ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ | 25ኛ ሳምንት ምርጥ 11

በቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 25ኛ ሳምንት በተደረጉት ጨዋታዎች ላይ በመመስረት ተከታዩን ምርጥ ቡድን አሰናድተናል።

አሰላለፍ፡ 4-4-2 ዳይመንድ

ግብ ጠባቂ

ቢኒያም ገነቱ – ወላይታ ድቻ

በቀዳሚ ተሰላፊነት መመረጥ ይቀጠለው ቢኒያም ሌላ ጥሩ ብቃት ያሳየበትን ዘጠና ደቂቃ አሳልፏል። በተለይም የጊዜ አጠባበቁ እና ጥንቁቅነቱ ወላይታ ድቻን ከተሻጋሪ ኳሶች አድጋ ጠብቆት ሲታይ በመጨረሻ ደቂቃ ለአርባምንጭ ከተማ ሦስት ነጥብ ለማስገኘት የተቃረበው የአሸናፊ ኤልያስን አስደንጋጭ ሙከራ በአስገራሚ ቅልጥፍና ያዳነበት መንገድ የሚያስጨበጭብ ነበር።

ተከላካዮች

እንየው ካሳሁን – ድሬዳዋ ከተማ

ለወትሮው በማጥቃት ሚናው የሚታወቀው ተጫዋቹ በ25ኛው ሳምንት ደግሞ ጥሩ የመከላከል ሚና ነበረው። ቡድኑ ከመከላከያ ጋር ነጥብ በተጋራበት ጨዋታ የተጋጣሚውን ዋነኛ የማጥቃት መሳሪያ ከግራ የሚነሳው ቢኒያም በላይ እንቅስቃሴን በአግባቡ መቆጣጠር ሲችል ከቢኒያም መቀየር በኋላ ደግሞ ወደ ማጥቃት ተሳትፎው ተመልሶ ተመልክተነዋል።

ያሬድ ባየህ – ፋሲል ከነማ

የዐፄዎቹ አምበል በቀደመ ብቃቱ ላይ ባለመገኘቱ ትችት ሲያስተናግድ ቢቆይም ለቡድኑ ወሳኝ በነበረው ጨዋታ ላይ ጎልቶ መውጣት ችሏል። የቅዱስ ጊዮርጊስን ጥቃቶች ለማቋረጥ በተረጋጋ ሁኔታ የተከላካይ መስመሩን መምራት የቻለው ያሬድ የቡድኑን የኳስ ፍሰት ያስጀምርበት የነበረበት መንገድም የፋሲልን የማጥቃት ሂደት በአግባቡ ከሜዳው እንዲወጣ የሚያስችል ነበር።

ሚሊዮን ሰለሞን – አዳማ ከተማ

አዳማ ከተማ ዳዋ ሆቴሳን በቀይ ካርድ ካጣ በኋላ ለረጅም ደቂቃዎችን በአስር ተጫዋች ለመጨረስ ሲገደድ የሚሊዮን የመከላከል ንቃት ተጠቃሚ አድርጎታል። የተጫዋቹ ሸርተቴዎች እና ጊዜ አጠባበቅ ቡድኑ በወሳኝ ቅፅበቶች እና አደገኛ የሜዳ ክፍሎች ላይ የቁጥር ብልጫው ችግር ውስጥ እንዳይከተው በማድረግ ሚሊዮን ጥሩ የጨዋታ ቀን አሳልፋል።

ደስታ ዮሐንስ – አዳማ ከተማ

በጨዋታ ሳምንቱ ከታዩ የግራ መስመር ተከላካዮች መካከል በግቦች ላይ ቀጥተኛ ተሳትፎ በማድረግ ደስታ ቀዳሚው ነበር። አዳማ አመዛኙን ደቂቃ በጎዶሎ ተጫዋች ለመዝለቅ ቢገደድም ከመከላከል ባለፈ በተለይ በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች በሜዳው የላይኛው ክፍል ላይ ጥሩ ጫና መፍጠር የቻለው ደስታ የፍፁም ቅጣት ምት ግብ ሲያስቆጥር ሦስተኛዋን ጎል ማመቻቸትም ችሏል።

አማካዮች

ይሁን እንዳሻው – ፋሲል ከነማ

እጅግ ተጠባቂ በነበረው ጨዋታ ይሁን የዐፄዎቹ የአማካይ ክፍል ጉልበት ሆኖ አሳልፏል። ከተከላካይ መስመሩ ፊት በነበረው ቦታ ላይ የተጋጣሚ አማካዮች ፊት ላይ ክፍተት እንዳያገኙ ጥሩ ሽፋን ሲሰጥ የታየ ሲሆን በአንድ ለአንድ ግንኙነቶች ላይ የነበረው ኳስ የማስጣል ብቃትም ቡድኑ መሀል ሜዳ ላይ ከፍ ያለ ብልጫ እንዳይወሰድበት ወሳኝ ነበር።

ቻርለስ ሪባኑ – አዲስ አበባ ከተማ

በአዲስ አበባ ውጤት ማጣት ውስጥም ቢሆን ናይጄሪያዊው አማካይ ከሳምንት እስከ ሳምንት የሚጠበቅበትን ማድረጉን ቀጥሏል። በጅማው ጨዋታ አመዛኙን ደቂቃ ከወትሮው ሚናው ወደ ፊት ገፋ ብሎ የተጫወተው ሪባኑ እንደወትሮው በታታሪነት የአማካይ ክፍሉን ሲሸፍን የግብ ዕድሎችን በመፍጠር እና ሙከራዎችን በማድረግ ጭምር በቡድኑ ጥቃቶች ላይ ተሳትፎ ነበረው።

ዳዊት ተፈራ – ሲዳማ ቡና

በአዲሱ አሰልጣኙ ስር ከዚህ ቀደም ከነበረው ይበልጥ ለማጥቃት ወረዳው ገፍቶ መጫወት የጀመረው ዳዊት የማጥቃት ተሳትፎው ጨምሮ ታይቷል። ቡድኑ ባህር ዳርን ባሸነፈበት ጨዋታ በመከላከሉ ከማገዝ በተጨማሪ ለፈጣን ጥቃት የሚሆኑ ኳሶችን በቶሎ ያደርስ የነበረ ሲሆን አንድ ኢላማውን የጠበቀ ሙከራ ከማድረግ ባለፈ የሲዳማን አሸናፊነት ያጠናቀቀችውን ጎል በግሩም ሁኔታ ማመቻቸት ችሏል።

ዮናስ ገረመው – አዳማ ከተማ

አዳማ ከተማ አዘውትሮ ከሚጠቀምባቸው አማካዮች መካከል አንዱ የሆነው ዮናስ በመረጥነው የዳይመንድ ቅርፅ ባለው አሰላለፍ ውስጥ የፊተኛውን ቦታ ሰጥተነዋል። አዳማ ሰበታን በረታበት ጨዋታ ለተጋጣሚ ሳጥን ቀርቦ የማጥቃት ሂደቱን ሲዘውር የነበረው አማካዩ ለፍፁም ቅጣት ምት መገኘት ምክንያት ሲሆን ማሳረጊያዋን ግብም ከመረብ ማሳረፍ ችሏል።

አጥቂዎች

አላዛር ሽመልስ – ኢትዮጵያ ቡና

የፊት መስመሩ ላይ በዋናነት የሚጠቀምባቸው ተጫዋቾች ባልነበሩበት ጨዋታ ቡና ሀዋሳን ሲረታ አላዛር ልዩነት ፈጣሪ ሆኗል። በተሰጠው ዕድል የቀኙን የማጥቃት ክፍል ስልነት ጨምሮ በልበ ሙሉነት ባደረገው ጨዋታ ቡድኑን አቻ ያደረገች ግብ በድንቅ ቅጣት ምት ሲያስቆጥር አሸናፊነታቸውን ያረጋገጠችው የፍፁም ቅጣት ምት እንድትገኝም ምክንያት መሆን ችሏል።

ሀብታሙ ገዛኸኝ – ሲዳማ ቡና

በሲዳማ ቡና ውስጥ የነበረው ልዩነት ፈጣሪነት ቀዝቅዝ ብሎ የቆየው ሀብታሙ በባህር ዳር ላይ ላሳኩት ድል ቁልፍ ሚና ነበረው። ለመልሶ ማጥቃት ምቹ አጥቂ መሆኑን ባሳይበት ጨዋታ ለይገዙ ቦጋለ ጎል ኳስ ማመቻቸት ሲችል ሦስተኛውን ጎል ከዳዊት ተፈራ የደረሰውን ኳስ አስደናቂ በሆነ መልኩ ተቆጣጥሮ ከመረብ ያገናኘበት መንገድ ደግሞ ድንቅ ነበር።

አሰልጣኝ፡ ኃይሉ ነጋሽ – ፋሲል ከነማ

በ25ኛው ሳምንት በመሸናነፍ ከተጠናቀቁ ጨዋታዎች ውስጥ ትልቅ ትርጉም የነበረው የፋሲል ከነማ የ1-0 ድል ነበር። ቡድኑን በኃላፊነት ከተረከበ በኋላ አስደናቂ ጉዞ በማድረግ ላይ የሚገኘው አሰልጣኝ ኃይሉ ይህንን እጅግ ወሳኝ ጨዋታ ጥንቃቄ በተሞላበት መንገድ አሸንፎ መውጣት መቻሉ ደግሞ ለሁለተኛ ጊዜ የሳምንቱ ምርጥ አሰልጣኝ አድርገን እንድመርጠው ምክንያት ሆኗል።

ተጠባባቂዎች

ሚኬል ሳማኬ – ፋሲል ከነማ
አዉዱ ናፊዩ – ድሬዳዋ ከተማ
አምሳሉ ጥላሁን – ፋሲል ከነማ
ምንተስኖት አዳነ – መከላከያ
ፍቅረየሱስ ተወልደብርሀን – ሀዲያ ሆሳዕና
አሸናፊ ኤልያስ – አርባምንጭ ከተማ
አቤል እንዳለ – ኢትዮጵያ ቡና
ብሩክ በየነ – ሀዋሳ ከተማ