የድሬዳዋ ኢንተርናሽናል ስታዲየም ማሻሻያ እየተደረገለት ነው

ዐምና እና ዘንድሮ በሊጉ ጨዋታዎች የተደረጉበት የድሬዳዋ ኢንተርናሽናል ስታዲየም ተጨማሪ ሥራዎች እየተከወኑለት ይገኛል።

ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ እየተከናወነባቸው ከሚገኙ ስታዲየሞች አንዱ የሆነው የድሬዳዋ ኢንተርናሽናል ስታድየም የዘንድሮ ኃላፊነቱን በመጀመሪያው ዙር በተደረጉ የስድስት ሳምንት ጨዋታዎች ተወጥቷል። አሁን ደግሞ ስታዲየሙ ለከርሞውም ተመሳሳይ ዕድል እንደሚሰጠው ከግምት ያስገባ የማሻሻያ ስራ እየተሳራበት እንደሆነ ታዝበናል።

በአሁን ሰዓት የኢትዮጵያ አንደኛ ሊግ የማጠቃለያ ውድድር እየተደረገበት የሚገኘው ስታድየሙ ከዘንድሮው ገፅታው ተሻሽሎ ለመቅረብ አዳዲስ ገፅታዎችን እየተላበሰ ነው። በዚህም ቀደም ሲል ግንባታው የተጀመረው የስታዲየሙ እስክሪን የተጠናቀቀ ሲሆን በሀገሪቱ ፈር ቀዳጅ የሚያደርገው የዲጂታል የማስታወቂያ ቦርድ ተከላም ተጀምሮ በመጠናቀቅ ላይ መሆኑን ታዝበናል።

በቀጣይ የመጫወቻ ሜዳውን የማስተካከል ሥራ እንደሚቀጥል እንዲሁም የሚዲያ ክፍሉን በዘመናዊ መንገድ የማዘጋጀት እና ሌሎች የስታዲየሙን ክፍሎች የተመለከቱ ሥራዎችን ለማጠናቀቅ መታሰቡን ሰምተናል።