የአሰልጣኞች አስተያየት | ድሬዳዋ ከተማ 1-3 ሀዋሳ ከተማ

ሀዋሳ ከተማ ሦስት ነጥብ ከድሬዳዋ ላይ ከወሰደበት ጨዋታ መጠናቀቅ በኋላ አሰልጣኞች አስተያየት ሰጥተዋል፡፡

አሰልጣኝ ዘርዓይ ሙሉ – ሀዋሳ ከተማ

ስለ ድሉ

“አንዳንዴ ውጤት ስታጣ ሌላ ሀሳብ ውስጥ ነው የምትገባው፡፡ ቡድኔ ዛሬ ለመጫወት ያሰብነው አንደኛ እነርሱ ወሳኝ ነጥብ ነው የሚፈልጉት ምክንያቱም ከእዛ አካባቢ ለመራቅ ዛሬ ያላቸው አማራጭ ማሸነፍ እንደሆነ ስላሰብን ብዙ ቦታዎችን እንደሚለቁም ጠብቀን መጫወት ነበር ያሰብነው ተሳክቶልናል፡፡ ሁለተኛ ከሽንፈትም ስለመጣን ጠብቆ መጫወቱ አድቫንቴጅ ነው ቢያንስ ጎልን ጠብቆ መጫወት ያዋጣል፡፡ ሦስተኛ ደግሞ ይሄ ሜዳ በጣም አቅም የሚፈልግ ፣ ጉልበት የሚጠይቅ ስለሆነ ሌላ ሜዳ ላይ እንደምትጫወተው የምትጫወት ከሆነ በአንድ እና በሁለት ስህተት ጎል ይቆጠርብሀል፡፡ ስለዚህ እነዚህን ታሳቢ ያደረገ ዝግጅት ነበር ሁለቱን ሳምንት ስንሰራ የነበረው ይሄንን ሜዳ ላይ ለማየት ሞክረናል፡፡ የሳትናቸውም ቢቆጠሩ ከዚህም በላይ ማግባት ይቻል ነበር፡፡ መጫወቻ የማይጠቅም ቦታ ሰጥተናቸዋል እንዲጫወቱ ፣ ግን ወደ አደገኛው ክልል ሲመጡ ተቆጣጥረን በእነርሱ ሜዳ ላይ ለመጫወት ያሰብነው ተሳክቶልናል፡፡

ስለ ኤፍሬም አሻሞ

“የመስፍን መውጣት አሰላለፍ ካወጣን በኋላ ነው የወጣው፡፡ የእርሱ መውጣት ቢያንስ ሁለት ሰው ቀይረናል፡፡ ኤፍሬሞ ከመስመር ነበር ይነሳ የነበረው አንድ ተከላካይ ይወጣል ፣ አንድ የተከላካይ አማካይ ነበር የሚገባው የሁለት ሰው ለውጥ ነው ያደረግነው የመስፍን ብቻ ሳይሆን ዞሮ ዞሮ አንዳንዴ ይከሰታል፡፡ ኤፍሬምም ደግሞ መጀመሪያ ከሚነሳበት ቦታ ወደ ፊት ተጠግቶ ስለተጫወተ ዛሬ ለጎል የሚሆን ኳሶች እና ጎል ራሱም አስቆጥሯል፡፡ ዛሬ ውጤታማ ነበር ብዬ ነው የማስበው፡፡

ሁለት ጎል ስላስቆጠረው ብሩክ በየነ

“ምንም ጥርጥር የለውም ማንም መናገር ይችላል፡፡ ሁለተኛው አቡበከር ነው ማለት ይቻላል፡፡ ምክንያቱም የግል ኳሊቲው ቦክስ ውስጥ ካገኘ ፖዚሽኑ ሁሉ ነገር የተሰጠው አጥቂ ነው፡፡ ትልቅ ቦታ ይደርሳል ብዬ ነው የማስበው፡፡”

አሰልጣኝ ሳምሶን አየለ – ድሬዳዋ ከተማ

ስለ ሽንፈቱ

“ብዙ ረጃጅም ኳሶች ከእኛ ከመስመር ጥቃቶች ይሄዱ ነበር፡፡ እነርሱ ያንን የአየር ኳስ ለመቆጣጠር ችግር አልነበረባቸውም ፣ በቀላሉ ለመቆጣጠር ይችሉ ነበር፡፡ ከእዛ ውጪ ተከላካይ አካባቢ ያለው መዘናጋት የአማካዩንም የአጥቂውንም እንቅስቃሴ እንዲገታው አድርጎታል፡፡ ሁለተኛው አርባ አምስት ላይ ኳሶች በተቻለ መሬት የያዙ ሆነው እንዲሄዱ ሞክረን ነበር፡፡ ወደ ጎል በመጠጋት በጣም ብዙ አልነበረንም፡፡ ግን የምናገኘውን ኳስ በአግባቡ ያለ መጠቀም እና የግብ ዕድል ያለ መፍጠር ችግር ትልቁ ነበር፡፡

የመከላከል ክፍተት የቡድን ወይንስ የተናጠል ?

“ሁለቱም ናቸው፡፡ በጣም ይታዩ የነበሩት፡፡ የተናጥልም ችግር ነበር የባላጋራን አጥቂ ያለ መቆጣጠር ችግር ቦታ ያለ መሸፈን ጀርባን ያለ መጠበቅ ችግሮች በጣም ነበር፡፡ ከኳስ ውጪ ያለውን ክፍት ቦታ ያለ መቆጣጠር ፣ እነዚህ ቡድናችን በሚፈልገው ልክ ነጥቡን ሳያስጠብቅ እንዲወጣ ምክንያቶች ነበሩ፡፡

ለአጥቂው ሄኖክ አየለ በቂ ኳስ ያለ መድረሱ

“ለማረም የሞከርነውም ይሄንን ነው፡፡ ሁለተኛው አርባ አምስት ላይ በጣም ይታይ የነበረውን በመጀመሪያው አርባ አምስት ኳሶች በሥርአት ወደ አጥቂዎች የሚያቀርብ ሰው ስላልነበረ እነዛን ከግራ እና ከቀኝ የሚነሱ ፉልባኮችን ለመጠቀም ጥረት ተደርጓል፡፡ ብሩክ ከገባ በኋላ የተሻለ አቅርቦት ነበር፡፡ በዚህም አጋጣሚ አንድ ጎል አግኝተን በሦስት ለባዶ ከመሸነፍ አንድ ጎል ይዘን እንድንወጣ ረድቶናል፡፡

ስለ ቀጣይ አራት ጨዋታዎች የቡድኑ ተስፋ

“አራት ጨዋታ ማለት አስራ ሁለት ነጥብ ስለዚህ ያንን አሳክተን ወደ ምንፈልገው ነገር መምጣታችን የማይቀር ነው፡፡”