አቡበከር ናስር ለአርባምንጩ ጨዋታ ይደርሳል

አቡበከር ናስር ወደ ደቡብ አፍሪካ በሚያደርገው ጉዞ ዙርያ በተሰረው ዘገባ ላይ የተደረገ ማስተካከያ…

ከሰኔ 24 ጀምሮ የደቡብ አፍሪካው ማሜሎዲ ሰንዳውንስ ንብረት የሚሆነው አቡበከር ናስር የዝውውር ሂደቱን ለማጠናቀቅ ትናንት ማምሻውን ወደ አዲስ አበባ እንደሄደ እና ዛሬ ወደ ደቡብ አፍሪካ እንደሚጓዝ መዘገባችን ይታወሳል።

ሆኖም ግን አቡበከር አሁን ባደረሰን መረጃ መሰረት ወደ አዲስ አበባ የተመለሰው አንዳንድ የጉዞው ሁኔታዎችን ለማስተካከል እንደሆነ እና ወደ ደቡብ አፍሪካ የሚያደርገው ጉዞ ያልተጠናቀቀ በመሆኑ ሐሙስ ወደ ባህር ዳር በመመለስ በ28ኛው ሳምንት ኢትዮጵያ ቡና ከአርባምንጭ ከተማ ጋር በሚኖረው ጨዋታ ላይ እንደሚሰለፍ ገልፆልናል።

ሰኔ 20 አካባቢ ወደ ደቡብ አፍሪካ እንደሚጓዝ የሚጠበቀው አበቡበከር በማስከተል በ29ኛው ሳምንት ኢትዮጵያ ቡና ከአፄዎቹ በሚያደርጉት ጨዋታ ወደ ደቡብ አፍሪካ የሚያደርገው ጉዞው የሚቃረብበት ቀን ከመሆኑ አንፃር የመጫወቱ ነገር አጠራጣሪ ሲሆን ከሰኔ 24 ጀምሮ ሙሉ ለሙሉ ንብረትነቱ ማሜሎዲ ሰንዳውንስ በመሆኑ የሊጉ የመጨረሻ ጨዋታ ኢትዮጵያ ቡና ከባህር ዳር ከተማ ጋር በሚያደርገው ሲያደርግ እንደማይኖር ተረጋግጧል።

ወደ ደቡብ አፍሪካ ከተጓዘ በኋላ አቡበከር ክለቡን ማሜሎዲ ሰንዳውንስ ጋር በመቀላቀል እዛው የሚቆይ ይሆናል። ቀደም ሲል ከአቡበከር ናስር ጉዞ ጋር በተያያዘ ባጋራነው መረጃ ላይ ለተፈጠረው ስህተት ይቅርታ እንጠይቃለን።