አሠልጣኝ ፍሬው ኃይለገብርኤል ወደ ዩጋንዳ ጉዞ ጀምረዋል

ለሴቶች የሴካፋ ዋንጫ ተሳትፎ ትናንት ከቡድኑ ጋር ያልተጓዙት አሠልጣኝ ፍሬው ኃይለገብርኤል ወደ ዩጋንዳ ጉዞ ጀምረዋል።

ዛሬ በይፋ በጀመረው የሴካፋ የሴቶች ውድድር ላይ ለመሳተፍ የኢትዮጵያ ሴቶች ብሔራዊ ቡድን ትናንት ወደ ስፍራው ማቅናቱ ይታወሳል።

ታዲያ ዋና አሰልጣኙ ፍሬው ኃይለገብርኤል ከልዑካን ቡድኑ ጋር አብረው አለመጓዛቸውን ከሰዓታት በፊት መዘገባችን ይታወሳል። አሰልጣኝ ፍሬው ኃይለገብርኤል ማምሻውን ለሶከር ኢትዮጵያ እንደገለፁት ከሆነ በግል ጉዳይ ምክንያት እንዳልተጓዙ እና አሁን ወደ ዩጋንዳ ለማቅናት መሳፈራቸውን በመግለፅ ነገ ማለዳ ቡድኑን በመቀላቀል በከሰዓቱ ጨዋታ ቡድኑን እንደሚመሩ አረጋግጠውልናል።

ሉሲዎቹ ነገ የመጀመርያውን የምድብ ጨዋታቸውን ከዛንዚባር ጋር ቀትር 07:00 ላይ የሚያደርጉ ይሆናል።