ሌላኛው መከላከያ ወደ ሀገሪቱ ከፍተኛ የሊግ እርከን ተጠግቷል

በሀገሪቱ ሁለት ከፍተኛ የሊግ እርከኖች የመሳተፍ ዕድል ያገኙት እና በመከላከያ ስር የሚገኙትን ቡድኖች በተመለከተ ተከታዩን አጠር ያለ ጥንክር አዘጋጅተናል።

በ1934 ጦር ሠራዊት በሚል ስያሜ የተመሰረተውና በአሁኑ ሰዓት በኢትዮጵያ ከሚገኙ ክለቦች ከቅዱስ ጊዮርጊስ በመቀጠል ሁለተኛው አንጋፋ ቡድን የሆነው መከላከያ በሁለቱም ፆታዎች በፕሪምየር ሊግ ከሚሳተፉ ቡድኖቹ በተጨማሪ የወታደር፣ ከ20 ዓመት በታች፣ ከ17 ዓመት በታች፣ የእጅ ኳስ፣ የመረብ ኳስ እና የስፖርት ለሁሉም (በመስሪያ ቤቱ የሚሰሩ ሰራተኞች የሚሳተፉበት) እንዲሁም በአትሌቲክሱ ከአጭር እስከ ማራቶን ድረስ በስሩ ቡድኖች እንዳሉት ይታወቃል። በቀጣዩ የውድድር ዓመት የጠቀስናቸው ሁሉም ቡድኖች መቻል በሚል ስያሜ ብቅ እንደሚሉ ከሳምንታት በፊት ገልፀን የነበረ መሆኑም አይዘነጋም። እግር ኳሱን በተመለከተ ከእድሜ እና የጤና ቡድኖቹ ውጪ በፕሪምየር ሊጉ ከሚሳተፈው ዋናው ቡድን በተጨማሪ በትናንትናው ዕለት ከኢትዮጵያ አንደኛ ሊግ ወደ ከፍተኛ ሊግ ያደገው የመከላከያ ሁለተኛ ቡድን ደግሞ የብዙዎች መነጋገሪያ ሆኗል።

ሁለተኛው ቡድንን በተመለከተ እና ሁለቱ ቡድኖች በመጪዎቹ ዓመታት በተመሳሳይ ሊግ ላይ እንዲሳተፉ ሊያደርግ የሚያስችል አጋጣሚ ቢፈጠር ምን ሊሆን እንደሚችል ከህግ አግባብ ያለውን ነገር ለማጣራት ሞክረን ተከታዩን ዘገባ አሰናድተናል።

በሀገር መከላከያ ሠራዊት ውስጥ በውትድርና የሚሳተፉ የእግርኳስ ፍቅር እና ተሰጥኦ ያላቸው ግለሰቦችን የሚያቅፈው የመከላከያ ሁለተኛ (ቢ) ቡድን ከሁለት ዓመታት በፊት (2012) ምስረታውን እንዳደረገ ይወሳል። በተለያዩ እዞች በሚከናወኑ የእግርኳስ ውድድሮች የሚታዩ ባለተሰጥኦዎችን በመሰብሰብ የተዋቀረው ቡድን በምስረታው ዓመት በኢትዮጵያ ክልሎች ሻምፒዮና መሳተፍ ከጀመረ በኋላ በተከታታይ ወደ አንደኛ ሊግ ከዛም ዘንድሮ ወደ ከፍተኛ ሊግ በማደግ ለዋናው የሊግ እርከን ለመብቃት አንድ ደረጃ ብቻ ቀርቶታል።

ከእድሜ እርከን እና ዋና የፆታ ቡድኖቹ ውጪ ያሉትን የስፖርት አይነቶች በሰራዊቱ አባላት ያዋቀረው መከላከያ በእግርኳሱ ዘርፍም የሰራዊቱን አባላት ለማሳተፍ በማቀድ ትናንት ወደ ከፍተኛ ሊግ ያደገውና “መከላከያ ቢ” እየተባለ የሚጠራ ቡድን ማቋቋም እንዳስፈለገ የመከላከያ ስፖርት ክለብ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ኮሎኔል ደረጄ መንግሥቱ ይናገራሉ። “ዋና ዓላማው የሰራዊቱን አባላት በሌሎች የስፖርት አይነቶች እንዳሳተፍነው በእግርኳሱም እናሳትፈው የሚል ነው። ” የሚሉት ኮሎኔል ደረጄ ” ከዚሁ ጋር ተያይዞ በዋናው ቡድን የሚኖሩትን የሰራዊቱ አባላት እያሰፋን እንሄዳለን ብለን ነው ዓላማ ይዘን የጀመርነው። ይሄንንም ለማድረግ ከታች ከግንባር ጀምሮ የተሻለ ብቃት ያላቸውን እያደራጀን ነው ቡድኑን ያዋቀርነው። ወደ ከፍተኛ ሊግ ያደገው ቡድን ውስጥም አብዛኛው ተጫዋች ከግንባር የተገኘ እና ባለ ማዕረግ ነው። እንዳልኩት ተቀዳሚው እቅድ ዋናው ቡድን ላይ ያለውን የሰራዊቱን ተሳትፎ ለማስፋት ነው። ግን ይሄን ነገር በአንድ ጊዜ ማድረግ ስለማይቻል ቀስ በቀስ ለማድረግ ነው ያሰብነው። እንደሚታወቀው ከድሮም ጀምሮ ቡድኑ በሠራዊቱ የተገነባ እና የተጠናከረ ነው። ስለዚህ አሁንም ይሄንን ለማጠናከር ነው “ቢ” ቡድኑን በጥሩ ሁኔታ ያደራጀነው።” ብለውናል።

ዳይሬክተሩ ወደ ከፍተኛ ሊግ ያደገው የመከላከያ ቢ ቡድን በቀጣዩ ዓመት (2015) በሊጉ ተሳትፎ ወደ ፕሪምየር ሊጉ ቢያድግ በሠራዊቱ ብቻ የተቋቋመ ቡድን ስለሆነ ከዋናው ቡድን ጋር ሳይጋጭ የሚሳተፍበትን ዕድል አመራሩ ሊያመቻች እንደሚችል ቢገልፁም ከህግ አግባብ በአንድ ተቋም ስር የሚገኙ ሁለት ቡድኖች በተመሳሳይ ሊግ ሊሳተፉ ይችላሉ ወይ? የሚለውን ጉዳይ ከሚመለከተው አካል ለማጣራት ሞክረናል። በዚህም የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን የውድድር ዳይሬክተር የሆኑት አቶ ከበደ ወርቁን አግኝተን ተከታዩን ምላሽ ተቀብለናል።

“እውነት ለመናገር በደንብ ደረጃ የተቀመጠ ነገር እስካሁን የለንም። እንደዚህ አይነት ነገሮች ከስንት አንድ ጊዜ ነው የሚፈጠሩት። ቢሆንም ግን ማሰሪያ ነገር ያስፈልጋቸዋል። ስለዚህ በቀጣይ ቁጭ ብለን ተነጋግረን ለጉዳዩ መፍትሔ እንፈልጋለን። ግን የመከላከያን ጉዳይ ከወሰድን በፊት ከነበሩት አመራሮች ጋር በቃል ደረጃ የተነጋገርነው የ”ቢ” ቡድኑ ለዋናው መጋቢ እንደሆነ ነበር። ቢሆንም ግን መከላከያን ብቻ ሳይሆን ሁሉንም ክለቦች የሚያቅፍ ደንብ በቀጣይ ለማዘጋጀት እንሞክራለን።” በማለት ሀሳባቸውን አጋርተውናል።

ያነሳነውን ጉዳይ የተመለከተ ህጋዊ ማዕቀፍ አለመኖሩ አግራሞትን የሚያስጭር ቢሆንም ከመከሰቱ በፊት ግን ጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልጋል። ለምሳሌ እንኳን በሊጉ የሚሳተፈው ዋናው ቡድን ወደ ከፍተኛ ሊጉ ቢወርድ አልያም ከላይ እንደገለፅነው የ”ቢ” ቡድኑ በቀጣዩ ዓመት ወደ ፕሪምየር ሊጉ ቢያድግ ምን መሆን እንዳለበት ቀድሞ ማሰብ እንደሚገባ እንደ ሚዲያ መጠቆም እንወዳለን። እንደ ተሞክሮ አንዳንድ የአውሮፓ ሀገራት ይህንን አይነት ሂደት የማይደግፉ ሲሆን በከፍተኛው የሊግ እርከን የሚሳተፈው ዋናው ቡድን ሁለተኛው ቡድን ወደሚሳተፍበት ሊግ የመውረድ ዕድል ቢገጥመው ወደ ቀጣዩ (3ኛው) ሊግ እንዲወርድ እንደሚደረግ አልያም ሁለተኛው ቡድን ዋናው ቡድን ወደሚወዳደርበት ከፍተኛ ሊግ የማደግ አጋጣሚ ቢያገኝ እንኳን ተግባራዊ እንዳይሆን እንደሚደረግ እናስተውላለን። የሌሎች ሀገራት ተሞክሮ እንዳለ ሆኖ እኛም ሀገር በራሳችን ልክ የተሰፋ ደንብ ጉዳዩ ከመከሰቱ በፊት እንዲዘጋጅ በአፅንኦት እንጠቁማለን።

ኮሎኔል ደረጄ እስካሁን የተፃፈ ህጋዊ አግባብ ባይኖርም ወደፊት ከኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን እና የፕሪምየር ሊጉ አክሲዮን ማኅበር ጋር በመነጋገር በሚቀመጡ አቀጣጫዎች ክለቡ ለመጓዝ ዝግጁ እንደሆነ ጠቅሰውልናል።