የአሠልጣኞች አስተያየት | ድሬዳዋ ከተማ 0-3 አርባምንጭ ከተማ

አዞዎቹ ከብርቱካናማዎቹ ሦስት ነጥብ እና ሦስት ጎል ካገኙበት ጨዋታ በኋላ ተከታዩ የድህረ-ጨዋታ አስተያየት ከአሠልጣኞቹ ተደምጧል።

መሳይ ተፈሪ – አርባምንጭ ከተማ

ቡድኑ ተከታታይ ሁለት ጨዋታዎች ስለማሸነፉ…?

መጀመሪያ ፈጣሪዬ እግዚአብሔርን ማመስገን እፈልጋለው። የተወሰኑ ጨዋታዎችን ባለፈው ተሸንፈን ነበር። ቀድሜ እንደተናገርኩትን የተደገፍነው አለት ላይ ነበር። የቆምንበትን መሰረት ነበር ያየነው። ሰርተናል። ከ5 ጨዋታዎች 3ቱን አሸንፈናል። እርግጥ ለሌሎቹም ጨዋታዎች ተዘጋጅተናል። ደረጃችን በቀጣይም እየተሻሻለ ይመጣል ብዬ አስባለው። መልካም ነበር።

ስለኤሪክ ካፓይቶ ብቃት…?

ወደ መጨረሻ አካባቢ ወደ ጥሩ ብቃት እየመጣ ነው። ሲከላከልም ጥሩ ነው። የጎል አጋጣሚዎችንም ለመፍጠር ጠንካራ ነገር አለው። በአጠቃላይ ከእርሱ ጋር የሚሄድ ነገር ለመስራት ተነጋግረን እነዛን ለውጦች ነው እያየን ያለነው።

ቡድኑ ግብ ካገኘ በኋላ ለማስጠበቅ ስለሚያደርገው እንቅስቃሴ…?

ከሀዲያው ጨዋታ ትምህርት የወሰድነው ነገር አለ። ጥንቃቄ እየወሰድን ነው ለማጥቃት ስንሞክት የነበረው። ብዙ ትምህርቶችን ወስደናል።

ሳምሶን አየለ – ድሬዳዋ ከተማ

ስለጨዋታው…?

ከባድ ነው። አርባምንጭ ከቆሙ ኳሶች እንደሚጠቀም ይታወቃል። እዚህ ላይ ተዘጋጅተንም ሰርተንም ነበር የመጣነው። ነገርግን በተግባር ሜዳ ላይ እየታየ የነበረው ነገር ይሄንን የሚገልፅ አልነበረም። እንደሰጋነው ሦስቱም ጎሎች የቆሙ ኳሶች ናቸው። በኳስ ቁጥጥር እና ወደ ጎል ተጠግቶ በመጫወት ረገድ የእኛ ቡድን የተሻለ ነው። ነገርግን ያንን መቆጣጠር ሳንችል ጎሎች ተቆጥረዋል። አስቸጋሪ ነው። ከፊት ያሉትን ጨዋታዎች እስከመጨረሻው እንጫወታለን።

ስለቡድኑ ድክመት…?

የተከላካይ ችግር ነው። የአቋቋም እና እንደ ቡድን ተናቦ የመጫወት ችግር አለ። ከእረፍት በፊት በነበረው ዙር ላይ ቡድኑ ላይ በእጅጉ ይታይበት የነበረው የተከላካይ የመቀናጀት ችግር ነበር። እርሱን ቀርፈናል የሚል ነገር ነበር። በተጨባጭም ባለፉት 6 እና 7 ጨዋታዎች የታየው ይሄ ነበር። አሁን ግን ይሄንን የሚገልፅ አይደለም። እንፈትሻለን። በቀረን ጊዜ እያስተካከልን እንሄዳለን።

ስለአጥቂ መስመሩ…?

አቅርቦቱ ነው። ፊት ላይ ያሉት ያለ ኳስ ያላቸው እንቅስቃሴ ደካማ ነው። ክፍት ቦታ የመግባት እና ያገኙትን የመጠቀም ችግር አሉ። ዒላማውን የጠበቀ ሙከራ አንዱ ጋርም አይታይም። ዞሮ ዞሮ ቡድኑ ራሱን በደንብ ፈትሾ በቀሪ ጨዋታዎች ለመቅረብ ይሞክራል።

ስለቀጣይ ጨዋታዎች እና ስለመውረድ ስጋት….?

አሁን እንዲህ ነው ብለን መደምደም አንችልም። ዛሬ ሦስት ነጥብ ደምረን ቢሆን ኖሮ ወደ ተሻለ ደረጃ እንሄድ ነበር። ግን እዛው ነው ያለነው። ከወራጅ ቀጠናው በአንድ ነጥብ ነው የወጣነው። ግን ያገኘነውን አጋጣሚ በአግባቢ ያለመጠቀም ችግር አንዱ የቡድኑ ችግር ነው በዋናነት ያለው ችግር ከስነልቦና አንፃር ነው። እርሱን እንፈትሻለን።

ስላለመውረድ ጭንቀት…?

ሀላፊነቱ ከባድ ነው። የእኔ ደግሞ ከማናቸውም ትንሽ ይለያል። ግማሽ ላይ ነው የገባሁት፣ ቡድኑ በሁሉም መልኩ የውጤት ቀውስ ውስጥ ነበር፣ የትኩረት እና በርካታ ችግሮች ነበሩበት። ያንን አስተካክለን መተናል። ለውጦች ነበሩት። ከብሔራዊ ቡድን እረፍት በኋላ ግን ወደ መጀመሪያው ነው እየተመለስን ያለነው። መሀል ላይ ወደነበርንበት ቁመና ለመመለስ በቀሪዎቹ ሦስት ጨዋታዎች ጠንክረን እንሰራለን። እግር ኳስ ነው እና የሚፈጠረው አይታወቅም።