ሪፖርት | ዋልያዎቹ ማጣሪያቸውን በሽንፈት ጀምረዋል

የአፍሪካ ዋንጫ የምድብ ማጣሪያ የመጀመሪያ ጨዋታውን ከሜዳው ውጪ ያደረገው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በማላዊ አቻው 2-1 ተረቷል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ፋሲል ገብረሚካኤልን በግብ ብረቶቹ መሐል ሲያደርግ ረመዳን የሱፍ ፣ ምኞት ደበበ ፣ ያሬድ ባየህ እና አስራት ቱንጆን በተከላካይ እንዲሁም መስዑድ መሐመድ ፣ አማኑኤል ዮሐንስ እና ሱራፌል ዳኛቸውን በአማካይ መስመር በማጣመር በአጥቂ ቦታ ላይ ደግሞ ዳዋ ሆቴሳ፣ አቡበከር ናስር እና አማኑኤል ገብረሚካኤል እንዲጫወቱ በማድረግ ለጨዋታው ቀርቧል።

ጨዋታው ከመጀመሩ ከደቂቃዎች በፊት ትኬት ያልያዙ ደጋፊዎች ወደ ስታዲየም ለመግባት ባደረጉት ያልተገባ ጥረት ከፀጥታ አካላት ጋር ግጭት ሲፈጥሩ ነበር። የሆነው ሆኖ ከስታዲየም ውጪ የነበረው ግርግር ረግቦ የጀመረው ጨዋታ በሚገርም የደጋፊዎች ድባብ ታጅቦ መከናወን ይዟል። ከጅምሩ አንስቶ ፍጥነት የታከለበት ቀጥተኛ አጨዋወት መከተል የመረጡት ማላዊዎች ገና በሦስተኛው ደቂቃ መሪ ሊሆኑ ተቃርበው ነበር። በዚህም ግብ ጠባቂው ፋሲል ገብረሚካኤል እግሩ ላይ ያዘገየውን ኳስ ተጭኖ እንዲሳሳት በማድረግ የጨዋታውን የመጀመሪያ ዕድል ፈጥረዋል። ከኳስ ጋር ጊዜ ለማሳለፍ ያሰበ የሚመስለው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ደግሞ በ7ኛው ደቂቃ ዳዋ ሆቴሳ ወደ ግራ ባዘነበለ ቦታ ያገኘውን ኳስ መሬት በመሬት በመላክ ጥቃት ሰንዝሯል። ይህ ሙከራ ከተደረገ ከሁለት ደቂቃዎች በኋላ ግን ኳስ እና መረብ የተገናኘበት ሁነት ተፈጥሯል። በዚህም ያሬድ ባየህ በሳጥን ውስጥ ቺምዌምዌ ኢዳና ላይ ጥፋት ሰርቶ የፍፁም ቅጣት ምት የተሰጠ ሲሆን አጋጣሚውንም ጋባዲኖ ማሀዶ አስቆጥሮት ጨዋታው መሪ አግኝቷል።

የሚፈልጉትን በጊዜ ያገኙት ባለሜዳዎቹ ብልጠት የተሞላበት አጨዋወታቸውን በመከተል በወሳኝ የሜዳ ላይ ፍልሚያዎች ላይ ብቻ ብልጫ እየወሰዱ መንቀሳቀስ ሲይዙ ተጋባዦቹ ደግሞ በማጥቃቱም ሆነ በመከላከሉ ረገድ የተረጋጋ አጨዋወት ሳያሳዩ ጨዋታው ቀጥሏል። በተለይ ከኳስ ውጪ ያላቸውን አደረጃጀት ቶሎ መከወን ተስኗቸው ራሳቸውን አደጋ ላይ ሲጥሉ ተስተውሏል። በ26ኛው ደቂቃም የግቡ ባለቤት ጋባዲኖ ማሀዶ ከመሐል ሜዳ ከረመዳን የሱፍ የተቀበለውን ኳስ ግብ ጠባቂው ፋሲል ክልሉን ለቆ መውጣቱን ተመልክቶ መትቶ ለጥቂት ወጥቶበታል። 33ኛው ደቂቃ ላይ ደግሞ ሌላኛው የመሐል ተከላካይ ምኞት ደበበ በድጋሚ በሳጥን ውስጥ ጥፋት ሰርቶ ማላዊ ሁለተኛ የፍፁም ቅጣት ምት ያገኘች ሲሆን ሁለተኛውንም አጋጣሚ ጋባዲኖ ማሀዶ ወደ ጎልነት ቀይሮታል።

የጨዋታው ውጤት ከቁጥጥራቸው ውጪ እየሆነ የመጣባቸው ዋልያዎቹ በ40ኛው ደቂቃ አማኑኤል ላይ የተሰራን ጥፋት ተከትሎ ሱራፌል ዳኛቸው በሞከረው የቅጣት ምት እንዲሁም በ43ኛው ደቂቃ አስራት ቱንጆ ከቀኝ መስመር አሻምቶ አቡበከር ናስር በግንባሩ ወደ ግብ በላከው ኳስ ግብ ሊያገኙ ተቃርበው ነበር። ነገር ግን ውጥናቸው ሳይሰምር እየተመሩ ወደ መልበሻ ክፍል አምየአፍሪካ

በሁለተኛው አጋማሽ ሽመልስ በቀለ እና ጋቶች ፓኖምን በመስዑድ መሐመድ እና ሱራፌል ዳኛቸው ተክተው ወደ ሜዳ ያስገቡት አሠልጣኝ ውበቱ አባተ ቡድናቸው በአብዛኛው የጨዋታ ምዕራፎች ብልጫ ወስዶ ታይቷል። በተለይ በሽግግሮች ላይ የነበረው ድክመት ተሻሽሎ የማላዊ የግብ ዕድል መፍጠሪያ አማራጭ ተዳክሞ ነበር። ይህ ቢሆንም ግን በ52ኛው ደቂቃ ክሁዳ ምያባ በግንባሩ የሞከረው እንዲሁም በ58 እና 59ኛው ደቂቃዎች ልዩነት የተሰነዘሩት ሦስት ተከታታይ ጥቃቶች የቡድኑን መሪነት ወደ ሦስት ሊያሳድጉ እጅግ የተቃረቡ ነበሩ። በመሐል ግን ሽመልስ ጥሩ ኳስ ከወደ ግራ የሳጥኑ ክፍል ተገኝቶ የመታውን ተከላካዮች መልሰውበታል።

ዕረፍት ሰዓት ላይ ከተቀየሩት ተጫዋቾች ድንቅ የነበረው ጋቶች ፓኖም የቡድኑን የአማካይ መስመር ሚዛናዊ ካደረገው በኋላ ዋልያው በመጀመሪያው አጋማሽ አጥቶት የነበረውን የግብ ዕድሎችን የመፍጠሪያ መንገድ አግኝቶ በተደጋጋሚ ወደ ላይኛው ሜዳ ሲሄድ ነበር። በ60ኛው ደቂቃ ደግሞ የተገኘውን ዕድል ከግብነት የታደገው የግቡ አግዳሚ ነበር። በተጠቀሰው ደቂቃ አቡበከር በተከላካዮች መሐል ራሱን ነፃ አድርጎ ተገኝቶ በደካማ ግራ እግሩ የመታው ጥብቅ ኳስ ለጥቂት ወጥቷል።

ይህ የቡድኑ ዕድገት ቀጥሎ በ68ኛው ደቂቃ ፍሬ አፍርቷል። በዚህም በ66ኛው ደቂቃ ተቀይሮ የገባው ቸርነት ጉግሳ ከደቂቃ በኋላ ጥፋት ተሰርቶበት የተገኘውን የፍፁም ቅጣት ምት አቡበከር አስቆጥሮታል። 

ወደ ጨዋታው ሊመለሱ የሚችሉበትን ግብ ያገኙት ዋልያዎቹ በቀጣዮቹም ደቂቃዎች በማላዊ ሜዳ ኳስ መያዛቸውን ቀጥለዋል። ነገር ግን በእጃቸው የገባውን ሦስት ነጥብ ማጣት ያልፈለጉትን የማላዊዎች የኋላ መስመር ሰብረው መግባት ተስኗቸው ጨዋታው ተጠናቋል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የምድብ ሁለተኛ ጨዋታውን የፊታችን ሐሙስ እዛው ማላዊ ላይ ከግብፅ አቻው ጋር የሚያደርግ ይሆናል።