ሪፖርት | ኢትዮጵያ ቡና አዳማን በመርታት ደረጃውን አሻሽሏል

በ26ኛ የጨዋታ ሳምንት ሁለተኛ የጨዋታ ዕለት የመጀመሪያ በነበረው እና አቡበከር ናስር ደምቆ ባረፈደበት ጨዋታ ኢትዮጵያ ቡና አዳማ ከተማን ከኋላ ተነስቶ አሸንፏል።

ጨዋታው ገና በማለዳው ነበር የመጀመሪያውን ግብ ያገኘው ፤ የአዳማው የመሀል ተከላካይ አዲስ ተስፋዬ በረጅሙ ከራሱ የግብ ክልል አቅራቢያ በቀጥታ ወደ ፊት የላከውን ኳስ ከግብ ክልላቸው ርቀው ይከላከሉ ከነበሩት የኢትዮጵያ ቡና ተከላካዮች መካከል አበበ ጥላሁን ኳሱን መቆጣጠር አለመቻሉን ተከትሎ አፈትልኮ የወጣው አሜ መሀመድ ከበረከት አማረ ጋር አንድ ለአንድ የተገናኘበትን አጋጣሚ ተረጋግቶ በማስቆጥር አዳማን መሪ ማድረግ ችሏል።

በተነቃቃ የሜዳ ላይ ፉክክር ጅማሮውን ባደረገው ጨዋታ 7ኛ ደቂቃ ላይ በተመሳሳይ ፀጋአብ ዮሴፍ ከተከለካይ ጀርባ ያደረሰውን ኳስ ተጠቅሞ አብዲሳ ጀማል ግሩም ሙከራ ያደረገ ሲሆን ኢትዮጵያ ቡናዎችም በተመሳሳይ አቡበከር ናስርን አፈተትላኪ ሩጫዎች ተጠቅመው ዕድሎችን ለመፍጠር ጥረት አድርገዋል።

በአጋማሹ በሙከራ ረገድ የተሻሉ የነበሩት ቡናዎች 14ኛው ደቂቃ ላይ በግራ መስመር በኩል በፈጣን ቅብብል ወደ አዳማ ሳጥን ያደረሱትን ኳስ አቤል አንዳለ ሳይጠቀምበት ሲቀር በ25ኛው ደቂቃ ላይ ደግሞ አላዛር ሽመልስ ከቀኝ መስመር ያደረሰውን ግሩም ኳስ አቡበከር ናስር ከሳኩቡ ካማራ ጋር ታግሎ ወደ ውስጥ ያሳለፈውን ታፈሰ ሰለሞን ወደ ግብ ቢሞክርም የአዳማ ተከላካዮች ተረባርበው አድነውበታል።

በአዳማዎች በኩል ምናልባት ሌላው ተጠቃሽ የአጋማሹ ሙከራ በ18ኛው ደቂቃ ላይ ከማዕዘን ምት የተነሳ ኳስ አማኑኤል ጎበና ከሳጥኑ ጠርዝ በቀጥታ የመታው እና ለጥቂት ወደ ውጪ የወጣችበት አጋጣሚ ብቻ ነበረች። የጨዋታው ሂደት በአመዛኙ አዳማ ከተማዎች መሀል ሜዳው ላይ ጠቅጠቅ ብለው የኢትዮጵያ ቡናዎችን ቅብብሎችን በማቋረጥ ሆነ በረጃጅም ኳሶች ደግሞ ከኢትዮጵያ ቡና ተከላካዮች ጀርባ በሚጣሉ ኳሶች ለመጫወት ጥረት ሲያደርጉ ቡናዎች ደግሞ በአቡበከር ናስር አድራጊ ፈጣሪነት በቅብብሎች ዕድሎች ለመፈጠር ሲታትሩ ተመልክተናል።

በሂደት የኢትዮጵያ ቡናዎች የበላይነት እያለበት በመጣበት የመጀመሪያ አጋማሽ ቀሪ ደቂቃዎች የጨዋታው ሂደት ሙሉ ለሙሉ በሚያስብል መልኩ በአዳማ አጋማሽ የተደረገ ነበር ፤ በዚህም ሂደት በርከት ያሉ የግብ አጋጣሚዎችን መፍጠር ቢችሉም አጋጣሚዎቹን ግን ወደ ግብነት መቀየር ሳይችሉ ቀርተዋል። በጨዋታው ግሩም ጥረት ሲያደርግ የነበረው አቡበከር ናስር በሁለት አጋጣሚዎች ከሳጥን ጠርዝ ከቆሙ ኳሶች ያደረጋቸው እና ለጥቂት ወደ ውጭ የወጡበት ሙከራ ጨምሮ በ32ኛው ደቂቃም እንዲሁ አቤል እንዳለ ከግራ መስመር ያሻማውን ኳስ አቡበከር ናስር በግንባሩ ገጭቶ ቢሞክርም ኳሷ በግቡ አግዳሚ ተመልሳበታለች።


እንደ መጀመሪያው ሁሉ ፈጠን ያለ አጀማመር በነበረው የሁለተኛው አጋማሽ በ51ኛው ደቂቃ ላይ አዳማ ከተማዎች ፍፁም ያለቀለት አጋጣሚን በአቡበከር ወንድሙ ካመከኑ በሰከንዶች ልዩነት በተቃራኒው ግብ ደግሞ እንዲሁ ሌላኛው አቡበከር አቡበከር ናስር ያደረገው ሙከራ ሳኩቡ ካማራ አድኖበታል። ከኢትዮጵያ ቡና ተከላካዮች ጀርባ ክፍተቶችን በተሻለ መጠን ማግኘታቸውን የቀጠሉት አዳማ ከተማዎች በ60ኛው ደቂቃ አብዲሳ ጀማል ያሳለፈለትን ኳስ ተጠቅሞ አሜ መሀመድ ከበረከት አማረ ጋር አንድ ለአንድ ያገኘውን አጋጣሚ ከግቡ አናት በላይ ሰዷታል።

አዳማ ከተማዎች ከአጥቂያቸው አብዲሳ ጀማል በስተቀር በቁጥር በርከት ብለው ለመከላከል ጥረት ማድረግ መጀመራቸውን ተከትሎ በ68ኛው ደቂቃ ግን ኢትዮጵያ ቡና አቻ መሆን ችለዋል። አዳማ ከተማዎች ኳስ ተቀባብለው ለመውጣት ጥረት በሚያደርጉበት ወቅት ከዮናስ ገረመው እግር የነጠቀውን ኳስ አላዛር ሽመልስ ራሱ ማስቆጠር እየቻለ ያቀበለውን ቀላል ኳስ አቡበከር በማስቆጠር ቡድኑን አተመልሳበታለች።


አዳማ ከተማዎች አዎንታዊ ለውጦችን በማድረግ በተወሰነ መልኩ ማጥቃታቸውን ለማነቃቃቅ ጥረት ያደረጉ ቢሆንም ጫና ፈጥረው መጫወታቸውን የቀጠሉት ኢትዮጵያ ቡናዎች መሪነቱን በደቂቃዎች ልዩነት ለመረከብ በቅተዋል። 79ኛው ደቂቃ ላይ አስራት ቱንጆ ከግራ መስመር ወደ ሳጥን ውስጥ ያደረሰውን ኳስ አቡበከር ናስር ተቆጣጥሮ በግሩም የግል ክህሎት ሁለት ተጫዋቾች አልፎ ማስቆጠር ችሏል።
በቀሩት ደቂቃዎች ክፍት ሆኖ በቀጠለው ጨዋታ አዳማ ከተማዎች በአንፃራዊነት ኢትዮጵያ ቡናዎች ወደ ራሳቸው ሜዳ እንዲገፉ ማድረግ ቢችሉም የግብ ዕድሎችን ግን መፍጠር የተቸገሩ ሲሆን በአንፃሩ የተሻለ የነበረው አጋጣሚ በሚኪያስ መኮንን አማካኝነት ያገኙት ኢትዮጵያ ቡናዎች አጋጣሚውን መጠቀም ሳይችሉ ቀርተዋል።

ጨዋታው በኢትዮጵያ ቡና የበላይነት መጠናቀቁን ተከትሎ ቡናማዎቹ በ40 ነጥብ ወደ 4ኛ ደረጃ ከፍ ብለው መቀመጥ ሲችሉ አዳማ ከተማዎች ደግሞ በ30 ነጥብ ወደ 11ኛ ደረጃ ተንሸራተዋል።