ሪፖርት | ሰበታ እና ሀዲያ ሆሳዕና ሳይሸናነፉ ቀርተዋል

የዕለቱ ሁለተኛ ጨዋታ በሰበታ ከተማ እና ሀዲያ ሆሳዕና መካከል ተደረጎ 0-0 ተጠናቋል።

ሰበታ ከተማ ከፋሲሉ ሽንፈት አብዱልሀፊስ ቶፊቅ ፣ ሀምዛ አብዱልመን እና ቢስማርክ አፒያን አሳርፎ በኃይሉ ግርማ ፣ ዴሪክ ኒሲባምቢ እና ፍፁም ገብረማሪያምን ተጠቅሟል። በሀዲያ ሆሳዕና በኩል በጅማ ሲሸነፉ ከተጠቀሙበት አሰላለፍ ዑመድ ዑኩሪ እና ሀብታሙ ታደሰ ወጥተው ሄኖክ አርፌጮ እና ተስፋዬ አለባቸው ተተክተዋል።

በቡድኖቹ ጥሩ የማጥቃት ተነሳሽነት እየተንፀባረቀበት በጀመረው ጨዋታ በመጀመሪያዎቹ 10 ደቂቃዎች ሀዲያ ሆሳዕናዎች በፍቅረየሱስ ተወልደብርሀን እና ሚካኤል ጆርጅ አማካይነት ከሳጥን ውስጥ ኢላማቸውን የጠበቁ ሙከራዎች አድርገዋል። በተለይም ሚካኤል ከባዬ ገዛኸኝ ተቀብሎ ወደ ግብ የላከው ኳስ የተሻለ ጠንከር ያለ ነበር። ከእነዚህ ሙከራዎች መነሻነት ወደ ኋላ ሳብ ብለው በታዩት ሰበታዎች በኩል ዴሪክ ንስባምቢ 10ኛው ደቂቃ ላይ ከሳጥን ውጪ ሞክሮት ወደ ውጪ የወጣው ኳስ ነበር በሙከራነት የታየው።

ሰበታ ከተማዎች ቀስ በቀስ በተሻለ ሁኔታ ኳስ በማንሸራሸር ከሜዳቸው መውጣት ሲጀምሩ በአንፃሩ ሀዲያ ሆሳዕናዎች ወደ ቀኝ መስመር ባመዘነ ፈጠን ያለ የማጥቃት ሂደትን ተከትለው ታይተዋል። ሰበታዎች ከኳስ ንክኪዎቻቸው ይልቅ 20ኛው ደቂቃ ላይ ከተለመደው የሙከራ ምንጫቸው ጌቱ ኃይለማሪያም በተሻገረ ኳስ አደጋ ፈጥረው የታዩ ቢሆንም ፍፁም ገብረማሪያም ከግቡ አፋፍ ላይ ተንሸራቶ ለማስቆጠር ያደረገው ጥረት ሳይሰምር ቀርቷል።

እስከ ውሃ ዕረፍቱ የፉክክር ይዘቱ ጥሩ ሆኖ በማጥቃት ምልልስ የቀጠለው ጨዋታ በቀሪዎቹ የአጋማሹ ደቂቃዎች ግን ተቀዛቅዟል። ሀዲያ ሆሳዕናዎች በንፅፅር የተሻለ የማጥቃት የበላይነት ኖሯቸው የታዩ ሲሆን ከማዕዘን ምቶች እና መካከለኛ ርቀት ካላቸው ቅብብሎች ለመፍጠር የሞከሯቸው የግብ ዕድሎች ሳይሰምሩ ጨዋታው ተጋምሷል።

ከዕረፍት መልስ ሁለቱም የተጫዋች ለውጦችን በማድረግ ተመልሰዋል። ከእነዚህ ውስጥ አንዱ የነበረው ሀብታሙ ታደሰ 50ኛው ደቂቃ ላይ ፍቅረየሱስ ከቀኝ በጥሩ ሁኔታ ተከላካይ አልፎ የሰጠውን ከጠባብ አንግል የሞከረበት አኳኋን ለግብ ቢቀርብም በሰለሞን ደምሴ ድኖበታል። ሰበታዎችም እንዲሁ ተቀይሮ በገባው ዱሬሳ ሹቢሳ ፍጥነት በመጥቀም ወደ ግራ መስመር አዘንብለው አልፎ አልፎ የሚታዩ የመልሶ ማጥቃት አጋጣሚዎችን ለመፍጠር ሲሞክሩ ታይተዋል። ሆኖም ግን ነብሮቹ የማጥቃት የበላይነቱን በመያዝ በእንቅስቃሴ እና በቅጣት ምት ኳሶች ደጋግመው የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር የሚያደርጉት ጥረት ጎልቶ ይታይ ነበር። ያም ቢሆን ግብ ጠባቂዎችን የፈተኑ ሙከራዎች ሳይታዩ ቆይተዋል።

የጨዋታው ቀጣይ አደገኛ የግብ ዕድል 75ኛው ደቂቃ ላይ ሲታይ ፍቅረየሱስ በድጋሚ ከቀኝ ለሀብታሙ ያደረሰው ኳስ ያለቀለት የነበረ ቢሆንም የአጥቂው የኳስ ቁጥጥር ያለመስመር ሰለሞን ደርሶ እንዲያድንበት ምክንያት ሆኗል። በቀሩት ደቂቃዎችም ነብሮቹ ይበልጥ ጫና ፈጥረው ተጫውተዋል። ነገር ግን ወደ ሳጥኑ ሰብረው መግባት ቀላል ያልሆነላቸው ሲሆን ከቅጣት ምት እንዲሁም ከሳጥን ውጪ በሚደረጉ ሙከራዎች ያደረጉት ጥረት ሳይሳካ ቀርቷል። በሌላው የግቡ ጫፍም የሰበታ ከተማዎች ደካማ የማጥቃት ሽግግር ጠንካራ የመልሶ ማጥቃት ዕድል ሳይፈጥርላቸው ጨዋታው ያለግብ ተቋጭቷል።

ውጤቱን ተከትሎ ሀዲያ ሆሳዕና በ34 ነጥቦች 8ኛ ሰበታ ከተማ ደግሞ 21 ነጥቦች 16ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል።