ወልቂጤ ከተማዎች ዝግጅታቸውን አልጀመሩም

አሰልጣኝ ተመስገን ዳና ከአንድ ሳምንት በፊት ለተጫዎቻቸው ጥሪ ቢያደርጉም ቡድኑ እስካሁን ለዝግጅት አልተሰበሰበም።

በአፍሪካ ዋንጫ ማጣርያ ጨዋታዎች ምክንያት ከተቋረጠ በኋላ ሰኔ 7 በሚጀምረው ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ውድድር አብዛኛዎቹ ክለቦች ከቀናት በፊት ዝግጅታቸውን በመጀመር እየሰሩ ይገኛሉ። በአሰልጣኝ ተመስገን ዳና የሚመሩት ክትፎዎቹ ለተጫዋቾቻቸው ለቀናት ዕረፍት በመስጠት ባሳለፍነው ሳምንት ሰኞ ዝግጅት ለመጀመር ሁሉም የቡድኑ አባላት ወደ ባህር ዳር እንዲጓዙ ጥሪ አስተላልፈው ነበር።

ሆኖም ይህን ዘገባ እስካጠናከርንበት ጊዜ ድረስ አሰልጣኝ ተመስገን ዳና እና ምክትላቸው ብቻ በመሆን የተቀሩትን የቡድኑ አባላትን ይመጣሉ በማለት ቢጠብቁም እስከ ዛሬ ድረስ ዝግጅት መጀመር አለመቻላቸውን አረጋግጠናል። ተጫዋቾቹ ተሰባስበው ዝግጅት ያለመጀመራቸው ምክንያት ምን እንደሆነ ባደረግነው ማጣራት የሦስት ወር ደመወዝ እንዳልተከፈላቸው እና ክፍያው እስካልተፈፀመ ድረስ ወደ ባህር ዳር እንደማይጓዙ ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ የቡድኑ አባላት ገልፀው ነገ ተፈራርመው ለሚመለከተው አካላት ሁኔታውን እንዲያውቁ ደብዳቤ እንደሚያስገቡ ሰምተናል።

አሰልጣኝ ተመስገን ዝግጅት መጀመር በሚገባው ጊዜ አለመጀመራቸውን ተከትሎ ከዚህ በኋላ ለሚፈጠው ማንኛውም ነገር ኃላፊነት እንደማይወስዱ ዛሬ ደብዳቤ ማስገባታቸውንም አውቀናል። በክለቡ በኩል በዚህ ጉዳይ ዙርያ መረጃ ለማግኘት ወደ ፕሬዝደንቷን ወ/ሮ እፀገነት ፍቃዱ ለማግኘት ብንሞክርም ለጊዜው ከክለቡ ኋላፊነት መነሳታቸውን እና በሌላ ኃላፊነት ላይ የሚገኙ በመሆናቸው ሰፋ ያለ ማብራሪያ ልናገኝ አልቻልንም። ሥራ አስኪያጁ አቶ ታምራት ታዬ ግን እንደሁልጊዜው ሁሉ ከበላይ አካላት ጋር በመነጋገር ለፋይናንስ ችግሩ መፍትሄ ለመስጠት እየሰሩ መሆናቸውን ነግረውናል።