ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 27ኛ ሳምንት ዓበይት ጉዳዮች (፩) – ክለብ ትኩረት

የመጀመሪያ ፅሁፋችን የሚሆነው በጨዋታ ሳምንቱ የተመለከትናቸው ትኩረት የሳቡ ክለብ ነክ ጉዳዮች ናቸው።

👉 የቅዱስ ጊዮርጊስ ወደ አሸናፊነት መመለስ እና የፋሲል ከነማ የድል ግስጋሴ መቀጠል

ቅዱስ ጊዮርጊስ እና ፋሲል ከነማ በዚህኛው ሳምንት ድል ማድረጋቸው ተከትሎ ፉክክሩ አሁንም እስከ መጨረሻው የማሸነፊያ ክር ድረስ የመቀጠሉ ነገር እርግጥ እየሆነ መጥቷል።

በ25ኛ የጨዋታ ሳምንት በውድድር ዘመኑ ለመጀመሪያ ጊዜ ሽንፈት ያስተናገዱት ቅዱስ ጊዮርጊሶች ሊጉ ዳግም በተመለሰበት የ26ኛ ሳምንት መርሃግብር ደግሞ ከባህር ዳር ከተማ ጋር አቻ መለያየታቸውን ተከትሎ ‘ቡድኑ በመጨረሻው ሰዓት እየተንሸራተተ ይሆን ?’ የሚል ስጋት በብዙሃኑ ዘንድ ሲሰነዘር ብናደምጥም በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት ወሳኝ ሦስት ነጥብን ከወልቂጤ ከተማ በመውሰድ የአጋጣሚዎች ጉዳይ እንጂ ለመጨረሻው ፍልሚያ አሁንም ዝግጁ የሆነ ቡድን መሆኑን አስመስክሯል።

በሁለተኛው ዙር እንዳደረጓቸው አብዛኞቹ ጨዋታዎች ሁሉ ጊዮርጊስ ወልቂጤ ከተማን በገጠመበት ጨዋታ በሁለቱ አጋማሾች የተለያየ መልክ የነበረው ሲሆን በዚህም በመጀመሪያው አጋማሽ በተሻለ መልኩ ኳሱን ተቆጣጥረው በተለይ ወደ ቀኝ መስመር ባደላ መልኩ ተደጋጋሚ ጥቃቶችን ሲሰነዝሩ የተመለከትን ሲሆን በሁለተኛው አጋማሽ ግን በወልቂጤ ከተማዎች ከፍ ያለ ጫና ውስጥ ወድቆ ተመልክተናል።

በከነዓን ማርክነህ እና ጋቶች ፖኖም ግቦች በፈረሰኞቹ አሸናፊነት መጠናቀቁን ተከትሎ ከሁለት ተከታታይ ነጥብ መጣሎች በኋላ ቅዱስ ጊዮርጊስ ወደ አሸናፊነት የተመለሰ ሲሆን ሌላው በጨዋታው ከውጤቱ ባሻገር ለቡድኑ አውንታዊ ዜና የሚሆነው እስማኤል ኦሮ-አጎሮ ከ12 ጨዋታዎች በኋላ ዳግም ወደ ሜዳ የመመለሱ ጉዳይ ነው። በጨዋታው የመጨረሻዎቹ ጥቂት ደቂቃዎች ከነዓን ማርክነህን ተክቶ በመግባት የጨዋታ ዝግጁነቱን ለመመለስ የሚረዱ ውጤታማ ጊዜያትን ያሳለፈው ተጫዋቹ በዚህም በአንድ አጋጣሚ ከመስመር የተሻገረለትን ኳስ በግንባሩ በመግጨት ግሩም ሙከራ ማድረግ ችሏል። በተቃራኒው ግን ከሰሞኑ ሌላው ከጉዳት የተመለሰው አቤል ያለው በወልቂጤው ጨዋታ በመጀመሪያ አጋማሽ ጉዳት አስተናግዶ በዳግማዊ አርዓያ ተቀይሮ የመውጣቱ ነገር እንደ መጥፎ ዜና የሚወሰድ ነው።

ከ2009 ወዲህ ዳግም ወደ ሊጉ ክብር እየተንደረደሩ የሚገኙት ቅዱስ ጊዮርጊሶች 15ኛውን ክብር ለመቀዳጀት 270 ያህል ደቂቃዎች ብቻ ቀርቷቸዋል። በቀጣይ ከሀዲያ ሆሳዕና ፣ አርባምንጭ ከተማ እና አዲስ አበባ ከተማ ጋር ጨዋታዎች የሚጠብቁት ቡድኑ እነዚህን ጨዋታዎች የሚያሸንፍ ከሆነ ማንም ሳይጠብቅ ከአምስት ዓመታት በኋላ ወደ ሊጉ አሸናፊነት የሚመለስ ይሆናል።

በአንፃሩ ከመሪው ቅዱስ ጊዮርጊስ በሦሰት ነጥብ አንሰው የተቀመጡት ፋሲል ከነማዎች በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት በህብረት ለመከላከል ከፍተኛ ጥረት ሲያደርጉ ከነበሩት አዳማ ከተማዎች ጠንከር ያለ ፉክክር ቢገጥማቸውም በሁለተኛው አጋማሽ ባገኟቸው ግቦች አሁንም በፉክክር ውስጥ መቀጣቸውን አረጋግጠዋል።

በተለይም በመጀመሪያ አጋማሽ አዳማ ከተማዎች በጠንካራ መከላከል መላው ፋሲላዊያኑን ጭንቀት ውስጥ ጥለው ቢቆዩም በሁለቱኛው አጋማሽ ግን የሙጂብ ቃሲም ሁለት ድንቅ አጨራረሶች ከጨዋታው ሙሉ ሦስት ነጥብ ይዘው እንዲወጡ አስችሏቸዋል።

አሁንም ቢሆን ወደ ዋንጫው ለማምራት የፈረሰኞቹን ነጥብ መጣል የሚጠባበቁት ፋሲሎች መሪው ላይ ጫናቸውን ማሳደር የቀጠሉ ሲሆን መሪው ነጥብ የሚጥልበት ዕድል ካለ አጋጣሚውን ለመጠቀም ተዘጋጅተው በመጠባበቅ ላይ ይገኛሉ። ለዚህም ምስክር የሚሆነው አስደናቂ ወቅታዊ የማሸነፍ ግስጋሴ ላይ የመሆናቸው ነገር ነው። በዚህም ዐፄዎቹ ስምንተኛ ተከታታይ ድላቸው ላይ የደረሱ ሲሆን በእነዚህ ጨዋታዎች 12 ግቦችን አስቆጥረው ሁለት ጊዜ ብቻ ነው መረባቸው የተደፈረው። ይህን መሰሉ የሊግ አጨራረስ መንገድ ላይ መገኘት የራሳቸውን የቤት ሥራ ለመወጣት መተማመኛ እንደሚሆናቸውም ይታመናል። ፋሲል ከነማ በቀሪ ሦስት የሊጉ ጨዋታዎች ከሀዋሳ ከተማ ፣ ኢትዮጵያ ቡና እና ድሬዳዋ ከተማ ጋር ይገናኛል።

👉 አደገኛ መንገድ ላይ የሚገኘው ባህር ዳር ከተማ

ከውድድሩ መጀመር አስቀድሞ ለአህጉራዊ ውድድሮች ታጭቶ የነበረው ባህር ዳር ከተማ አሁን ላይ ግን በቀጣይ ዓመት በሊጉ ስለመቆየቱም እንኳን ዋስትና በሌለበት እጅግ አደገኛ ስፍራ ላይ ይገኛል።

ውድድሩ ወደ ባህር ዳር ከማምራቱ አስቀድሞ በነበሩት የጨዋታ ሳምንታት ቡድኑ ከነበረበት የውጤት አልባ ጉዞ አንፃር በብዙዎች ዘንድ ባህር ዳር በሜዳው እና በደጋፊዎቹ ዘንድ በሚያደርጋቸው ቀሪዎቹ የሊግ ጨዋታዎች ውጤቱን ያቃናል ተብሎ ቢጠበቅም በሊጉ በሜዳቸው እንደተጫወቱ ሌሎች ቡድኖች ሁሉ በሜዳው በመጫወቱ ይገኘዋል የተባለው ዕድል እስካሁን መጠቀም ሳይችል ቀርቷል።

ሊጉ ወደ ባህር ዳር ካቀናበት የ22ኛ የጨዋታ ሳምንት አንስቶ ቡድኑ በሜዳው እና በደጋፊው ፊት ካደረጋቸው ስድስት ጨዋታዎች ማግኘት ከሚገባው 18 ነጥቦች ውስጥ ማሳካት የቻለው 5 (28%) ብቻ መሆኑ ከሜዳ ተጠቃሚነትም ባለፈ በሊጉ ለመቆየት በሚደረገው ትግል ውስጥ ይበልጥ እንዲዘፈቅ አድርጎታል።

ባህር ዳር በተከታታይ ጨዋታ የተስፋ እና የስጋት ስሜቶች እየተፈራረቁበት ይገኛል። በ24ኛ የጨዋታ ሳምንት ድንቅ ከነበረ የሜዳ ላይ እንቅስቃሴ ጋር አዳማን የረታው ቡድኑ በቀጣይ የጨዋታ ሳምንት ግን ሳይጠበቅ በሲዳማ ቡና የተሸነፈ ሲሆን ባሳለፍነው የጨዋታ ሳምንት ደግሞ ሳይጠበቅ መሪው ቅዱስ ጊዮርጊስን ፈትነው አቻ መለያየታቸውን ተከትሎ በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት ይህን ሂደት ያስቀጥላሉ ተብለው ቢጠበቁም በሀዋሳ ከተማ ሽንፈትን ለማስተናገድ ተገደዋል።

በመጨረሻ ሦስት የሊግ ጨዋታዎች ከድሬዳዋ ከተማ ፣ ሰበታ ከተማ እና ኢትዮጵያ ቡና ጋር ጨዋታዎች የሚጠብቋቸው ባህር ዳር ከተማዎች አሁን ካሉበት እጅግ አደገኛ ስፍራ ለማምለጥ የደጋፊዎቻቸውን አውንታዊ ድጋፍ እና የተጫዋቾችን ያላቸውን ሙሉ መስጠትን ይጠብቃሉ።

👉 ድሬዳዋ ከተማ አጣብቂኝ ውስጥ ገብቷል

ወደ ፕሪሚየር ሊጉ ዳግም ከተመለሱ ወዲህ ሁሌም ቢሆን በሊጉ ለመትረፍ በመጨረሻዎቹ ሳምንታት ሲፍጨረጨሩ የምናውቃቸው ድሬዳዋ ከተማዎች ሦስት ጨዋታ በቀረው የዘንድሮ ውድድርም በለመዱት ስፍራ እየዳከሩ ይገኛሉ።

ለምስራቁ የኢትዮጵያ ክፍል ብቸኛ የፕሪሚየር ሊጉ ተወካይ የሆነው ድሬዳዋ ከብዙ ክለቦች በተሻለ የፋይናንስም ሆነ አስተዳደራዊ ሁኔታዎች ውስጥ ቢገኝም በየዓመቱ በተመሳሳይ አዙሪት ውስጥ የመገኘቱ ጉዳይ አሁንም እንቆቅልሽ ሆኖ የቀጠለ ሲሆን ዘንድሮም ላለፉት ጥቂት ሳምንታት በ29 ነጥብ 13ኛ ደረጃ ላይ ቢሰነብቱም በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት ግን አዲስ አበባ ነጥብ መጋራቱን ተከትሎ ወደ ወራጅ ቀጠና ውስጥ ገብተዋል።

ዘንድሮም የአሰልጣኝ ለውጥ ካደረገ ወዲህ በተወሰነ መልኩ መሻሻሎችን አሳይቶ የነበረው ቡድን አሁን ላይ ግን እጅግ አደገኛ የውጤት አልባ ጉዞ ላይ ይገኛል። በመጨረሻዎቹ ሁለት የሊግ ጨዋታዎች በድምሩ ስድስት ግቦችን አስተናግደው ሽንፈት ማስተናገዳቸውን ተከትሎ በዚህ ወሳኝ ሰዓት ከእነዚህ ሽንፈቶች እንዴት ያገግማሉ የሚለው ጉዳይ ይጠበቃል።

እርግጥ ከውጤት ባሻገር በሁለቱ ጨዋታዎች በሀዋሳ በተሸነፈበት ጨዋታ በመጀመሪያው አጋማሽ ከተወሰደበት ብልጫ ባለፈ በሦስቱ የጨዋታ አጋማሾች የተሻሉ ነገሮችን ለማድረግ ሲጥር ታይቷል። በዚህ ከእንቅስቃሴዎች በላይ ውጤቶች ትልቅ ዋጋ ባላቸው የመጨረሻው የሊግ ምዕራፍ ላይ በፍጥነት ውጤቶችን ወደ ማስመዝገብ መመለስ ካልቻሉ ግን እጅግ አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ራሳቸውን ማግኘታቸው አይቀሬ ነው።

ተጋጣሚዎቹ ላይ የተሻለ የኳስ ቁጥጥር ለመውሰድ የሚሞክረው ቡድኑ ኳሶችን አደጋ ወደ ሚፈጥሩ ቀጠናዎች በማስገባትም ሆነ ተደጋጋሚ የግብ ዕድሎችን በመፍጠር ረገድ ውስንነቶች ያሉበት ሲሆን በመከላከሉ ወቅትም መዋቅራዊ እና እጅግ አደገኛ የሆኑ ግለሰባዊ ስህተቶችን መቀነስ ይኖርበታል።

በቀሪዎቹ ሦስት የጨዋታ ሳምንታት በቀጥታ ላለመውረድ እየተፎካከሩት ከሚገኙት ባህር ዳር ከተማ እና አዳማ ከተማ ጋር የሚያደርጋቸው “የስድስት ነጥብ ዋጋ” ያላቸው ሁለት ጨዋታዎችን ጨምሮ ቡድኑ በመጨረሻው የጨዋታ ሳምንት ደግሞ ለሊጉ ክብር እየተፋለመ ከሚገኘው ፋሲል ከነማ ጋር እጅግ ጠንካራ ጨዋታ የሚጠብቀው መሆኑ ነገሮችን ይበልጥ የሚያከብዱበት ይመስላል። በመሆኑም ድሬዳዋ ከተማውዎች ዘንድሮስ እነዚህን ፈተናዎች በስኬት ተወጥተው በሊጉ ለተጨማሪ ዓመት መቆየታቸውን ያረጋግጡ ይሆን የሚለው ጉዳይ ያጓጓል።

👉 ከትልቁ ዕድል በትንሹ የተጠቀሙት አዲስ አበባዎች

14ኛ ደረጃ ላይ ተሰፍተው የሰነበቱት አዲስ አበባ ከተማዎች በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት ግን ነጥባቸውን ወደ 29 በማሳደግ በግብ ልዩነትም ቢሆን ወደ 13ኛ ደረጃ ከፍ ብለዋል።

በሰንጠረዡ ከወገብ በታች ከሚገኙት ቡድኖች መካከል ሀዲያ ሆሳዕና ፣ መከላከያ እና ሰበታ ከተማ ብቻ ነጥብ ሲጋሩ የተቀሩት ቡድኖች ደግሞ ሽንፈት ማስተናገዳቸውን ተከትሎ በጨዋታ ሳምንቱ የማሳረጊያ በነበረው መርሃግብር ኢትዮጵያ ቡናን የገጠሙት አዲስ አበባ ከተማዎች ከዚህ ጨዋታ ሙሉ ሦስት ነጥብ ይዘው መውጣት ከቻሉ ነጥባቸውን ወደ 31 እንዲሁም ደረጃቸውን ደግሞ እስከ 10ኛ ማሳደግ የሚችሉበትን ዕድልን ይዘው ያደረጉት ጨዋታ ነበር።

በጨዋታው የተሻለ ጥረትን በሁለቱም አጋማሾች በማድረግ ኢትዮጵያ ቡናን መፈተን የቻሉት አዲስ አበባ ከተማዎች እንደተለመደው በመጀመሪያው አጋማሽ ያገኙትን መሪነት ማስጠበቅ ሳይችሉ ከኢትዮጵያ ቡና ጋር ነጥብ ተጋርተው መውጣት ተገደዋል። ይህም ምንም እንኳን ድሬዳዋ ከተማን በግብ ልዩነት በልጠው 13ኛ ደረጃ ላይ በ29 ነጥብ እንዲቀመጡ ቢያስችላቸውም በዙሪያቸው የሚገኙ ክለቦች ነጥብ መጣላቸውን ተከትሎ ከወራጅነት ስጋት በተወሰነ መልኩ ራቅ ሊሉበት የሚችሉትን ውጤት ማስመዝገብ ሳይችሉ እንዲቀሩ አድርጓል።

በመጨረሻዎቹ ሦስት ጨዋታዎች ሰበታ ከተማ ፣ ሲዳማ ቡና እና ቅዱስ ጊዮርጊስን የሚገጥሙት አዲስ አበባ ከተማዎች ከተቀናቃኛቸው ድሬዳዋ ከተማ አንፃር የተሻለ የግብ ልዩነት ላይ መገኘታቸው ለቀጣይ ጨዋታዎች የተሻለ ስንቅ ይሆናቸዋል ተብሎ ይጠበቃል።

👉 ድንቅ ጉዞ ላይ የሚገኙት አዞዎቹ

አርባምንጭ ከተማ በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት ድሬዳዋ ከተማን ማሸነፋቸውን ተከትሎ በዘንድሮው የውድድር ዘመን ለመጀመሪያ ጊዜ በሁለት ተከታታይ ጨዋታዎች ድል ማስመዝገብ ችለዋል።

አሰልጣኝ መሳይ ተፈሪ ምንም እንኳን በኳስ ቁጥጥር ረገድ ያደገ ቡድን በመጨረሻዎቹ ሳምንታት ጠብቁ ቢሉም በመጨረሻዎቹ ሁለት ጨዋታዎች ቡድኑ በዚህ ረገድ የሚታይ መሻሻሎችን ለማሳየት የተቸገረ ሲሆን በማጥቃቱ ረገድ ግን ያላቸው አፈፃፀም እምርታን አሳይቷል።

በመጨረሻው የድሬዳዋ ጨዋታ እንኳን በጨዋታ እንቅስቃሴ ተበልጠው የቆዩት አርባምንጭ ከተማዎች ምንም እንኳን ሁለት ግቦችን በፍፁም ቅጣት ምት ቢያገኙም በጨዋታው በጥቂት አጋጣሚዎች በመልሶ ማጥቃት ወደ ድሬዳዋ ሳጥን በተጠጉባቸው ቅፅበቶች በጣም አደገኛ እንደነበሩ ማስተዋል እንችላለን።

በሁለት ተከታታይ ጨዋታዎች ድል ማድረጋቸውን ተከትሎ በሰንጠረዡ ሽቅብ በመጓዝ ላይ የሚገኙት አርባምንጭ ከተማዎች አሁን ላይ በ37 ነጥቦች 7ኛ ደረጃ ላይ የሚገኙ ሲሆን በዚህ አካሄዳቸው የሚቀጥሉ ከሆነ በ2013 የውድድር ዘመን ወጣ ገባ ከነበረ የውድድር ዘመን በኋላ በመጨረሻ ጨዋታዎች በማንሰራራት በሊጉ 5ኛ ደረጃን ይዞ ያጠናቀቀውን የሰበታ ከተማን ታሪክ ለመድገም የሚያልሙ ይመስላል።

👉 ጓዙ የተሸከፈው ሰበታ ከተማ

ሊጠናቀቅ የሦስት ጨዋታዎች ዕድሜ በቀረው የሊግ ውድድር ሰበታ ከተማ ከሊጉ መውረዱ የተረጋገጠው የመጀመሪያ ቡድን ለመሆን ተቃርቧል።

ከሜዳ ውጭ ባሉ ሁነቶች የተወጠረው ሰበታ በትልቅ ደረጃ በመወዳደር ላይ ከሚገኝ አንድ ቡድን በማይጠበቅ መልኩ በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ እንደ ቡድን በጣት በሚቆጠሩ አጋጣሚዎች ብቻ ልምምዶችን ከውነው ጨዋታዎችን እያደረጉ የሚገኙ ቢሆንም በእንቅስቃሴ ረገድ ግን ሜዳ ላይ መጥፎ ቡድን ሆነው አልተመለከትንም። ነገር ግን አሁንም ቢሆን በሊጉ የመቆየት ተስፋቸውን የሚያለመልም ሦስት ነጥብ ግን መጨመር አየቻሉ አይገኙም።

ከሀዲያ ሆሳዕና ጋር ያለ ግብ አቻ መለያየታቸውን ተከትሎ በ21 ነጥቦች በሊጉ ግርጌ የሚገኙት ሰበታ ከተማዎች ከቀሪዎቹ 3 ጨዋታዎች ሙሉ ሦስት ነጥብ ቢያሳኩ እንኳን አጠቃላይ የነጥብ ድምራቸው የሚደርሰው 30 ነጥብ ላይ ነው። ይህም አሁን ድረስ በሂሳባዊ ስሌት ቡድኑን በሊጉ የሚያቆይ ቢመስልም ከቀጣይ ጨዋታዎች በአንዱ ቡድኑ ነጥብ የሚጥል ከሆነ ግን በሊጉ የመቆየት እና የሚሳካ የማይመስለው ህልማቸው ሙሉ ለሙሉ የሚያበቃለት ይሆናል