ሪፖርት | አዞዎቹ ሁለተኛ ተከታታይ ድላቸውን አሳክተዋል

በምሳ ሰዓቱ ጨዋታ ያገኟቸውን ጥቂት ዕድሎች ወደ ግብነት መቀየር የቻሉት አዞዎቹ የብርቱካናማዎቹ በሊጉ የመቆየት ህልም ላይ ትልቅ እክል የሚፈጥር ድል አስመዝግበዋል።

በአሰልጣኝ ሳምሶን አየለ በኩል በሀዋሳ ከተማ ከተረታው ስብስባቸው ከግማሽ በላይ ለውጥ ያደረጉ ሲሆን በዚህም ደረጀ ዓለሙ ፣ ከድር ኸይረዲን ፣ አቤል አሰበ ፣ አብዱረህማን ሙባረክ ፣ ሳሙኤል ዘሪሁን እና ጋዲሳ መብራቴ ወጥተው በምትካቸው ፍሬው ጌታሁን ፣ መሳይ ጳውሎስ ፣ ሱራፌል ጌታቸው ፣ ብሩክ ቃልቦሬ ፣ ማማዱ ሲዲቤ እና አቤል ከበደ የመጀመሪያ ተመራጭ ሆነዋል። በአንፃሩ አሰልጣኝ መሳይ ተፈሪ ደግሞ ሲዳማ ቡናን ከረታው ስብስብ ምንም ለውጥ ሳያደርጉ ጨዋታቸውን አከናውነዋል።

በጨዋታው የተሻለ የኳስ ቁጥጥር ድርሻ በመያዝ የጀመሩት ድሬዳዋ ከተማዎች ፈጠን ባሉ ቅብብሎች ወደ አርባምንጭ ከተማ ሳጥን በመድረስ ያደርጉ የነበረው ጥረት አበረታች ነበር። ነገር ግን በጨዋታው ቀዝቀዝ ያለ አጀማመርን ያደረጉት አርባምንጭ ከተማዎች ሳይጠበቁ በ14ኛው ደቂቃ መሪ መሆን ችለዋል። ወደ ቀኝ ካደላ አቋቋም አርባምንጭ ከተማዎች ያገኙትን የቅጣት ምት ኳስ እንዳልካቸው መስፍን በግሩም ሁኔታ ያሻማውን ጊዜውን የጠበቀ ኳስን አህመድ ሁሴን በግንባሩ በመግጨት ቡድኑን ቀዳሚ አድርጓል።

ከግቧ መቆጠር በኋላ በተመሳሳይ የጨዋታ መንገድ ለመቀጠል ጥረት ያደረጉት ድሬዎች ኳሶችን ወደ መስመር በማውጣት ከመስመር መነሻቸውን ባደረጉ ኳሶች ጥቃት ለመሰንጠር ጥረት አድርገዋል። በዚህም በ30ኛው ደቂቃ አቤል ከበደ ከቀኝ የሳጥን ጠርዝ ወደ ውስጥ ያሻማው ኳስ በአርባምንጭ ከተማው ግብ ጠባቂ ይስሀቅ ተገኝ ሲመለስ ሳጥን ውስጥ ያገኘውን ኳስ ማማዱ ሲዲቤ አስቆጠረ ተብሎ ሲጠበቅ አጋጣሚዋን ሳይጠቀም ቀርቷል። በአንፃሩ መሀል ሜዳ ላይ በቁጥር በዝተው ኳሶችን የመንጠቅ ፍላጎት የነበራቸው አርባምንጭ ከተማዎች በአንዳንድ አጋጣሚዎች በተለይ ለአህመድ ሁሴን በሚጣሉ ተሻጋሪ ኳሶች አደጋ ለመፍጠር ጥረት ያደርጉ ሲሆን በአጋማሹም ከኳስ ውጪ የነበራቸው አደረጃጀትም ጥሩ የሚባል ነበር።

በአጋማሹ በብዙ መመዘኛዎች ሁለተኛ የነበሩት አርባምንጮች 44ኛው ደቂቃ ላይ ደግሞ አጋማሹን 2-0 እየመሩ የፈፀሙበትን ግብ አግኝተዋል። ከማዕዘን ምት የተሻማን ኳስ የድሬዳዋ ከተማ ተጫዋቾች ለመከላከል ባደረጉት ጥረት ውስጥ ዳንኤል ደምሴ በርናርድ ኦቼንግ ላይ በሰራው ጥፋት አርባምንጮች ያገኙትን የፍፁም ቅጣት ምት ኳስ ኤሪክ ካፓይቶ ማስአምክኖባቸዋል።

በሁለተኛው አጋማሽ ጅማሮ አርባምንጮች በመጀመሪያው አጋማሽ መጠነኛ ጉዳት ያስተናገደውን አህመድ ሁሴንን በአሸናፊ ኤልያስ ተከትተው የቀረቡ ሲሆን በአንፃሩ ግብ ያስፈልጋቸው የነበሩት ድሬዳዋ ከተማዎች ደግሞ በተመሳሳይ ስብስብ የጀመሩበት ነበር። በሁለተኛው አጋማሽ ገና ከጅምሩ የአቻነት ግብ ማሰስ የጀመሩት ድሬዳዋ ከተማዎች በተለይም በ56ኛው ደቂቃ ላይ ማማዱ ሲዲቢ ከቅጣት ምት ያደረገውን ድንቅ ሙከራ ይስሀቅ ተገኝ ያዳነበት እንዲሁም በ60ኛው ደቂቃ አቤል ከበደ ከቀኝ የሳጥን ጠርዝ ሰብሮ ያደረገውን ሙከራ በተመሳሳይ ይስሀቅ አምክኖባቸዋል።

በጨዋታው አመዛኙን የጨዋታ ክፍለ ጊዜ በአርባምንጭ አጋማሽ ላይ እንዲደረግ ማስገደድ የቻሉት ድሬዳዋ ከተማዎች ተለዋዋጭ የሆነ የማጥቃት ሀሳብ እጥረት እንደበረባቸው የተመለከትን ሲሆን በዚህም የነበራቸውን ብልጫ ወደ ግብ ዕድልነት በመቀየር ረገድ ፍፁም ደካማ ነበሩ። በጨዋታው በተመሳሳይ አድበተው የድሬዳዋ ከተማን ስህተት ሲጠባበቁ የነበሩት አርባምንጮች በ78ኛው ደቂቃም እንዲሁ በድሬዳዋ ተጫዋቾች ስህተት ላይ ተጨማሪ ግብ አግኝተዋል። መሳይ ጳውሎስ ኤሪክ ካፓይቶ ላይ በሰራው ጥፋት አርባምንጮች ያገኙትን የፍፁም ቅጣት ምት ራሱ ካፓይቶ በማስቆጠር የቡድኑን አሸናፊነት አረጋግጧል።

ውጤቱን ተከትሎ ሁለተኛ ተከታታይ ድላቸውን ያሳኩት አርባምንጭ ከተማዎች በ37 ነጥብ በነበሩበት 7ኛ ደረጃ ሲቀጥሉ በአንፃሩ በሁለት ተከታታይ ጨዋታዎች የተሸነፉት ድሬዳዋ ከተማዎች ደግሞ ለጊዜውም ቢሆን በ29 ነጥብ 13ኛ ላይ ይገኛሉ።