ቅድመ ዳሰሳ | የነገ ሦስት ጨዋታዎች ዳሰሳ

የ26ኛ ሳምንት የሁለተኛ ቀን ሦስት ጨዋታዎችን የተመለከተው ዳሰሳችን እንደሚከተለው ተሰናድቷል።

ኢትዮጵያ ቡና ከ አዳማ ከተማ

በስድስት ደረጃዎች ተለያይተው 5ኛ እና 11ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት ኢትዮጵያ ቡና እና አዳማ ከተማ ሊጉ ለአህጉራዊ የብሔራዊ ቡድኖች ጨዋታ ከመቋረጡ በፊት ጣፋጭ ድል አስመዝግበው ነበር። ሊጉ መቋረጡ ሁለቱም ከሽንፈት መልስ ያገኙትን የአሸናፊነት መንገድ ያስታቸው ይሆን? የሚለው ጥያቄ ነገ የሚመለስ ሲሆን ቡድኖቹም ከሚከተሉት ማጥቃት የተሞላበት አጨዋወት መነሻነት ጥሩ ፉክክር እንደሚያደርጉ ይጠበቃል።

በባህር ዳር ስታዲየም ካደረጋቸው አራት ጨዋታዎች አንዱን ብቻ የተረታው እና ከሚከተለው ኳስን መሰረት ካደረገ አጨዋወት አንፃር የመጫወቻ ሜዳው የተመቸው የሚመስለው ኢትዮጵያ ቡና ነገም ከኳስ ጋር የሚያሳልፈውን ጊዜ ዘለግ እንደሚል ይገመታል። ለቀሪዎቹ 5 ሳምንታት በጥሩ ሁኔታ ሲሰናዳ የነበረው ቡድኑ ይታይበት የነበረውን ግብ የማስቆጠር ችግር በመጠኑ በመጨረሻዎቹ ጨዋታዎች ቀርፎ የነበረ ቢመስልም አጥጋቢ ግን አይደለም። የነገ ተጋጣሚው አዳማ ከተማ ደግሞ በመከላከሉ ረገድ የተዋጣለት ቡድን ስለሆነ ከጨዋታው አንዳች ነገር ለማግኘት የጎል ፊት መፍትሔዎችን በሚገባ አዘጋጅቶ መቅረብ ይገባዋል። በተቃራኒውም ግቡን የሚያጋልጥበት መንገድ መጠናከር አለበት።

በ25ኛ ሳምንት ከሰበታ ከተማ ጋር ተጫውቶ የነበረው አዳማ ከተማ ከ10 ጨዋታዎች በኋላ ያገኘው ድል ነገም መነሳሳት የሚፈጥርለት ከሆነ ኢትዮጵያ ቡና ሊቸገር ይችላል። ዋና አሠልጣኙ ፋሲል ተካልኝን ካሰናበተ በኋላ በምክትሉ ይታገሱ እንዳለ እየተመራ ከድል ጋር የታረቀው አዳማ በዕለቱ ከ70 ደቂቃዎች በላይ በጎዶሎ ተጫዋቾች ተፋልሞ ድል ማግኘቱ ትልቅ ነገር ነው። ሊጉ ከተቋረጠ ከአንድ ሳምንት በኋላ ዝግጅቱን የጀመረው ቡድኑ ከኳስ ውጪ ያለው ጠበቅ ያለ አደረጃጀት ተጠናክሮ እንደሚመጣ ሲጠበቅ ግብ ፊት ያለው ስልነትም እንደ ቡና መሻሻል ይገባዋል። የሊጉ ሁለተኛው ትንሽ ጎል ያስቆጠረው ስብስብም ፈጣን የመልሶ ማጥቃቶችን እና የቡናን የኳስ ቅብብል ስህተቶች እንደ ግብ ምንጭነት ለመጠቀም መጣሩ የማይቀር እንደሚሆን መገመት ይቻላል።

ምንም የጉዳት ዜና የሌለበት አዳማ ከተማ በቅጣት ምክንያት ወሳኞቹን ተጫዋቾች ዳዋ ሁቴሳ እና ሚሊዮን ሰለሞንን በነገው ጨዋታ አያሰልፍም። ኢትዮጵያ ቡናም ምንም ጉዳት የሌለበት ሲሆን ዊሊያም ሰለሞንን ብቻ በቅጣት የሚያጣ ይሆናል።

የጨዋታው ዳኞች – ዋና ዳኛ በላይ ታደሰ ፣ ረዳቶች ተመስገን ሳሙኤል እና ዘሪሁን ኪዳኔ ፣ አራተኛ ዳኛ ቢኒያም ወርቅአገኘሁ

ተጨማሪ ዳኞች – ትግል ግዛው እና ወጋየሁ አየለ

እርስ በርስ ግንኙነት

– ሁለቱ ቡድኖች 39 ጊዜ ተገናኝተው ኢትዮጵያ ቡና 21 ጊዜ በማሸነፍ የበላይነቱን ይዟል። አዳማ ከተማ በበኩሉ 7 ጊዜ ድል ሲቀናው በ11 ጨዋታዎች ደግሞ ቡድኖቹ አቻ ተለያይተዋል። በሁለቱ የእርስ በርስ ግንኙነት ቡና 68 ፤ አዳማ 34 ጎሎች ማስቆጠር ችለዋል።

ግምታዊ አሰላለፍ


አዳማ ከተማ (4-3-3)

ሴኩምባ ካማራ

ጀሚል ያዕቆብ – ቶማስ ስምረቱ – አዲስ ተስፋዬ – ደስታ ዮሐንስ

አማኑኤል ጎበና – ዮሴፍ ዮሐንስ – ዮናስ ገረመው

አቡበከር ወንድሙ – አብዲሳ ጀማል – አሜ መሐመድ

ኢትዮጵያ ቡና (4-3-3)

በረከት አማረ

ሀይሌ ገብረተንሳይ – አበበ ጥላሁን – ገዛኸኝ ደሳለኝ – አስራት ቱንጆ

አማኑኤል ዮሐንስ – አብነት ደምሴ – ታፈሠ ሰለሞን

አቤል እንዳለ – አቡበከር ናስር – አላዛር ሽመልስ

ወላይታ ድቻ ከ አዲስ አበባ ከተማ

በደረጃ ሰንጠረዡ የላይኛው እና የታችኛው ቦታ ላይ የሚገኙት ድቻ እና አዲስ አበባ በየመንገዳቸው የነገውን ጨዋታ ውጤት አጥብቀው ይፈልጉታል። በተለይ ድል ካደረጉ ዘጠኝ ጨዋታዎች ያለፋቸው ወላይታ ድቻዎች ከበታቾቻቸው የሚገኙት ቡድኖች ደረጃቸውን አለመንጠቃቸውን እያመሰገኑ ወደ አሸናፊነት ለመመለስ እንደሚጥሩ ይታሰባል። አስተዳደራዊ በሆኑ ጉዳዮች ተጫዋቾቹ ልምምድ ያቋረጡበት አዲስ አበባ ከተማም እርግጥ ባይሆንም ከሰባት ተከታታይ የአቻ ውጤቶች በኋላ ለማሸነፍ ወደ ሜዳ እንደሚገቡ ይገመታል።

ከላይ እንደገለፅነው ከድል ጋር ከተራራቀ የሰነባበተው ወላይታ ድቻ የሊጉ መቋረጥ ምናልባት ጥሩ ጠቀሜታ ይዞለት ሊመጣ ይችላል። ከነበረበት የውጤት ድባቴም እንዲወጣ ሊያደርገው እንደሚችል ይገመታል። እንደውም በመጀመሪያው ዙር ውድድር የሰበሰበው ውጤት ጠቀመው እንጂ በደረጃ ሰንጠረዡ ግልባጭ ይገኝ ነበር። በተለይ በመጨረሻዎቹ ዘጠኝ ጨዋታዎች ያስቆጠሩት ሁለት ጎል ምነኛ እየተቸገሩ እንደሆነ የሚያመላክት ነው። በእረፍት ጊዜው ግን ይህን ክፍተት ለመድፈን እንደሚጥሩ ሲጠበቅ ጉዳት ላይ የነበሩት ምንይሉ ወንድሙ እና ቃልኪዳን ዘላለም ለጨዋታው ዝግጁ መሆናቸውም ትልቅ ብርታት የሚሰጣቸው ይሆናል።

ያለፉትን አምስት ቀናት በአስተዳደራዊ ጉዳዮች ተጫዋቾቹ ልምምድ ያልሰሩበት አዲስ አበባ ከተማ ነገ ሜዳ የመግባቱ ጉዳይ የለየለት ባይሆንም ከተጫዋቾች እና አሠልጣኞች እንዲሁም አመራሮች ባገኘነው መረጃ ያለ ልምምድ ጨዋታውን ያደርጋሉ። ይህ ለክለቡ ደጋፊዎች ጥሩ ዜና ቢሆንም ያለ ልምምድ ጨዋታን ማድረጋቸው የሚፈጥረው ተፅዕኖ ግን በመጠኑ የሚያሰጋ ነው። ይህ ቢሆንም ቀድሞ ስምንት ቀን ልምምድ ሰርተው የነበረ ሲሆን ተጫዋቾቹም በግላቸው ሲዘጋጁ እንደነበር በመግለፅ ጨዋታውን ኮስተር ብለው እንደሚቀርቡ አሠልጣኙ ጻውሎስ ጌታቸው ገልፀውልናል። የሆነው ሆኖ ውጤት የማስጠበቅ ስር የሰደደ አባዜ ያለበት ክለቡ ክፍተቱን አሻሽሎ እንደሚገባ የሚጠበቅ ሲሆን ተቀዳሚ ዓላማውም ግቡን ላለማስደፈር በማድረግ በመከላከል ላይ የተመረኮዘ አጨዋወት እንደሚከተል ቀድሞ መናገር ይቻላል።

ወላይታ ድቻ አንተነህ ጉግሳን በቅጣት ምክንያት ሲያጣ አዲስ አበባ ከተማ ደግሞ ሳሙኤል አስፈሪን በጉዳት ምክንያት የማያገኝ ይሆናል።

የጨዋታውን ዳኞች – ዋና ዳኛ አባይነህ ሙላት ፣ ረዳቶች አበራ አብርደው እና ሀብተወልድ ካሳ ፣ አራተኛ ዳኛ ተካልኝ ለማ

ተጨማሪ ዳኞች – ዳንኤል ጥበቡ እና ሙለነህ በዳዳ

እርስ በርስ ግንኙነት

– ሁለቱ ቡድኖች በሊጉ 3 ጊዜ ተገናኝተው የመጀመርያውን አዲስ አበባ ከተማ 1-0 ሲያሸንፍ ሁለተኛውን ያለ ጎል አቻ ተለያይተዋል። ዘንድሮ በመጀመሪያው ዙር ደግሞ ወላይታ ድቻ 2ለ1 አሸንፏል።

ግምታዊ አሰላለፍ


ወላይታ ድቻ (4-3-3)

ቢኒያም ገነቱ

በረከት ወልደዮሐንስ – መልካሙ ቦጋለ – ደጉ ደበበ – አናጋው ባደግ

ሀብታሙ ንጉሴ – ንጋቱ ገብረስላሴ – እንድሪስ ሰዒድ

ምንይሉ ወንድሙ – ስንታየሁ መንግስቱ – ቃልኪዳን ዘላለም

አዲስ አበባ ከተማ (4-3-3)

ዳንኤል ተሾመ

አሰጋኸኝ ጴጥሮስ – ዘሪሁን አንሼቦ – አዩብ በቀታ – ሮቤል ግርማ

ሙሉቀን አዲሱ – ቻርለስ ሩባኑ – ኤሊያስ አህመድ

እንዳለ ከበደ – ሪችሞንድ ኦዶንጎ – ፍፁም ጥላሁን

ድሬዳዋ ከተማ ከ ሀዋሳ ከተማ

በሁለቱ የደረጃ ሰንጠረዥ ግልባጭ ላይ የሚገኙት ድሬዳዋ እና ሀዋሳ የዕለቱ የመጨረሻ መርሐ-ግብር ያከናውናሉ። የወራጅነት ስጋት ያለበት ድሬዳዋ ከተማ በአሠልጣኝ ሳምሶን ስር እየተሻሻለ እንደመጣ እየተመለከትን እንገኛለን። ይህ መሻሻል አጥጋቢ ባይሆንም ከቀጠናው ቀስ እያለ እየሸሸ ይገኛል። ነገም ድል አሳክቶ ነጥቡን ወደ ሠላሳዎች እንደሚያሳድግ ይታመናል። በተቃራኒው ሳይጠበቅ ጨዋታ በጨዋታ እየወረደ የመጣው ሀዋሳ ከተማ ከመጥፎው ጉዞ ሊወጣበት ከቻለ የሊጉ መቋረጥ ይጠቅመዋል። ካለፉት ዘጠኝ ጨዋታዎች አንዱን ብቻ የረታው ቡድኑ ነገ ተሻሽሎ ወደ ሜዳ በመግባት ደረጃውን እንደሚያሻሽል ይታሰባል።

አሁንም የወራጅነት ስጋት ያልተላቀቃቸው ድሬዳዋዎች በቅርብ ጨዋታዎች የሚከተሉት ጥንቃቄ አዘል አጨዋወት በመጠኑ ዋጋ እያስገኘላቸው ይገኛል። በዚህም ግብ የማስተናገድ ችግር ያለበትን የኋላ መስመር ለመሸፈን ከኳስ ውጪ ታታሪ ተጫዋቾችን በመጠቀም ጨዋታዎችን እየቀረቡ ብልጠት የተሞላበት እንቅስቃሴ ሲያደርጉ ይታያል። ግብ ለማስቆጠር ደግሞ ቀጥተኝነት የተሞላበት አጨዋወት በመከተል ግብ ለማግኘት ይሞክራሉ። የነገው ተጋጣሚያቸው የሚመሳሰል አቀራረብ ሊኖረው ስለሚችል ግን መጠነኛ የአጨዋወት ለውጥ ሊያደርጉ ይችላሉ።

በርከት ያሉ የተጫዋች ጉዳት አስተናግደውበት ሲቸገር የነበረው ሀዋሳ ከተማ የሊጉ መቋረጥ ከገባበት መጥፎ ውጤት ብቻ ሳይሆን የሚያወጣው የተጎዱ ተጫዋቾቹንም ይመልስለታል። ይህ ደግሞ ቀደም ብሎ የነበረውን ጠንካራ እንቅስቃሴ እንዲያገኝ ሊረዳው ይችላል። የጠጣር የኋላ መስመር ባለቤት የሆነው ሀዋሳ ከተማ በሊጉ የመጨረሻ ጨዋታዎች ብቻ ሰባት ግቦችን አስገናግዶ ነበር። ይህ የኋላ መስመር ክፍተት ብቻ ሳይሆን ፊት ላይ ያለ ግቦችን የማስቆጠር ችግርም ቡድኑ ጨዋታዎችን እንዲያሸንፍ እንዳደረገው በደንብ ታይቷል። ከነገው ጨዋታ በፊት በመቀመጫ ከተማው 10 ባህር ዳር ደግሞ 2 በአጠቃላይ 12 የልምምድ መርሐ-ግብሮችን ያደረገው ስብስብ የጠቀስናቸውን ክፍተቶቹን አሻሽሎ እንደሚመጣ ይጠበቃል።

የጉዳት እና የቅጣት ዜናን ስንመለከት ሀይቆቹ ፀጋሰው ድማሙ እና ወንድማገኝ ማዕረግን በጉዳት አዲስዓለም ተስፋዬን ደግሞ በቅጣት ምክንያት ከጨዋታው ውጪ አድርገዋል። ብርቱካናማዎቹ በበኩላቸው ፍሬው ጌታሁን እና ሚኪያስ ካሣሁን ጉዳት ላይ ሲሆኑባቸው መሳይ ጻውሎስ እና ሙኸዲን ሙሳ ግን በማገገማቸው ለጨዋታው ዝግጁ ይሆኑላቸዋል ተብሏል።

የጨዋታው ዳኞች – ዋና ዳኛ አዳነ ወርቁ ፣ ረዳቶች ለአለም ዋሲሁን እና ሸዋንግዛው ከበደ ፣ አራተኛ ዳኛ ዳንኤል ግርማይ

ተጨማሪ ዳኞች – ሸዋንግዛው ተባበል እና ትንሳኤ ፈለቀ

እርስ በርስ ግንኙነት

– ሁለቱ ክለቦች እስካሁን በሊጉ 19 ጊዜ ሲገናኙ ሀዋሳ ሰባቱን ድሬዳዋ ደግሞ አምስት ጊዜ ድል አድርገው በቀሪዎቹ ሰባት ጨዋታዎች አቻ ተለያይተዋል። በጨዋታዎቹ ሀይቆቹ 20 ጎሎችን ሲያስመዘግቡ ብርቱካናማዎቹ 18 ጎሎች አሏቸው።

ግምታዊ አሰላለፍ


ድሬዳዋ ከተማ (4-2-3-1)

ደረጄ ዓለሙ

እንየው ካሣሁን – አውዱ ናፊዩ – መሳይ ጳውሎስ – አብዱለጢፍ መሐመድ

ዳንኤል ደምሴ – ብሩክ ቃልቦሬ

አብዱርሀማን ሙባረክ – ሱራፌል ጌታቸው – ጋዲሳ መብራቴ

ሄኖክ አየለ

ሀዋሳ ከተማ (3-4-3)

ዳግም ተፈራ

ካሎንጂ ሞንዲያ -አብዱልባሲጥ ከማል – ላውረንስ ላርቴ

ዳንኤል ደርቤ – ወንድምአገኝ ኃይሉ – በቃሉ ገነነ – መድሃኔ ብርሃኔ

ኤፍሬም አሻሞ – ብሩክ በየነ – መስፍን ታፈሰ