ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 26ኛ ሳምንት ዓበይት ጉዳዮች (፬) – ሌሎች ጉዳዮች

የመጨረሻው ፅሁፋችን ደግሞ በጨዋታ ሳምንቱ ሌሎች የታዘብናቸው ጉዳዮች ላይ ትኩረት ያደረገ ይሆናል።

👉 ሊጉ ተመልሷል

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በ2023 በአይቬሪኮስት አስተናጋጅነት ለሚደረገው የአፍሪካ ዋንጫ በምድብ አራት ለነበሩበት ሁለት ጨዋታዎች ከ20 ለሚልቁ ቀናት ተቋርጦ የነበረው ሊጉ ዳግም በዚህኛው ሳምንት ጅማሮውን አድርጓል።

ታድያ ሊጉ ከዕረፍት ሲመለስ በሰንጠረዡ ሁለት ፅንፎች አስገራሚ ውጤቶች የተመዘገቡበት ሲሆን ይህም ሊጉ በቀጣይ ሳምንታት ይበልጥ አጓጊ ሆኖ እንዲቀጥል የሚያደርግ ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል።

የመጨረሻ ውጤት በሚወስነው የመጨረሻ ምዕራፍ (Run In) ላይ የሚገኘው ሊጉ እስከ ያዝነው ወር መገባደጃ ላይ የሚደረጉ አራት የጨዋታ ሳምንታት አሸናፊውን እና ወራጅ ቡድኖችን ጨምሮ ሁለተኛው የአፍሪካ መድረክ ተሳታፊ ቡድን ይለያሉ ተብሎ በጉጉት ይጠበቃሉ።

ከዚህም ባለፈ አሁን ላይ በሰንጠረዡ በክለቦች መካከል ካለው የነጥብ መቀራረብ አንፃር በአንድ ጨዋታ ማሸነፍ እና መሸነፍ ከሚኖረው መለዋወጥ አንፃር ሊጉ በቀጣይ ከሚመዘገቡ ውጤቶች መነሻነት በሰንጠረዡ ላይ የሚኖሩ መለዋወጦችም እንዲሁ አጓጊ ሆነዋል።

👉 ጉዳት ያስተናገዱት የህክምና ባለሙያ

በጨዋታ ሳምንቱ ወላይታ ድቻን ከአዲስ አበባ ከተማ ያገናኘው እና ብዙዓየሁ ሰይፈ በተጨማሪ ደቂቃ ባስቆጠራት ግብ ድራማዊ አጨራረስን ያስመለከተን ጨዋታ ሌላም እንግዳ አጋጣሚን ያስመለከተን ነበር።

መደበኛው የጨዋታ ክፍል ተጠናቆ በተጨመሩት አራት ደቂቃዎች ውስጥ አዲስ አበባ ከተማዎች መሪ የሆኑበትን ግብ ካገኙ በኋላ በተፈጠረ አንድ ቅፅበት ጉዳት ያስተናገደውን የአዲስ አበባ ከተማው ግብ ጠባቂ ዳንኤል ተሾመን የህክምና እርዳታ ለማድረግ ወደ ሜዳ እየገሰገሱ የነበሩት የአዲስ አበባ ከተማ የህክምና ባለሙያ የሆኑት አቶ አደም መሀመድ ሜዳውን አቋርጠው ወደ ግብ ጠባቂው እየሮጡበት በነበረ ቅፅበት በድንገት መሀል ሜዳውን አለፍ እንዳሉ ሚዛናቸውን መጠበቅ ሳይችሉ በመቅረታቸው ለመውደቅ ተገደዋል።

ለህክምና እርዳታ የተላኩት እኚሁ ግለሰብ እንዳለመታደል ሆኖ ራሳቸውን ለህክምና የዳረገ አጋጣሚ በመፈጠሩ በዚህም የህክምና እርዳታ ተደርጎላቸው ከሜዳ በቃሬዛ ለመውጣት ተገደዋል። ባለሙያው ከጨዋታው ማግስት ዕረፍት እንደተሰጣቸው እና አሁን በመልካም ጤንነት ላይ እንደሚገኙ ለማወቅ ችለናል።

👉 ዓይነ ግቡ የሳር አጨዳ

ሊጉ ከዕረፍት ሲመለስ ከሰሞኑ ውድድሩን ሲያስተናግድ የነበረው የባህር ዳር ስታዲየም የመጫወቻ ሳርም እንዲሁ ከውድድሩ መቋረጥ የተጠቀመ መስሏል።

ወቅቱ ዝናብ መጣል የሚጀምርበት እንደመሆኑም የመጫወቻ ሜዳው ይበልጥ ባማረ አረንጓዴያማ ገፅታ የተመለሰ ሲሆን ይህን ተከትሎም የሳር አጨዳውም ቢሆን ለሜዳው የተለየ ገፅታ አላብሶታል።

በሀገራችም እምብዛም ባልተለመደ መልኩ በሁለት አይነት መልኩ (Pattern) የታጨደው ሳሩ ለሜዳው በዕይታ ረገድ ካላበሰው ማራኪ ገፅታ ባለፈ ለመስመር ዳኞች በተለይ ከጨዋታ ውጭ የሆኑ እንቅስቃሴዎችን በመለየት ረገድ ከሚኖረው አበርክቶ አንፃር በዚህ ወሳኝ ምዕራፍ ጥሩ አበርክቶ ይኖረዋል ተብሎ ይጠበቃል።

ከዚህ ባለፈ ባህር ዳር እየተመለከትነው የምንገኘው የሜዳ እንክብካቤ ከእኛ ሀገር ንባራዊ ሁኔታ አንፃር ፍፁም ሊበረታታ የሚገባ ሲሆን ሌሎች ስታዲየሞችም ይህን እንደ መነሻ በመውሰድ ለመጫወቻ ሜዳዎች እንክብካቤ ትኩረት ሊሰጡ ይገባል።

👉 ሊጉ በሠላም እንዴት ይጠናቀቅ ?

ሊጉ ሊጠናቀቅ የመጨረሻ አራት ጨዋታዎች ብቻ ይቀራሉ። እነዚሁ ጨዋታዎች የቡድኖችን ዕጣ ፈንታ በመወሰን ረገድ ትልቅ ዋጋ ያላቸው ጨዋታዎች ከመሆናቸው ጋር ተያይዞ ከፍተኛ ጥንቃቄ ይሻሉ።

በቀደሙት ዓመታት የመጨረሻ ጥቂት መርሐግብሮች ላይ ጨዋታዎች በሜዳ ላይ ከሚደረጉ ፉክክሮች ባለፈ በጠረጴዛ ዙርያ በሚደረጉ ድርድሮች የጨዋታ ውጤቶች ይወሰናሉ የሚሉ እና ሌሎችም እግርኳሳዊ ያልሆኑ አመክኔዎች ለውጤቶች መለወጥ እንደ ምክንያት ሲቀርቡ መስማት የተለመደ ነው።

አሁንም ምንም እንኳን ውድድሩ ፍፁም በተሻለ አስተዳደር እንደመመራቱ እና የቴሌቪዥን ስርጭት እንደመኖሩ ከላይ የጠቀስናቸው ነገር የመከሰታቸው ዕድል የጠበበ ቢመስልም አሁንም ቢሆን ያማረ ፍፃሜ እንዲኖር የሁሉምንም ጥረት ይጠበቃል። በመሆኑም አሁንም አጠቃላይ በሰንጠረዡ ላይ ካለው የክለቦች የነጥብ መቀራረብ አንፃር ሁሉም ጨዋታዎች እጅግ ከፍ ያለ ዋጋ ያላቸው እንደመሆናቸው ጥንቃቄ ሊደርግባቸው ይገባል።

በዚህ ሂደት ውስጥ ከአወዳዳሪው አካል አንስቶ ሁሉም ባለድርሻ አካላት የሚጠበቅባቸውን ብቻ ሳይሆን ከሚጠበቅባቸው በላይ ኃላፊነታቸውን መውጣት ካልቻሉ ግን “እንዲሁም ዘንቦብሽ” በሆነው እና በሴራ ትንተና እና በመጠላለፎች በተተበተበው እግርኳሳችን ውስጥ ሌላ መጥፎ ታሪክ ጥሎ እንዳያልፍ ከወዲሁ የሴራ ንድፈ ሀሳቦች አየሩን ሳያጨናንቁት ርብርቦች መደረግ ይኖርባቸዋል።