ቅድመ ዳሰሳ | የ25ኛ ሳምንት የሁለተኛ ቀን ጨዋታዎች

ከነገዎቹ የሊጉ ጨዋታዎች ውስጥ በቀዳሚነት የሚደረጉት ሁለት ጨዋታዎችን በዳሰሳችን ተመልክተናል።

አዳማ ከተማ ከ ሰበታ ከተማ  

ረፋድ ላይ የሚደረገው ጨዋታ ለተጋጣሚዎቹ ብቻ ሳይሆን በወራጅ ቀጠናው ውስጥ ያሉ እና ለቀጠናው የቀረቡ ቡድኖችን ሁሉ ይመለከታል። ከድል ጋር ተራርቆ የቆየው አዳማ ከተማ ሳይታሰብ ከአደጋው ሁለት ነጥብ ርቀት ላይ ሲገኝ ሁለት ተከታታይ ድል ያሳኩት ሰበታዎች ደግሞ ዛሬ ጅማ አንድ ነጥብ ማግኘቱን ተከትሎ ወደ ሰንጠረዡ ግርጌ ተመልሰዋል። ሁለቱ ቡድኖች ነገ የሚያሳኩት ነጥብ አጠቃላይ የቀጠናውን እንድምታ የሚወስን ቢሆንም በይበልጥ ለሰበታ ከተማ በቀጣይ ጨዋታዎች ተስፋን ለመሰነቅ ወሳኝ ይሆናል።

ከአሰልጣኝ ፋሲል ተካልኝ ጋር የተለያየው አዳማ ከተማ በጊዜያዊ ዋና አሰልጣኝ ይታገሱ እንዳለ እየተመራ የመጀመሪያ ጨዋታውን ያደርጋል። ከሰበታ ከተማ የኳስ ቁጥጥር ወዳድነት አንፃር አዳማዎች ብርቱ መከላከል ላይገጥማቸው ቢችልም ሰሞኑን በተደጋጋሚ የታየው ዕድሎችን የመጨረስ ችግር ማሻሻል ለአሰልጣኝ ይታገሱ ቀዳሚው የነገ የቤት ሥራ ይመስላል። በሰበታ በኩል ነገሮች ጥሩ እየሄዱ ነው። የቡድኑ የኳስ ቁጥጥር ትርጉም ያላቸው እየሆኑ በታዩባቸው ያለፉት ጨዋታዎች ከጌቱ ኃይለማሪያም ከቀኝ መስመር በሚነሱ ኳሶች እና በአብዱልሀፊስ ቶፊቅ ቀማሪነት ቡድኑ መሀል ለመሀል የሚከፍታቸው ጥቃቶች ጥሩ ውጤት እያስገኙ ይገኛል። ነገ ይህን መሻሻል ከጠንካራው የአዳማ ተከላካይ ጋር ማስቀጠል መቻል ለሰበታ ወሳኝ ይሆናል።

ምንተስኖት ዓሎ እና ዘላለም ኢሳይያስ በሰበታ ከተማ የጉዳት ዝርዝር ውስጥ ያሉ ሲሆን አዳማ ከተማም ዮሴፍ ዮሐንስን በቅጣት ነቢል ኑሪን በጉዳት ያጣል።

የእርስ በእርስ ግንኙነት

– እስካሁን ዘጠኝ ጨዋታዎችን ያደረጉት ተጋጣሚዎቹ ሁለት ጊዜ ነጥብ ሲጋሩ አዳማ አራት ሰበታ ሦስት ድሎችን አስመዝግበዋል። በጨዋታዎቹ አዳማ ስድስት ሰበታ አምስት ግቦች አሏቸው።

የጨዋታው ዳኞች – ዋና ዳኛ ባህሩ ተካ ፣ ረዳቶች ክንዴ ሙሴ እና ፍሬዝጊ ተስፋዬ ፣ አራተኛ ዳኛ ተስፋዬ ጉሩሙ ፣ ተጨማሪ ዳኞች ሸዋንግዛው ይልማ እና ሰለሞን ተስፋዬ

ግምታዊ አሰላለፍ

አዳማ ከተማ (4-3-3)

ሴኮባ ካማራ

ጀሚል ያዕቆብ – ቶማስ ስምረቱ – ሚሊዮን ሰለሞን – ደስታ ዮሐንስ

አማኑኤል ጎበና – ዮሴፍ ዮሐንስ – ዮናስ ገረመው

አቡበከር ወንድሙ – ዳዋ ሆቴሳ – አሜ መሐመድ

ሰበታ ከተማ (4-2-3-1)

ለዓለም ብርሀኑ

ጌቱ ኃይለማሪያም – በረከት ሳሙኤል – አንተነህ ተስፋዬ – ኃይለሚካኤል አደፍርስ

በኃይሉ ግርማ – ጋብርኤል አህመድ

ሳሙኤል ሳሊሶ – አብዱልሀፊዝ ቶፊቅ – ዱሬሳ ሹቢሳ

ዴሪክ ኒስባምቢ

አርባምንጭ ከተማ ከ ወላይታ ድቻ

ከአራት ጨዋታዎች በኋላ ወደ ድል የተመለሰው አርባምንጭ ከተማ እና ከድል ጋር ከተራራቀ ስምንት ጨዋታዎች ያለፉት ወላይታ ድቻ ቀትር ላይ ይፋለማሉ። አርባምንጮች ባሳለፍናው ሳምንት ድላቸው ወራጅ ቀጠናውን መሸሽ ቢችሉም ከሰንጠረዡን አጋማሽ ለመሻገር የነገውን ውጤት ይፈልጉታል። በአንፃሩ የአራተኝነት ደረጃውን ዛሬ ላሸነፈው ኢትዮጵያ ቡና የለቀቀው ወላይታ ድቻ ከኮንፌዴሬሽን ዋንጫ ደረጃ ይበልጥ ላለመራቅ እንደመጀመሪያው ዙር ሁሉ አዞዎችን ማሸነፍ አስፈላጊው ይሆናል።

አርባምንጭ የመጨረሻ ሳምንት ድሉ በሥነልቦናው የተረጋጋ ቡድንን ነገ ለማስየት እንደሚረዳው ይጠበቃል። ጠንካራ የአካላዊ ፍልሚያ እንደሚኖረው በሚጠበቀው በነገው ጨዋታ ቡድኑ በዚህ ረገድ ያለውን ጥሩ ገፅታ ማስቀጠል እና በአንዳንድ ጨዋታዎች የሚታይበትን ያልታሰበ የመከላከል ድክመት በማረም ወደ ቦታው መመለስ ይጠበቅበታል። ከዚህ ባለፈ አርባምንጮች ቀጥተኛ በሆነ አቀራረብ የፊት አጥቂዎቻቸውን ያማከሉ ኳሶችን በመላክ እንደሚያጠቁ ይጠበቃል። ጥሩ አቋም ላይ የማይገኙት ወላይታ ድቻዎች የስብስብ ጥልቀታቸው ይበልጥ እየጎዳቸው ነው። ነገም ከቅጣት መልስ ከሲዳማው ጨዋታ የተሻለ ቡድን ይዘው እንደሚገቡ ሲጠበቁ ከፊት መስመር ላይ ያለባቸው መሳሳት ግን የሚቀጥል ይመስላል። በመሆኑም ቡድኑ ከሌሎቹ ተሰላፊዎቹ በተለይም ከቆሙ ኳሶች ግቦችን የሚፈልግበት ጨዋታ ሲሆን ከረጅም ጊዜ ጉዳት በኋላ ሊሰለፍ የሚችለው ስንታየሁ መንግሥቱም ቡድኑ በተሻለ ኳስ ለመያዝ ይሞክራል ተብሎ በሚጠበቅበት ጨዋታ ልዩነት እንዲፈጥር ይጠበቃል።

አርባምንጭ ከተማ ሙና በቀለን ከቀይ ካርድ ቅጣት መልስ የሚያገኝ ሲሆን አንድነት አዳነ ፣ ተካልኝ ደጀኔ እና ፍቃዱ መኮንን በጉዳት ፀጋዬ አበራ በቅጣት ከጨዋታው ውጪ ናቸው። በተመሳሳይ ያሬድ ዳዊት እና ደጉ ደበበን ከጉዳት መልስ የሚያገኘው ወላይታ ድቻ ቃልኪዳን ዘላለም እና ምንይሉ ወንድሙን በጉዳት ሲያጣ ጠንከር ያለ ልምንድ የጀመረው ስንታየሁ መንግሥቱ እንደሚመለስለት ይጠበቃል።

የእርስ በእርስ ግንኙነት

– በሊጉ እስካሁን ከተገናኙባቸው 11 ጨዋታዎች ወላይታ ድቻ 4 አርባምንጭ ከተማ ደግሞ 1 ጊዜ አሸንፈው በ6 ጨዋታዎች አቻ ተለያይተዋል። ወላይታ ድቻ 7 አርባምንጭ ከተማ 2 ግቦች አሏቸው።

የጨዋታው ዳኞች – ዋና ዳኛ ዮናስ ካሳሁን ፣ ረዳቶች ኤፍሬም ኃይለማርያም እና አያሌው አሰፋ ፣ አራተኛ ዳኛ ዮናስ ማርቆስ ፣ ተጨማሪ ዳኞች ማንደፍሮ አበበ እና አለማየሁ ለገሰ።

ግምታዊ አሰላለፍ

አርባምንጭ ከተማ (4-4-2)

ይስሀቅ ተገኝ

ወርቅይታደስ አበበ – ማርቲን ኦኮሮ – በርናንድ ኦቼንግ – መላኩ ኤልያስ

ሙና በቀለ – አቡበከር ሸሚል – እንዳልካቸው መስፍን – ሀቢብ ከማል

አህመድ ሁሴን – በላይ ገዛኸኝ

ወላይታ ድቻ (4-3-3)

ቢኒያም ገነቱ

በረከት ወልደዮሐንስ – ደጉ ደበበ – አንተነህ ጉግሳ – አናጋው ባደግ

ሀብታሙ ንጉሴ – ንጋቱ ገብረስላሴ – እንድሪስ ሰዒድ

አበባየሁ አጪሶ – ስንታየሁ መንግሥቱ – ቢኒያም ፍቅሬ