ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 25ኛ ሳምንት ዓበይት ጉዳዮች (፪) – ተጫዋች ትኩረት

ሁለተኛው የትኩረት ፅሁፋችን በጨዋታ ሳምንቱ ትኩረት በሳቡ ተጫዋቾች ላይ ያተኩራል።

👉 የፋሲል ከነማው አዕምሮ – በዛብህ መለዮ

የአሰልጣኝ ውበቱ አባተ ቀዳሚዎቹ ፈራሚዎች መካከል የነበረው እና ወላይታ ድቻን ለቆ ፋሲል ከነማን ከተቀላቀለ ወዲህ በየዓመቱ ተፅዕኖው እየጎላ የሚገኘው በዛብህ መለዮ አሁን ላይ የቡድኑ ሁለመና ነው ብንል ቅር የሚሰኝ አይኖርም።

መጀመሪያ ወደ ቡድኑ ሲመጣ እንደ አማራጭ ተጫዋች ይታይ የነበረው በዛብህ በሂደት ግን ከተጠባባቂ ወንበር እየተነሳ በሚያሳየው ተስፋ ሰጪ እንቅስቃሴ በቡድኑ ውስጥ የሚሰጠው ሚና እያደገ የመጣ ሲሆን በተለይ ዘንድሮ ደግሞ እጅግ ምርጡን ጊዜ በፋሲል ቤት እያሳለፈ ይገኛል። በዘንድሮው የውድድር ዘመን በፋሲል ከነማ መለያ በርከት ያሉ ጨዋታዎችን ካደረጉ ተጫዋቾች ተርታ የሚመደበው በዛብህ በ22 ጨዋታዎች ላይ የተሰለፈ ሲሆን በውድድር ዘመኑ ስድስት ግቦችን በማስቆጠር በጣምራ የቡድኑ ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ ከሆኑት ፍቃዱ ዓለሙ እና ኦኪኪ አፎላቢ በአንድ ግብ አንሶ ይገኛል። ይህም በተጠናቀቀው የውድድር ዘመን ካስቆጠረው አራት ግብ አንፃር ሲታይ የተሻለ እምርታ ነው።

ለመነሻነት በግብ ማስቆጠር ረገድ ያለውን ቁጥር አነሳን እንጂ በተለይ በሱራፌል ዳኛቸው የፈጠራ አቅም ላይ በጣሙን ጥገኛ ለነበሩት ፋሲል ከነማዎች ዘንድሮ በዛብህ መለዮ የተለየ አማራጭ በመሆን አሁን የቡድኑን የማጥቃት እንቅስቃሴ የሚዘወረው በእሱ ሆኗል። በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት ቡድኑ ቅዱስ ጊዮርጊስን ሲያሸንፍ ወሳኟን ኳስ ለኦኪኪ አፎላቢ ማቀበል የቻለው አማካዩ በአማካይ ስፍራ የተለያዩ ሚናዎችን በሚገባ መወጣት የመቻሉ ነገር ራሱ በጣም የተለየ ያደርገዋል። ከጥልቅ የሚነሳ እንዲሁም ሲያስፈልግ ለአጥቂዎች ቀርቦ መጫወት የሚችለው በዛብህ ወደ ሳጥን ዘግይቶ በመድረስ ኪስ ቦታዎችን በማጥቃትም በሊጉ ወደር አይገኝለትም።

ከዚህ ባለፈም ተጫዋቹ የመከላከል ኃላፊነትን በመወጣት ረገድ የሚታማ አይደለም። አሉታዊ ሩጫዎችን በማድረግ የቡድን አጋሮቹን በመከላከል ለማገዝ የሚጥር ሲሆን በአንድ ለአንድ ግንኙነቶች ወቅት ለተጋጣሚው በቀላሉ እጅ የሚሰጥ አይደለም። እጅግ አስደናቂ የውድድር ዘመን ላይ የሚገኘው አማካዩ ስለዘንድሮው የፋሲል ከነማ የውድድር ዘመን ስናነሳ በአዎንታዊነት ከሚጠቀሱ ተጫዋቾች ቀዳሚው እንዲሆን የሚያስችለውን ብቃት እስካሁን ያሳየ ሲሆን በቀጣይም ቡድኑን የተሻለ ደረጃ ለማድረስ የፋሲላውያን መተማመኛም ነው።

👉 ጊት ጋትኩት እና የኃይል አጨዋወቶቹ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በመጪዎቹ ቀናት ለሚያደርጋቸው የአፍሪካ ዋንጫ ጨዋታዎች ማጣሪያ የ28 ተጫዋቾች ዝርዝር ይፋ ሲደረግ ከተካተቱ ተከላካዮች መካከል የሲዳማ ቡናው ጊት ጋትኩት ይገኝበታል።

በሁሉም ዘንድ አሳማኝ የሆነ እና ለብሔራዊ ቡድን እስከመጠራት ድረስ ያበቃን አስደናቂ የውድድር ዘመን በክለቡ ሲዳማ ቡና እያሳለፈ የሚገኘው ተጫዋቹ ግን በተለይ ከኃይል አጨዋወት ጋር በተያያዘ አንዳንዴ ጥያቄዎች እንዲነሱበት የሚያደርጉ ከብስለት ማነስ የሚነጩ ውሳኔዎችን ሲወስን እየተመለከትነው እንገኛለን። በዚህ ሳምንት ቡድኑ ባህር ዳር ከተማን ሲገጥም ገና በ18ኛው ደቂቃ ላይ ወደ መሀል ሜዳ አካባቢ በሁለት እግሩ አደገኛ አጨዋወት መጠቀሙን ተከትሎ ቢጫ ካርድ የተመለከተው ተጫዋቹ ይህ ካርድ የውድድር ዘመኑ 10ኛ ቢጫ ካርዱ ሆኖ ተመዝግቧል። በዚህም በቀጣይ ሲዳማ በሚያደርጋቸው ሁለት ጨዋታዎች ላይ ግልጋሎት የማይሰጥ ይሆናል። ከዚህ ባለፈም በሁለተኛው አጋማሽ ተደጋጋሚ ጥፋቶችን ሲፈፅም የተመለከትነው ሲሆን በተለይ በ72ኛው ደቂቃ ፍፁም ዓለሙ ላይ የሲዳማ የሳጥን ጠርዝ ላይ የሰራው አደገኛ ጥፋት በዳኛው ታለፈ እንጂ ራሱንም ሆነ ቡድኑን ዋጋ የሚያሰከፍልበት አጋጣሚ በሆነ ነበር።

ይህን ጨዋታ ለአብነት አነሳን እንጂ ባለፉት ጥቂት ጨዋታዎች እንኳን ወደ ኋላ መለስ ብንል ተጫዋቹ በብዙ አጋጣሚዎች እጅግ አደገኛ የሆኑ ጥፋቶችን ሲፈፅም ተመልክተናል። እርግጥ የኃይል አጨዋወት በተገቢው መጠን እና ቦታ ጥቅም ላይ እስከዋለ ድረስ አስፈላጊነቱ ባያጠያይቅም እንደ ጊት ግን ራስን እና ቡድንን አደጋ ላይ በሚጥል እና ከልክ ባለፈ መጠን ጥቅም ላይ ሲውሉ የታለመላቸውን አላማ የመምታታቸው ነገር አነስተኛ እየሆነ መምጣቱ አያጠያይቅም።

በመሆኑም ጥሩ የመሀል ተከላካይ ለመሆን የሚያበቁ በርካታ መስፈርቶችን እንደሚያሟላ እያስመሰከረ የሚገኘው ተከላካዩ ይበልጥ የተሻለ ተጫዋች ለመሆን ይህን አንደኛውን ጉልህ ደካማ ጎኑን መቅረፍ ይኖርበታል።


👉 ብኩኑ ቢኒያም ጌታቸው

አዲስ አበባ ባለፉት ሁለት ጨዋታዎች ስለጣላቸው ነጥቦች እንደ ቡድን ያለው ድክመት እንዳለ ሆኖ በግል ጥሩ አፈፃፀም ያላሳዩ ተጫዋች በተናጠል መጥራት ካስፈለገ በዚህ ዝርዝር ውስጥ ከሚሰፍሩት አንዱ ቢኒያም ጌታቸው መሆኑ የሚያጠራጥር አይደለም።

እንደ አዲስ አበባ ያለ ላለመውረድ እየታገለ የሚገኝ ቡድን አጥቂዎቹ እጅግ ስል እንዲሆኑ በሚጠበቅበት በዚህ ጊዜ አጥቂው ቢኒያም አሰልጣኝ ጳውሎስ ጌታቸው በተደጋጋሚ እምነት አሳድረው እየሰጡት በሚገኘውን ዕድል የሚፈልጉትን እየሰጣቸው ግን አይገኝም። ከድሬዳዋ ከተማ ጋር ተገናኝተው ሲመሩ ቆይተው በመጨረሻ ደቂቃ ሄኖክ አየለ ባስቆጠረባቸው ግብ ነጥብ ለመጋራት በተገደዱበት ጨዋታ በተለይ በሁለተኛው አጋማሽ ሁለት ፍፁም ያለቀላቸውን አጋጣሚዎችን ማግኘት የቻለው አጥቂው በሁለቱም አጋጣሚዎች ከግቡ አፋፍ መገኘት ቢችልም ሙከራዎቹ ኢላማቸውን መጠበቅ ባለመቻላቸው ቡድኑን አደጋ ውስጥ መጣሉ አይዘነጋም።

በተመሳሳይ በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት እንደተለመደው በተለይ በመጀመሪያው አጋማሽ በርከት ያሉ ዕድሎችን የፈጠሩት አዲስ አበባ ከተማዎች በአስቆጪ ሁኔታ ካመከኗቸው ኳሶች ውስጥ እጅግ የተሻሉ የነበሩት አጋጣሚዎች እንዲሁ የመከኑት በቢኒያም ጌታቸው ደካማ አጨራረስ ነበር። አጥቂው ፍፁም ጥላሁንን በጉዳት ላጡት አዲስ አበባ ከተማዎች የተለየ ነገርን ይፈጥራል ተብሎ እምነት ቢጣልበትም ይህን በተግባር ለማሳየት ተቸግሯል። በዚህም መነሻነት ከጨዋታዎች መጠናቀቅ በኋላ በከፍተኛ የሀዘን ስሜት ውስጥ ሆኖ ሜዳውን ሲለቅም እየተመለከትን እንገኛለን።

በከፍተኛ ሊጉ ራሱን ከፍ ባለ ደረጃ ማሳየት የቻለው ቢኒያም በፕሪምየር ሊጉ ዕድል ባገኘባቸው ጨዋታዎች ግብ ለማስቆጠር በሚደረዱ ቦታዎች ላይ ለመገኘት ያለው ግንዛቤ እና ታታሪነት አስደናቂ ቢሆንም ይህንን በጥሩ ውሳኔ አሰጣጥ ማጀብ ካልቻለ በቀጣይ የሊጉ ቆይታው እንዳይቸግር የሚያሰጋ ነው።

👉 የዳዋ ሆቴሳ እና ጌታነህ ከበደ ያልተገባ ድርጊት

የአዳማ ከተማ እና ወልቂጤ ከተማ አምበሎች በጨዋታ ሳምንቱ አላስፈላጊ ድርጊት መፈፀማቸውን ተከትሎ በመጪዎቹ ጨዋታዎች ቡድናቸውን አያገለግሉም።

በጨዋታ ሳምንቱ ለ20ኛ ጊዜ አዳማ ከተማን ወክሎ መጫወት የቻለው ዳዋ ሆቴሳ ቡድኑ ውጤት አጥብቆ ይፈልግ በነበረበት የሰበታ ከተማው ጨዋታ ያልተጠበቀ ተግባርን ፈፅሞ ተመልክተናል።

በውድድር ዘመኑ ለቡድኑ አምስት ግቦችን ማስገኘች የቻለው ዳዋ ከአጥቂ ተጫዋች እምብዛም በማይጠበቅ መልኩ ስድስት ቢጫ ካርዶችን የተመለከተ ሲሆን በተለይም ትልቅ ትርጉም በነበረው በዚህ ሳምንት ጨዋታ አጥቂው ሳይጠበቅ በቀጥታ ቀይ ካርድ የተሰናበትበት መንገድ አነጋጋሪ ነበር። ቀስ በቀስ ራሱን በወራጅ ቀጠናው አካባቢ ያገኘው አዳማ ከዚህ ስጋት ለመላቀቅ እጅግ አስፈላጊው በነበረው ጨዋታ ዳዋ ከኳስ ውጪ በተፈጠረ ያልተገባ የቃላት ልውውጥ በወሳኙ ጨዋታ ገና በ17ኛው ደቂቃ ነበር በቀጥታ ቀይ ካርድ የተወገደው። ታድያ ምስጋና ለቡድን አጋሮቹ ይግባና የቀሩትን ደቂቃዎች በአስደናቂ ተጋድሎ በመጫወት ከጨዋታው ሦስት ነጥብ ይዘው መውጣት ችለዋል።

ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላ አዲሱ የቡድኑ አሰልጣኝ የዳዋን ድርጊት ለመከላከል በሚመስል መልኩ ‘በቡድኑ ላይ ካለው ከፍተኛ ጫና እና ጭንቀት የመነጨ የተፈጠረ ነገር ነው’ በሚል አስተያየት ቢሰጥም በተቃራኒው ውጤቱን አጥተው ቢሆን ኖሮ የሚፈጠረው ሂደት ለማሰብ አይከብድም። የሆነው ሆኖ በዳዋ ደረጃ ልምድ ያለው እና ቡድኑን በአምበልነት እየመራ የሚገኝ ተጫዋቾች ከራሱ ግላዊ መሻት ይልቅ የቡድንን ጥቅም ከግምት ውስጥ ባስገባ ሁኔታ ራሱን በመግዛት ምሳሌ መሆን ሲገባው ይህ ነው የሚባል ፋይዳ በሌለው እሰጥ አገባ ውስጥ የትኩረቶች ማዕከል በመሆን የቀይ ካርድ ተመልክቶ ለተጨማሪ ሦስት ጨዋታዎች ከሜዳ መራቅ የሚጠበቅ አይደለም።

በተጨማሪም በከፍተኛ ግብ አስቆጣሪነት ፉክክር ውስጥ የሚገኘው ጌታነህ ከበደ ቡድኑ ከሀዲያ ሆሳዕና ጋር ነጥብ ሲጋራ በመጨረሻ ደቂቃ ባስተናገዱት ግብ አቻ ከተለያዩበት ጨዋታ መጠናቀቅ በኋላ የጨዋታ አመራሮችን በመዝለፉ በተላለፈበት የቅጣት ውሳኔ መሰረት ቀጣዩቹ ሦስት ጨዋታዎች በቅጣት የሚያልፉት ይሆናል።

ይህም ሊጉን በከፍተኛ አስቆጣሪነት ለማጠናቀቅ በ13 ግቦች ከይገዙ ቦጋለ ጋር ከፊት ሆኖ እየመራ የሚገኘው ተጫዋቹ ለሦስተኛ ጊዜ የሊጉ ከፍተኛ አስቆጣሪ ለመሆን የነበረው ህልም ላይ ተፅዕኖ ከማሳደሩ ባለፈም እንደ ቡድን የሚያሳድርባቸውም ተፅዕኖ በቀላሉ የሚታይ አይሆንም።

👉 የሚካኤል ሳማኪ አስደናቂ ተሳትፎ

ከጥቂት ሳምንታት በፊት አቋሙ ወርዷል ሲባል የነበረው ሚካኤል ሳሚኪ ባለፉት ጥቂት ጨዋታዎች ግን የቀደመ ብቃቱን እያገኘ ይመስላል።

ግብ ጠባቂዎች በመጨረሻዎቹ ጥቂት ጨዋታዎች ጥሩ ጥሩ የሚባሉ ወደ ግብ የሚደረጉ ሙከራዎችን ከማምከን ባለፈ በቆሙ ኳሶች ወቅት ያለው አስደናቂ የሳጥን አጠባበቅ ብቃት እጅግ የሚያስደንቅ ሆኗል። በተለይ ቡድኑ በተጋጣሚ ጫና ውስጥ በሚወድቅባቸው ደቂቃዎች ወቅት በቆሙ ኳሶች በተለይም ወደ ጎን ከተለጠጠ አቋቋም የሚገኙ ቅጣት ምቶች እና የማዕዘን ምቶች ወቅት የሚሻሙ ኳሶች ታሳቢ ወዳደረጓቸው የሳጥኑ ክፍሎች በፍጥነት የግብ ክልሉን ለቆ በመውጣት ኳሶችን የሚከላከልበት መንገድ በጣም አስደናቂ ነበር።

በቅዱስ ጊዮርጊሱ ጨዋታ በተለይ በሁለተኛው አጋማሽ ጊዮርጊሶች ተደጋጋሚ ኳሶችን ከቆሙ ኳሶች በማሻገር ጥረት ቢያደርጉም የሳማኬ አስደናቂ የሳጥን ውስጥ የበላይነት (Cross Engagement) ለፈረሰኞቹ ፈተና ሲሆንባቸው ተመልክተናል። በዚህ የግብ ጠባቂው ክህሎት በተለይ ቡድኑ የቆሙ ኳሶችን በመከላከል ወቅት የሚኖረውን አፈፃፀም በማሻሻል ረገድ ትልቅ ሚና ሲወጣ እየተመለከትን እንገኛለን።

👉 የመጀመሪያ ግባቸውን ያስቆጠሩት ተጫዋቾች

በ25ኛው የጨዋታ ሳምንት አምስት ተጫዋቾች የሊጉን የመጀመሪያ ግቦችን አስመዝግበዋል።

ኢትዮጵያ ቡና ያለ አቡበከር ናስር እና ዊልያም ሰለሞን ሀዋሳ ከተማን ገጥሞ 3-1 በረታበት ጨዋታ ሁለቱ ግቦች የተመዘገቡት በአላዛር ሽመልስ እና አማኑኤል ዮሀንስ ነበር። ሁለቱም ተጫዋቾች በዚህኛው ሳምንት ያገኟቸው ግቦች በውድድር ዘመኑ የመጀመሪያዎቹ ነበሩ።

ከፍፁም ቅጣት ምት ግቧን ያስቆጠረው አማኑኤል ዮሐንስ በሊጉ በ24ኛው ጨዋታ የመጀመሪያ ግቡ ሆና የተመዘገበች ሲሆን ምናልባት አሁን ላይ በተወሰነ መልኩ ከአብነት ደምሴ መምጣት በኋላ ይበልጥ ለተጋጣሚ ሳጥን ቀርቦ እየተጫወተ እንደመገኘቱ ቀጣዩን ግብ ለማግኘት እንደ አሁኑ ብዙ ላይጠብቅ ይችላል። በአንፃሩ ካደረጋቸው 12 ጨዋታዎች 10 የሚሆነውን ተቀይሮ በመግባት ያደረገው እና በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት በቋሚነት የጀመረው አላዛር ይህን ዕድል በሚገባ በመጠቀም እንዲሁ የውድድር ዘመኑን የመጀመሪያ ግቡን አግኝቷል።

በተመሳሳይ ከግብ ርቀው የሰነበቱት አዳማ ከተማዎች ሰበታ ከተማ ላይ ሦስት ግቦችን አስቆጥረው ሲያሸንፎ በተመሳሳይ ሁለቱ ግቦቹ የተገኙት የመጀመሪያ ግባቸው በውድድር ዘመኑ ካስቆጠሩት ደስታ ዮሀንስ እና ዮናስ ገረመው ስም ነበር። አማካዩ ዮናስ ገረመው በ21ኛው ጨዋታው የመጀመሪያ ግቡን ሲያገኝ የግራ መስመር ተከላካዩ ደስታ ዮሐንስ ደግሞ በ23ኛው ጨዋታ ከፍፁም ቅጣት ምት ቢሆንም ግብ አስቆጥሯል። ሌላኛው በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት ግብ በስሙ ያስመዘገበው ወጣቱ የሲዳማ ቡና ተከተላካይ ጊት ጋትኩት ነበር።

👉 ያለ ተጠባባቂ ግብ ጠባቂ ጨዋታውን ያደረገው ጅማ አባ ጅፋር

ጅማ አባ ጅፋር ከአዲስ አበባ ጋር አንድ አቻ በተለያዩበት ጨዋታ የጅማ የቡድን ዝርዝር ላይ ጨዋታውን በቋሚዎቹ መካከል ከጀመረው ወጣቱ ግብ ጠባቂ ለይኩን ነጋሽ ውጪ ግብ ጠባቂ ሳይዙ ያደረጉት ነበር።

10 ተጫዋቾችን በተጠባባቂነት ይዞ የጀመረው ቡድኑ 3 አማካዮች ፣ 1 ተከላካይ እና 6 አጥቂዎችን ይዞ ጀምሯል። ይህም አይበለውና በጨዋታው ጉዳት ወይንም የቀይ ካርድ ስንብት ቢያጋጥም ለይኩንን ሊተካ የሚችለው የሜዳ ላይ ተጫዋች በሆነ ነበር። በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት ቡድኑ በጊዮርጊስ በተሸነፈበት ጨዋታ በቀጥታ ቀይ ካርድ የተሰናበተው አላዛር ማርቆስ አለመኖሩን ተከትሎ ወጣቱ ግብ ጠባቂ ለይኩን ነጋሽ ተክቶት ቢገባም ሌላኛው የቡድኑ ግብ ጠባቂ ታምራት ዳኜ ከስብስብ ውጪ እንደነበር አስተውለናል።

ይህ ሂደት በተለይ ባለፉት ሁለት ዓመታት የጅማ አባ ጅፋር ታሪክ ውስጥ የተለመደ አጋጣሚ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ አሁን ላይ ማስገረሙን ያቆመም ይመስላል። በተጠናቀቀው የውድድር ዘመን የሜዳ ላይ ተጫዋችን በግብ ጠባቂነት የተጠቀሙበት እንዲሁም ያለ ተጠባባቂ ግብ ጠባቂ ጨዋታቸውን ያደረጉባቸው አጋጣሚዎች እንደነበሩ የምናስታውሰው ነው።

👉 ስንታየሁ መንግሥቱ ተመልሷል

ለረጅም ጊዜያት ከሜዳ ርቆ የነበረው የወላይታ ድቻው ፊት አውራሪ ስንታየሁ መንግሥቱ በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት ዳግም በሜዳ ላይ ተመልክተነዋል።

ለመጨረሻ ጊዜ በ16ኛ የጨዋታ ሳምንት ድሬዳዋን ሲረቱ በ63ኛው ደቂቃ ጉዳት አስተናግዶ በአበባየሁ አጪሶ ተቀይሮ የወጣው ስንታየሁ ላለፉት ዘጠኝ ጨዋታዎች በጉዳት ምክንያት ቡድኑን ማገልገል ሳይችል ቀርቷል። በዚህ ወቅትም በተለይ በጨዋታዎች ወቅት ቡድኑ እሱን ፊት መስመር ላይ ምን ያህል አጥቶት እንደነበር በተደጋጋሚ ተመልክተናል።

ከጉዳቱ አስቀድሞ በ14 ጨዋታዎች የቡድኑን የፊት መስመር የመራው ስንታየሁ ለቡድኑ አምስት ግቦችን ማስቆጠር ችሏል። በጉዳት ረዘም ላለ ጊዜ ከሜዳ ርቆ ቢያሳልፍም አጥቂው አሁንም ቢሆን የቡድኑ ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ ነው።

ጥሩ አጥቂ መሆኑን እያስመሰከረ የሚገኘው ስንታየሁ ተደጋጋሚ ጉዳቶች ግን በወጥነት ራሱን እንዳያሳይ ተግዳሮት እየሆኑበት ይገኛል።

👉 ኤዲ ኤሞሞ ንጎይ የመጀመሪያ ጨዋታውን አድርጓል

በውድድር ዘመኑ አጋማሽ የዝውውር መስኮት ሲዳማ ቡናን ተቀላቅሎ የነበረው የዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎው አማካይ ኤዲ ኤሞሞ ንጎይ ስምምነቱን አፍርሶ ወደ ወልቂጤ ከተማ ለማምራት ስለመስማማቱ አይዘነጋም።

አማካዩ ወልቂጤ ከተማን ስለመቀላቀሉ ቢነገርም በተወሰኑ የሁለተኛው ዙር ጨዋታዎች ላይ የዝውውር ሂደቱ በጊዜ አለመጠናቀቃቸውን ተከትሎ ስብስብ ውስጥ መካተት ሳይችል ቢቆይም ወልቂጤ ከተማዎች ከኢትዮጵያ ቡና እና ከሰበታ ከተማ ጋር በነበራቸው ጨዋታዎች ጥቅም ላይ ሳይውል በተጠባባቂነት ቢያሳልፍም በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት ግን በወልቂጤ መለያ የመጀመሪያውን ጨዋታ አድርጓል።

እንደ ቡድን የቅርፅ ለውጥ አድርገው ጨዋታውን የጀመሩት ወልቂጤ ከተማዎች በ3-5-2 አደራደር ኤዲ ኤሞሞ ንጎይ በስድስት ቁጥር ሚና ከበኃይሉ ተሻገር እና ሀብታሙ ሸዋለም ጋር በማጣመር የተጠቀሙበት ቢሆን እንደ መጀመሪያ ጨዋታነቱ እና ቡድኑ በጨዋታው እንደመቸገሩ ደካማ የሚባል የጨዋታ ቀንን አሳልፎ ተቀይሮ ለመውጣት ተገዷል።

ከተከላካዮች ፊት ባለው የስድስት ቁጥር ቦታ ላይ የተለያዩ አማራጮችን እየተጠቀሙ የሚገኙት አሰልጣኝ ተመስገን ዳና አሁንም ቢሆን ለዚህ ቦታ ትክክለኛውን ሰው ያገኙ አይመስልም።