ሉሲዎቹ የሴካፋ ዋንጫን በድል ጀምረዋል

በሴካፋ ሴቶች ዋንጫ በመጀመሪያ ጨዋታው ዛንዚባርን የገጠመው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን 5-0 በሆነ ውጤት አሸንፏል።

በምድብ ሁለት የሚገኙትን ኢትዮጵያ እና ዛንዚባርን ያገናኘው ጨዋታ ቀትር 7፡00 ሲል ተደርጓል፡፡ በ4-3-3 የጨዋታ አደራደር ወደ ሜዳ የገቡት ሉሲዎቹ ገና ጨዋታው ከተጀመረ ሁለት ያህል ደቂቃ ብቻ እንደተቆጠረ መሪ መሆን ችለዋል፡፡

2ኛው ደቂቃ ላይ ከቀኝ መስመር በረጅሙ የደረሳትን ኳስ አረጋሽ ካልሳ ከተከላካዮች መሀል ፍጥነቷን ተጠቅማ በመውጣት ኳስ እና መረብ በማገናኘት ሀገሯን ወደ 1-0 መሪነት አሸጋግራለች፡፡ ከፍ ባለ የራስ መተማመን ኳስን በንክኪ በመጫወት በዛንዚባር ላይ የጨዋታ ብልጫን መውሰድ የቻሉት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ተጫዋቾች በተለይ መሳይ ተመስገን እና አረጋሽ ካልሳ በሚያሳዩት ድንቅ ጥምረት መነሻነት የመስመር አጨዋወትን በደንብ ተግባራዊ በማድረግ በተደጋጋሚ ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል ሲደርሱ ተስተውሏል፡፡

12ኛ ደቂቃ ላይ ንቦኝ የን ከመሳይ ተመስገን ጋር ጥሩ ቅብብልን ካደረገች በኋላ በመጨረሻም መሳይ የደረሳትን ኳስ ወደ ጎል አክርራ መትታ ለጥቂት በግቡ አግዳሚ ታኮ ወጥቶባታል፡፡ የኢትዮጵያን የኳስ ቅብብል ለመግታት የተጫዋች ለውጥ በማድረግ ወደ ጨዋታ ለመመለስ ዛንዚባሮች ያደረጉት ጥረት እምብዛም ፍሬያማ ነበር ማለት አይቻልም፡፡ ይሁን እንጂ ተሽለው በአጋማሹ የቀረቡት የአሰልጣኝ ፍሬው ኃይለገብርኤል ሉሲዎቹ 27ኛ ደቂቃ ላይ በሎዛ አበራ ግብ የጎል መጠናቸውን ከፍ ማድረግ ችለው ወደ መልበሻ ክፍል 2-0 በሆነ ውጤት ወጥተዋል፡፡

ጨዋታው ከዕረፍት ሲመለስ ልክ እንደ ቀዳሚው አርባ አምስት ሁሉ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በእንቅስቃሴም ሆነ የጠሩ የግብ ዕድሎችን በመፍጠሩ ረገድ የተሻለ ሆኖ ሲታይ ደካማ የአጋማሽ ቆይታ የነበራቸው ዛንዚባሮች አንድ ኢላማውን ካልጠበቀ ሙከራ ውጪ ወደ ኢትዮጵያ የግብ ክልል ለመድረስ ፍፁም ተቸግረዋል፡፡ 54ኛ ደቂቃ ላይ በጨዋታው የመሀል ሜዳ ክፍሉን በመቆጣጠሩ ረገድ የተዋጣላት ኝቦኝ የን ሰንጣቂ ኳስ ለረድኤት ሰጥታት ረድኤትም ለሎዛ በፍጥነት አቀብላት አምበሏ ወደ ጎልነት ለውጣው ለራሷ ሁለተኛ ለቡድኑ ሦስተኛ ግብ አድርገዋለች፡፡ ብርቱካን ገብረክርስቶስን በአረጋሽ ካልሳ ፣ ናርዶስ ጌትነትን በአሪያት ኦዶንግ ፣ ንግስት በቀለን በማዕድን ሳህሉ አሰልጣኝ ፍሬው ከለወጡ በኋላ ይበልጥ የቡድኑ የማጥቃት ሂደት ከፍ እንዲል ሆኗል፡፡

72ኛው ደቂቃ ላይ በዚህ የጨዋታ ጫና ከቅጣት ምት የተገኘን ኳስ ኝቦኝ የን ስታሻማው ተከላካይዋ ቅድስት ዘለቀ በግንባር በመግጨት አራተኛ ጎል አድርጋዋለች፡፡ 85ኛው ደቂቃ ላይ ደግሞ ከማዕዘን መሳይ አሻምታ ቅድስት ዘለቀ ለራሷ ሁለተኛ ለቡድኗ አምስተኛ ጎል በግሩም ሁኔታ ከመረብ አሳርፋለች፡፡ በቀሩት ደቂቃዎች በሎዛ ፣ ረድኤት ፣ መሳይ እና ንግስት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ጥቃት መሰንዘር ቢችልም በዕለቱ ጥሩ ለመንቀሳቀስ የቻለችው የዛንዚባር ግብ ጠባቂ ሲዌና ያሲን አማካኝነት ተጨማሪ ጎል ሳይቆጠር ጨዋታው በኢትዮጵያ 5-0 አሸናፊነት ተጠናቋል፡፡

የተጠቀምናቸውን መስሎች ያገኘነው ከዩጋንዳ እግርኳስ ፌዴሬሽን ማህበራዊ ገፆች ነው