የቻን ማጣሪያ ድልድል ታውቋል

ዋልያዎቹ በቀጣዩ የቻን ውድድር ላይ ለመሳተፍ በማጣሪያው ተጋጣሚዎቻቸውን አውቀዋል።

በሀገር ውስጥ ሊጎች በሚጫወቱ ተጫዋቾች ብቻ የሚደረገው የአህጉሪቱ ውድድር ዘንድሮ በአልጄሪያ አስተናጋጅነት ይከናወናል። በዚህ ውድድር ላይ የሚሳተፉ ሀገራትን ለመለየት ካፍ ከደቂቃዎች በፊት ባወጣው ድልድል መሰረትም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የመጀመሪያ ጨዋታውን ከ ደቡብ ሱዳን ጋር እንደሚያደርግ ታውቋል። ዋልያዎቹ ይህንን ጨዋታ አሸንፈው ወደ ሁለተኛው ዙር ካለፉ ደግሞ ቀጣይ ተጋጣሚያቸው ሩዋንዳ እንደምትሆን በዕጣ ማውጣት ሥነ ስርዓቱ ላይ ታውቋል።

የመጀመሪያው ዙር የመጀመሪያ ጨዋታ ከሐምሌ 16- 18 ባሉት ቀናት ላይ የሚደረግ ሲሆን የመልሱ ጨዋታ ከሐምሌ 22-25 ባሉት ቀናት ላይ ይከናወናል። በተጨማሪ የሁለተኛው ዙር ቀዳሚ ጨዋታዎች ከነሐሴ 20-23 የመልሱ ጨዋታ ደግሞ ከነሐሴ 27-29 ባሉ ቀናት ላይ እንደሚደረግ በሥነ ስርዓቱ ላይ ተገልጿል።