ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 26ኛ ሳምንት ዓበይት ጉዳዮች (፫) – አሰልጣኞች ትኩረት

በጨዋታ ሳምንቱ በተመለከትናቸው ጨዋታዎች ላይ የታዩ ትኩረት የሳቡ አሰልጣኝ ነክ ጉዳዮች እንደሚከተለው ቀርበዋል።
👉 ዮሐንስ ሳህሌ ወደ ሜዳ ተመልሰዋል

ባለፉት አምስት ጨዋታዎች በጤና እክል ምክንያት ልምምድ ከማሰራት ባለፈ በጨዋታ ወቅት ቡድናቸውን መምራት ሳይችሉ የቆዩት አሰልጣኝ ዮሐንስ ሳህሌ በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት ግን ዳግም ወደ ሜዳ ተመልሰዋል።

ስለአሰልጣኙ ቀጣይነት ብዙ መላምቶች ሲሰጡ ቢቆይም ሊጉ ከዕረፍት ሲመለስ ግን በአዲስ መንፈስ ወደ መንበራቸው ተመልሰው ተመልክተናል። በተመለሱበትም ጨዋታ ቡድናቸው በብዙ ረገድ የተሻለ የነበረ ቢሆንም ከጨዋታው ግን ሙሉ ሦስት ነጥብ ይዘው መውጣት ሳይችሉ ቀርተዋል።

አሰልጣኙ በህመም ምክንያት ከቡድኑ በራቁበት ወቅት በዋነኝነት ይነሳ የነበረው ጉዳይ ቡድኑ በሚታይ ደረጃ እንደ ድክመት ይነሳበት የነበረው የማጥቃት አፈፃፀም ላይ ያሳየውን ፍፁም የተሻለ መነቃቃትን እንደነበር አይዘነገም። ታድያ ቡድኑ በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት ምንም እንኳን ከወልቂጤ ከተማ ጋር ያለ ግብ በአቻ ውጤት ቢለያይም በጨዋታው የተሻሉ የግብ ዕድሎችን ሲፈጥር ተመልክተናል።

ወደ ሊጉ ባደጉበት ዓመት መከላከያን በሊጉ የማቆየት ተቀዳሚ ግብን የሰነቁት አሰልጣኙ ይህን ግብ ለማሳካት አሁንም ከቀጣይ አራት ጨዋታዎች ተፈላጊውን ነጥብ የመሰብሰብ ኃላፊነት ይጠብቃቸዋል።

👉 የተለወጠ አርባምንጭ ከተማ

የአሰልጣኝ መሳይ ተፈሪ ቡድኖች በሊጉ የራሳቸው መገለጫ አላቸው ብለን ከምንጠራቸው ጥቂት ቡድኖች መካከል ተጠቃሽ ናቸው። ታድያ በመጨረሻዎቹ ጨዋታዎች ላይ ግን ከአቀራረብ ጋር በተያያዘ የተወሰኑ ለውጦች እንደሚኖሩ አሰልጣኙ ጠቁመዋል።

ዘንድሮው በሊጉ የተመለከትነው አርባምንጭ ከተማ እንኳን ይበልጥ ቀጥተኛ ማጥቃቶችን ምርጫው ያደረገ እንዲሁም በአንዳንድ ጨዋታዎች ደግሞ ከሜዳው ከፍ ብሎ ተጋጣሚን ጫና ውስጥ በመክተት ለመጫወት የሚፈልግ እንደነበር ስናስተውል ቆይተናል። ነገር ግን ካለፉት ጥቂት ጨዋታዎች አንስቶ ግን ቡድኑ በተወሰነ መልኩ በጨዋታዎች ላይ ያለው የኳስ ቁጥጥር ድርሻ ለማሳደግ እና ኳሱን በመቆጣጠር ጨዋታውን የመቆጣጠር ጥረቶችን እያደረገ እንደሚገኝ እያስተዋልን እንገኛለን።

ሲዳማ ቡናን ከረቱበት ጨዋታ መጠናቀቅ በኋላ አሰልጣኙ በሰጡት አስተያየት ፤ “ከሌላው ጊዜ ያደገ የኳስ ቁጥጥሮች ይኖራሉ ፤ ጠብቁ። አንዱ መከላከል ኳስን ለባለ ጋራ አለመስጠት ነው። ስለዚህ እነዚህን ነገሮች በቀጣይ ጊዜያት እናሳድጋለን።” የሚልን ሀሳብ ሰጥተዋል።

ታድያ ምናልባት ከዚህ ቀደም ለምናስበው ከፍተኛ ታታሪነትን ለሚጠይቀው የመሳይ ተፈሪ ተመራጭ አጨዋወት የተመለመሉት ተጫዋቾች ከአዲሱ የጨዋታ ሀሳብ ጋር በምን መልኩ ይጣጣማሉ የሚለው ጉዳይ ይጠበቃል።

👉 ፈተናዎችን እንደ ዕድል – ይታገሱ እንዳለ

ከጥቂት ሳምንታት በፊት አዳማ ከተማን የተረከበው አሰልጣኝ ይታገሱ እንዳለ በተወሰነ መልኩ የቡድኑን መንፈስ ለመለወጥ ስራዎችን እየሰራ እንደሚገኝ እየተመለከትን እንገኛለን።

በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት ቡድኑ ኢትዮጵያ ቡናን ሲገጥም የቡድኑ ቁልፍ ተጫዋቾች የነበሩትን አጥቂውን ዳዋ ሆቴሳ እና ሚልዮን ሰለሞንን በተለያዩ ምክንያቶች ሳይዙ ባደረጉት ጨዋታ ምንም እንኳን ሽንፈት ቢያስተናግዱም አሰልጣኙ ከጨዋታው መጀመር ሆነ መጠናቀቅ በኋላ የሰጣቸው አስተያየቶች ከግለሰቦች ይልቅ በቡድን ላይ ስላለው የፀና ዕምነት የሚያሳዩ ነበሩ።

ከጨዋታው መጀመር አስቀድሞ ስለሁለቱ ተጫዋቾች አለመኖር ሲያብራራ ተጫዋቾቹ የቡድኑ ቁልፍ ተጫዋቾች መሆናቸውን አስረድቶ አለመኖራቸው ግን በጨዋታው ላይ በሚያሳዩት እንቅስቃሴም ሆነ ውጤት ላይ በምክንያትነት መቀረብ እንደማይችል በአፅንኦት ሲናገር ያደመጥን ሲሆን የእነሱን አለመኖር ለመጠቀም ራሳቸውን አዘጋጅተው የሚጠበቁ ሌሎች ብቁ የሆኑ ተጫዋቾችም ስለመኖራቸው ሀሳቡን ሰጥቷል።

ምንም እንኳን በማጥቃቱ ቡድኑ ያመከናቸው ኳሶች የዳዋን መኖር የሚያስመኙ እንዲሁም በአንዳንድ አጋጣሚዎች ደግሞ በመከላከሉ ወቅት የነበሩ ሂደቶች ሚሊዮን ሰለሞንን እንድናስብ የሚያስገድዱ የሚመስሉ ቢሆኑም አሰልጣኙ ግን ይህ ያሳሰበው አይመስልም። ይልቁኑ ያልነበሩትን ከማሰብ ይልቅ ስለነበረው ነገር መናገርን መርጧል።

በየትኛውም ሁኔታ ራስን ነፃ ማውጣት እና ሁኔታዎችን እንደ ሰበብ የመደርደር የብልጣብልጥነት እሳቤ ተጠናውቶት በነበረው እግርኳሷችን አዳዲስ እየመጡ የሚገኙት ወጣት አሰልጣኞች ግን ይህን አሳቤ እየሰበሩ ይገኛሉ። የይታገሱ እንዳለም ሀሳብ የዚህ ማሳያ ተደርጎ ይወሰዳል።