ሰበታ ከተማ ተጫዋቾቹን ነገ ያገኝ ይሆን?

በ7 ተጫዋቾች ብቻ እስከ ዛሬ ልምምዱን ሲሰራ የነበረው ሰበታ ከተማ ነገ ከፋሲል ከነማ ጋር ጨዋታውን ሊያደርግ ስላሰበበት መንገድ መረጃዎችን ያሰባሰብን ሲሆን በዲሲፕሊን ኮሚቴ ውሳኔ የተወሰነባቸው ተጫዋቾችም ይግባኝ ማለታቸው ታውቋል።

የቤትኪንግ ኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ከብሔራዊ ቡድኖች ጨዋታ እረፍት በኋላ የ26ኛ ሳምንት ጨዋታዎችን ከትናንት ጀምሮ ማድረግ እንደጀመረ ይታወቃል። በደረጃ ሰንጠረዡ አናት እና ግርጌ የሚደረገው ፉክክር አሁንም ሲቀጥል በታችኛው ቀጠና ከሚገኙ ክለቦች መካከል ደግሞ ሰበታ ከተማ ይገኝበታል። የክለቡ ተጫዋቾች “ደሞዝ እና ጥቅማ ጥቅም ካልተሰጠን ወደ ልምምድም ሆነ ውድድር አንሄድም” በማለት አቋማቸውን ገልፀው ለፌዴሬሽኑ ደብዳቤ አስገብተው አንደነበረም ይታወሳል። ትናንት ደግሞ ክለቡ እስከ ሰኔ 15 ድረስ ያለበትን ክፍያ እንዲፈፅም በማሳሰብ የፌዴሬሽኑ የዲሲፕሊን ኮሚቴ ተጫዋቾች ወደ ሥራ ገበታቸው እንዲመለሱ መወሰኑን ዘግበን ነበር። ክለቡም ከውሳኔው በኋላ እስከ ዛሬ 6 ሰዓት ተጫዋቾች የፌዴሬሽኑን ትዕዛዝ አክብረው ሪፖርት እንዲያደርጉ ማስታወቂያ አውጥቶ ነበር።

የዝግጅት ክፍላችን ባጣራቸው መሠረት እስከ ዛሬ ድረስ 7 ሆነው ልምምምድ ሲሰሩ የነበሩትን ተጫዋቾች አመሻሽ ላይ ዱሬሳ ሹቢሳ፣ ፍፁም ገብረማርያም፣ ለዓለም ብርሀኑ እና አብዱልሀፊዝ ቶፊቅ እንደተቀላቀሉ አውቀናል። ቀሪዎቹ 14 ተጫዋቾች ደግሞ ነገ ከጨዋታው በፊት ረፋድ ላይ ከያሉበት ወደ ባህር ዳር እንደሚጓዙ ተረድተናል። ከላይ ስማቸውን ከጠቀስናቸው ተጫዋቾች መካከል ፍፁም እና አብዱልሀፊዝ ቀድመው ወደ ስፍራው ያመሩት የኮቪድ-19 ምርመራ ለማድረግ እንደሆነ እና ሌሎቹ ክትባት ስለወሰዱ በምርመራው መገኘት ስለማይጠበቅባቸው ለጨዋታው ብቻ ለመድረስ አስበው የጉዞ ቀጠሯቸውን ነገ እንዳደረጉ ሰምተናል። ስለዚህ ክለቡ እስከ ትናንት በ6 ዛሬ ደግሞ በ7 ተጫዋቾች ልምምድ ቢያሰራም ነገ 10 ሰዓት ከፋሲል ከነማ ጋር በሚያደርገው ጨዋታ ሁሉንም ተጫዋቾች እንደሚያገኝ አውቀናል።

በተያያዘ ዜና በትናንትናው ዕለት ወደ ስራ ገበታችሁ ተመለሱ ተብለው በፌዴሬሽኑ የፍትህ አካል ውሳኔ የተወሰነባቸው ተጫዋቾች ውሳኔውን አክብረው በአንዳንድ ጉዳዮች ላይ ይግባኝ ማለታቸውን ገልፀውልናል።

በመጀመሪያ በውሳኔው ላይ የተጠቀሱትንና የ2013 ደመወዝ መጠየቃቸው አግባብ አይደለም የተባሉ ተጫዋቾችን ውል አያይዘው ክለቡ ለተጫዋቾቹ በውል መሰረት የመክፈል ግዴታው እንደሆነ በመግለፅ ከ2-4 ወር ደመወዝ ክለቡ እንዲከፍል እና የፍትህ አካሉ ውሳኔውን በድጋሜ እንዲመለከት ጠይቀዋል። ሁለተኛ ደግሞ የዱሬሳ ሹቢሳ ውል የሚጀምረው ከሀምሌ 1 መሆኑ እንዲታወቅ በመግለፅ ክለቡ ያቀረበው ማስረጃ ፍፁም ከእውነት የራቀ ነው በማለት ውሳኔውን እንዲጤን አቤት በለዋል። አያይዘውም ፌዴሬሽኑ በተቀመጠው ቀነ ገደብ መሰረት ክለቡ ደሞዛቸውን እንዲከፍል እንዲያደርግ አደራ ብለው ካልሆነ ግን ጉዳዩን ወደ ካፍ እና ፊፋ እንደሚወስዱት ጠቁመዋል።