሙ የነሀስ ሜዳሊያ ተሸልሟል፡፡ የስፖርታዊ ጨዋነት ሽልማት አራዳ ክፍለ ከተማ ሲያገኝ ለውድድሩ መሳካት አስተዋጽኦ ላደረጉ አካላትም ሽልማት ተሰጥቷቸዋል፡፡