የአሰልጣኞች አስተያየት | ኢትዮጵያ ቡና 1-1 አዲስ አበባ ከተማ

ሁለቱ የመዲናይቱ ክለቦች ነጥብ ከተጋሩበት ጨዋታ በኋላ አሰልጣኞች አስተያየት ሰጥተዋል፡፡

አሰልጣኝ ካሣዬ አራጌ – ኢትዮጵያ ቡና

ሰለ ጨዋታው…?

“ጨዋታውን በምንፈልገው መጠን መቆጣጠር አልቻልንም፡፡ እነርሱ ካለባቸው ውጥረት አንፃር ጫና ፈጥረው ሊጫወቱ እንደሚችሉ ገምተናል ፤ ያም ሆኖ ጨዋታውን መቆጣጠር የምንችልበት ዕድል ነበር። ብልጭ ድርግም የሚል አይነት ነገር ነበረው፡፡ አንዳንዴ ጥሩ ይሄዳል የኳሱ ፍሰት አንዳንዴ ደግሞ ይቋረጥ ነበር፡፡ እኛ ሜዳ ላይ መጥተው በጣም በጥንቃቄ ነበር የሚጠብቁን። በምንፈልገው ልክ ጨዋታውን ተቆጣጥረናል ብዬ አላስብም፡፡

የወራጅነት ስጋት ያለባቸው ክለቦች ደጋፊዎች በስታዲየም መገኘት ስለ ፈጠረው ተፅእኖ…?

“እኛ መጀመሪያም የተነጋገርነው ነገር ነበር፡፡ እኛ ለቡድናችን ክብር ነው የምንጫወተው። በዛ ውስጥ በሚፈጠረው ነገር የነጥብ ልዩነት በክለቦች ላይ ሊፈጥር ይችላል። በእኛም ላይ ሊፈጥር ይችላል። እኛ ትኩረት የምናደርገው የሌላ ቡድን ደጋፊዎች ኖሩም አልኖሩም ለክለባችን ክብር ነው የምንጫወተው። ያንን ብዙም ታዛቢ አላደረግንም፡፡

የአቡበከር ናስር የመጨረሻ ጨዋታዎች እና እሱን ለመተካት ስለሚደረጉ ሂደት…?

“ለእኔ ግልፅ የሆነ ነገር የለም፡፡ እስከ አሁን ድረስ ግልፅ የሆነ ከክለቡ ጋር በምን አይነት መልኩ ነው የሚሄደው፣ እስከ ስንት ጨዋታ ድረስ እኛ ጋር ይቆያል ስለሚለው የማውቀው ነገር ስለሌለ ምንም ማለት አልችልም፡፡

አሰልጣኝ ጳውሎስ ጌታቸው – አዲስ አበባ ከተማ

ስለ ጨዋታው…?

“ጨወታው ማለቅ ያለበት ከዕረፍት በፊት ነበር ፤ ብዙ ኳሶች ስተናል፡፡ እንዳያችሁት አጥቅተን ነው የተጫወትነው፡፡ ወራጅ ቀጠና ውስጥም ያለ ቡድን አይመስልም፡፡ በጣም በጣም ደስተኛ ነኝ። ዘጠና ደቂቃው ለእኔ ጥሩ ነው፡፡

ስለተሰጠባቸው የፍፁም ቅጣት ምት…?

“እኔ አሁን ምንም መናገር አልፈልግም፡፡ ይሄ የራሱ አካል አለው። እሱ ይመልከተውና የራሱን አስተያየት ይስጥበት፡፡ በአጠቃላይ ያለው ግን በእኔ ለቀጣይ ከቡድኑ ጋር የተቀናጀ ነገር እሰራለሁ፣ ለሚቀጥለው ምን አደርጋለሁ፣ ምን ሰርቼ ቡድኔን አተርፋለሁ የሚለው ላይ ባተኩር ይሻለኛል፡፡

ተጨማሪ ጎል ያለስቆጠሩበት ምክንያቱ…?

“ከዕረፍት በፊት የነበሩትን ኳሶች መጠቀም ብንችል ኖሮ ከዕረፍት በኋላ ብዙ ኳሰ ይዘን የመጫወቱ ነገር ነበረን፡፡ ከእረፍት በኋላ ግን የተሰጠው ፍፁም ቅጣት ምት ተጫዋቾቼ ላይ ትንሽ የመውረድ ነገር አሳይቷል፡፡ ከዛ ደግሞ እንደገና አገግመን መጨረሻ ላይ መሀመድ በረኛውን አልፎ ንክኪ አለው ብዬ ገምታለው በእኔ ዕይታ። ሁሉ ነገር አልተሳካም አንድ ነጥብ አግኝተናል ከጨዋታው ተመስገን ነው፡፡

የወራጅነት ስጋት እና ጫናው እንቅልፍ ያሳጣል ስለመባሉ…?

“ለምንድነው እንቅልፍ የማጣው፡፡ በታሪክ እንቅልፍ የሚያሳጣኝ የለም፡፡ ገምቶ የመጣ ሰው እንቅልፍ ሊያጣ ይችላል፡፡ እኔ በመሀል መጥቻለሁ። ይሄን ቡድን አቀናጅቼ በፕሪምየር ሊጉ እዛው እንዲቆይ ለማድረግ ነው። እንደውም ዘና ብዬ የእንቅልፍ ሰዓቴን ጨምሪያለሁ፡፡