ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 28ኛ ሳምንት ዓበይት ጉዳዮች (፪) – ተጫዋች ትኩረት

ሁለተኛው ፅሁፋችን ደግሞ ትኩረት በሳቡ ተጫዋቾች ላይ ትኩረቱን ያደረገ ይሆናል።

👉 አቡበከር ናስር በክብር ተሸኝቷል

በ2009 በኢትዮጵያ ቡና መለያ ወደ ከፍተኛው የኢትዮጵያ ክለቦች እግርኳስ ብቅ ያለው አቡበከር ናስር ባለፉት ጥቂት ዓመታት ከተስፋ ሰጪ ተጫዋችነት ወደ አስደናቂ ኮከብነት ራሱን ማሸጋገር ችሏል።

ገና በለጋ ዕድሜው በኢትዮጵያ እግርኳስ በትውልዶች መካከል የተገኘ ተሰጥኦ ባለቤት የሆነው አቡበከር በኢትዮጵያ ቡና በነበሩት ዓመታት እጅግ ስኬታማ ጊዜያትን ማሳለፍ ችሏል። በተለይም በተጠናቀቀው የውድድር ዘመን 29 ግቦችን በማስቆጠር ቡድኑን በሊጉ በ2ኛ ደረጃ እንዲያጠናቅቅ ያስቻለበት ስኬት በትልቅነቱ የሚጠቀስለት ነው።

ታድያ በተለይ በተጠናቀቀው የውድድር ዘመን ያሳየውን ድንቅ አቋም ተከትሎ የብዙ ክለቦች የዝውውር ኢላማ የነበረው ተጫዋቹ ከደቡብ አፍሪካው ክለብ ማማሌዲ ሰንዳውንስ የቀረበለትን የዝውውር ጥያቄ ተቀብሎ በመጪዎቹ ቀናት የዝውውር ሂደቱን በይፋ ለማጠናቀቅ ወደ ስፍራው የሚያቀና ይሆናል።
ከዚህ ጋር በተያያዘ በኢትዮጵያ ቡና መለያ የመጨረሻውን ጨዋታ በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት ቡድኑ አርባምንጭ ከተማን ሲገጥም ያደረገው አቡበከር ከጨዋታው መጀመር አስቀድሞ በክለቡ በኩል ይፋዊ የሽኝት መርሃግብር ተደርጎለታል።

ከጨዋታው መጀመር አስቀድሞ የኢትዮጵያ ቡና ተጫዋቾች እና የአሰልጣኝ ቡድን አባላት “መልካሙ ሁሉ ይግጠምህ” የሚል ፅሁፍ የሰፈረበት ቲቨርት ለብሰው ሲያሟሙቁ የተመለከትን ሲሆን ከጨዋታው መጀመር አስቀድሞ የሁለቱ ቡድኖች ተጫዋቾች ወደ ሜዳ በሚገቡበት ወቅት የኢትዮጵያ ቡና ተጫዋቾች ከጀርባው “አቡበከር” እና “10” የሰፈበት እና በፊት ገፁ ደግሞ የአቡበከር ምስል የታተመበትን ቲሸርት ለብሰው ወደ ሜዳ በመግባት ከአርባምንጭ ተጫዋቾች እና ከዕለቱ የጨዋታ አመራሮች ጋር በመሆን የክብር አጥር “Guard of Honour” በመስራት በአጀብ ወደ ሜዳ ያስገቡት ሲሆን በማስከትልም በክለቡ ስራ አስክያጅ አቶ ገዛኸኝ ወልዴ አማካኝነት በክለቡ ይጠቀምበት የነበረው መለያ በስጦታነት የተበረከተለት ሲሆን በማስከትልም ከቡድን አጋሮቹ ጋር በጋራ የማስታወሻ ፎቶ ተነስተዋል።

በተመሳሳይ ጨዋታው ከመጀመሩ አስቀድሞ የመጀመሪያ ተመራጭ ተሰላፊዎች በጋራ “አቡበከር እናመሠግንሀለን” የሚል ባነር ይዘው ፎቶ በመነሳት አጋጣሚውን የሚዘክሩ ታሪካዊ ፎቶዎችን አስቀርተዋል። ምንም እንኳን በጨዋታው በአቡበከር ደረጃ ቀዝቃዛ የነበረ የጨዋታ ዕለት ያሳለፈው ተጫዋቹ ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላ ከክለቡ አመራሮች ፣ የቡድኑ አምበል አማኑኤል ዮሐንስ ፣ የቀድሞ አሰልጣኙ አጥናፉ ዓለሙ እና ከአሰልጣኝ ካሳዬ አራጌ ጋር በመሆን እንዲሁ የመታሰቢያ ኬክ ቆርሰዋል።

ለአምስት ዓመታት የዘለቀ ቆይታን በኢትዮጵያ ቡና መለያ ማድረግ የቻለው አቡበከር ናስር 70 ግቦችን ማስቆጠር የቻለ ሲሆን በግሉም በርካታ ክብሮችን እንዲሁ ተቃዳጅቷል። አቡበከር ናስር አንደኛው የእግርኳስ ህይወቱ ምዕራፍ ተዘግቶ ወደ ሁለተኛው ምዕራፍ እየተሸጋገረ እንደመገኘቱ ያገኘውን ዕድል በሚገባ በመጠቀም እና አቅሙን ይበልጥ አጎልብቶ ስኬቶቹን በማስቀጠል በአውሮፓ የመጫወት ህልሙን እንዲያሳካ እንመኛለን።

👉 ድንቅ የነበሩት ግብ ጠባቂዎች

በጨዋታ ሳምንቱ በተመለከትናቸው ጨዋታዎች መካከል የፍሬው ጌታሁን ፣ መሀመድ ሙንታሪ እና መሳይ አያኖ እንቅስቃሴ ድንቅ የሚባል ነበር።

በጨዋታ ሳምንት “የሞት እና የሽረት” ያህል ትልቅ ዋጋ በነበረው መርሃግብር ምንም እንኳን ድሬዳዋ ከተማዎች በባህር ዳር ከተማዎች በጠባብ ውጤት ቢሸነፉም የድሬዳዋ ከተማው አምበል ፍሬው ጌታሁን እንቅስቃሴ ግን ፍፁም የተለየ ነበር። በጨዋታው በተለይ በሁለተኛው አጋማሽ በርከት ያሉ ያለቀላቸው የግብ ማግባት አጋጣሚዎችን ባህር ዳር ከተማዎች መፍጠር ቢችሉም በዕለቱ ድንቅ የነበረው ፍሬው ጌታሁን ግን የሚቀመስ አልነበረም። ጥቂት የማይባሉ ያለቀላቸው አጋጣሚዎች ጋር የተጋፈጠው ፍሬው በድንቅ ሁናቴ ኳሶቹን ማምከን ችሏል።

በጨዋታ ሳምንቱ ፋሲል ከነማ ሀዋሳ ከተማን 1-0 በረታበት ጨዋታ ሀዋሳ ከተማዎች እስከ መጨረሻው እንዲቆዩ በማድረግ ረገድ ጋናዊው ግብ ጠባቂ የተወጣው ሚና በቀላሉ የሚታይ አይደለም። በጨዋታው በተለይ በመጀመሪያው አጋማሽ አንፃራዊ የበላይነት የነበራቸው ፋሲል ከነማዎች ተደጋጋሚ ሙከራዎችን ማድረግ የቻሉ ሲሆን በጨዋታው ድንቅ የነበረው መሀመድ ሙንታሪ ከአምስት ያላነሱ አደገኛ ሙከራዎችን በማምከን ቡድኑን ከአስከፊ ሽንፈት ታድጓል። በክረምቱ የዝውውር መስኮት ሀዲያ ሆሳዕናን ለቆ ሀዋሳ ከተማን ከተቀላቀለ ወዲህ ምንም እንኳን በ18 ጨዋታዎች ላይ ተሰልፎ የክለቡን ግብ የጠበቀ ቢሆንም ከፋሲል ከነማ ጋር ያሳየው ዓይነት ብቃት በሌሎች ጨዋታዎች አሳይቷል ብሎ ለመናገር አያስደፍርም። ይልቁንም በሚሰራቸው የተለያዩ ስህተቶች ቡድኑን አንገት ሲያስደፋ የቆየው ግብ ጠባቂው ከዚህ ቀደም ወደ ኢትዮጵያ ሲመጣ የነበረውን የሚመስል የሜዳ ላይ ብቃትን በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት አሳይቶናል።

በተመሳሳይ ቅዱስ ጊዮርጊስ ከሀዲያ ሆሳዕና ጋር ባደረጉት እና አንድ አቻ በተለያዩበት ጨዋታ እንዲሁ በውድድር ዘመኑ ለ12ኛ ጊዜ የመሰለፍ ዕድልን ያገኘው መሳይ አያኖ በጨዋታው ጥሩ ጥሩ ኳሶችን ያመከነ ሲሆን በተለይም በሁለት አጋጣሚዎች ቸርነት ጉግሳ ከሳጥን ውጭ እንዲሁም በግንባሩ ገጭቶ ያደጋቸውን ሙከራዎች ያዳነበት መንገድ እንዲሁ በመልካምነቱ የሚነሳ ነበር። የጨዋታ ሳምንቱ የግብ ጠባቂዎች እስኪመስል ድረስ የኢትዮጵያ ቡናው በረከት አማረ እንዲሁም የሲዳማ ቡናው መክብብ ደገፉም እጅግ ለግብ የቀረቡ ኳሶችን ሲያድኑ ተመልክተናል።

👉 ልቡ የተሰበረው ብሩክ ቃልቦሬ

ድሬዳዋ ከተማ በባህር ዳር ከተማ በተረታበት ጨዋታ ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላ የድሬዳዋ ከተማ ተጫዋቾች ስሜት ግን ስሜት የሚነካ ነበር። በተለይ በመጨረሻ ደቂቃ ግብ አስቆጥረው የነበረ ቢሆንም ግቧ ሳትፀድቅ የመቅረቷ ነገር የተጫዋቾቹን ስሜት ክፉኛ የጎዳ አጋጣሚ ነበር።

ታድያ ይህ ጉዳይ እና ሽንፈቱ በሊጉ የመቆየታቸውን ጉዳይ አጣብቂኝ ውስጥ ከማስገባቱ ጋር ተዳምሮ የተጫዋቾቹን ስሜት ይበልጥ የነካ አጋጣሚ ነበር። ከጨዋታው መጠናቀቅ በኃላ በእንባ ታጅቦ ከሜዳ ሲወጡ ከተመለከትናቸው ተጫዋቾች መካከል አንዱ የሆነው ብሩክ ቃልቦሬ ላይ የተመለከትነው የእልህ እና ቁጭት ስሜት ግን የተለየ ነበር።

የጨዋታው መጠናቀቂያ ፊሽካ ሲነፋ በከፍተኛ የሀዘን ስሜት ውስጥ የነበረው ብሩክ የቀድሞው የቡድን አጋሩ እና በጨዋታው ብቸኛዋን የማሸነፊያ ግብ ያስቆጠረው መናፍ ዓወል ሊያበረታው ቢሞክርም እሱ ግን ፍቃደኛ ሳይሆን ቀርቷል። በዚህም እንዲለቀው የተቻለው ሁሉ ጥረት ሲያደርግ የተመለከትንበት አጋጣሚ በሳምንቱ ከተመለከትናቸው ትኩረት የሳቡ አጋጣሚዎች አንዱ ነበር።

👉 አሰልጣኙ ጌታነህ ከበደ

በ25ኛ የጨዋታ ሳምንት ላይ የጨዋታ አመራሮችን ዘልፈሃል በሚል ምክንያት የ3 ጨዋታዎች ቅጣቱ የፀናበት ጌታነህ ከበደ በዚህኛው ጨዋታ ደግሞ በሌላ ሚና ተመልክተነዋል።

ቡድኑ ከሲዳማ ቡና ጋር አንድ አቻ የተለያየበትን ጨዋታ ከተመልካች ጋር ሆኖ የተከታተለው ጌታነህ ከበደ በጨዋታው የመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች ላይ ከተጠቀመጠበት ወርዶ ወደ መልበሻ ቤት መግቢያ ዋሻው በር ላይ በመቆም በጨዋታው የመጨረሻ ደቂቃዎች ሲዳማ ቡናዎች ከወሰዱባቸው ብልጫ አንፃር ተጨማሪ ግብ እንዳያስተናግዱ በተቻለው መጠን የቡድን አጋሮቹን ሲያበረታ ተመልክተናል።

ጌታነህ ከበደ የተጣለበትን ቅጣት በዚህኛው ጨዋታ ማጠናቀቁን ተከትሎ ከቀጣይ ጨዋታ አንስቶ ቡድኑን የሚያገለግል ሲሆን የከፍተኛ ግብ አስቆጣሪነት ፉክክሩ ላይ ልዩነት ይፈጥራል ተብሎ ይጠበቃል።

👉 ሱራፌል ዳኛቸው የተሻለ ብቃቱን እያሳየ ይገኛል

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን እና የፋሲል ከነማ አማካይ የሆነው ሱራፌል ዳኛቸው ከሰሞኑ በወጥ ብቃት እየተንቀሳቀሰ ይገኛል።

በዘንድሮው የውድድር ዘመን ከአፍሪካ ዋንጫው መጀመር አስቀድሞ በነበሩቶ የጨዋታ ሳምንታት በጉዳት ከሜዳ ርቆ የተመለሰው ሱራፌል ዳኛቸው በሁለተኛው የውድድር ዘመን አጋማሽ ግን ቀስ በቀስ ራሱን ፈልጎ እያገኘ ያለ ይመስላል። በተለይ በመጨረሻዎቹ ሁለት ጨዋታዎች ላይ ጨዋታን በሚወስኑ እንቅስቃሴዎች ላይ ያለው ተሳትፎ እያደገ የሚገኘው አማካዩ በሁለት ተከታታይ ጨዋታዎች ግብ የሆነ ኳስ አመቻችቶ ማቀበል ችሏል።

19ኛ የሊግ ጨዋታውን ያደረገው ሱራፌል በሊጉ ሰባት ለግብ የሆኑ ኳሶችን በማቅረብ ረገድ የተሻለ ጊዜን እያሳለፈ የሚገኝ ሲሆን በተለይ ከሙጂብ ቃሲም ጋር እየፈጠሩት የሚገኘው ደመነፍሳዊ መግባባት እጅግ የሚያስደንቅ ነው።

👉 ሪችሞንድ አዶንጎ እና የደስታ አገላለፆቹ

ወደ ኢትዮጵያ እግርኳስ ከተዋወቅ ወዲህ እጅግ ውጤታማውን የውድድር ዘመን እያሳለፈ የሚገኘው ሪችሞንድ ኦዶንጎ በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት ተጨማሪ ሁለት ግቦችን ወደ ግብ ካዝናው ማስገባት ችሏል።

በሊጉ በ26 ጨዋታዎች ላይ በድምሩ ለ2233 ደቂቃዎች ተሰልፎ መጫወት የቻለው አጥቂው በሊጉ በድምሩ ያስቆጠረቅን የግብ መጠን ወደ 14 በማሳደግ አሁንም የሊጉን ከፍተኛ አስቆጣሪነትን ከአቡበከር ናስር እና ይገዙ ቦጋለ ጋር በጣምራ እየመራ ይገኛል።

ታድያ ከግቦቹ ባለፈ ሌላው ትኩረት የሚስበው ጉዳይ ተጫዋቹ ግቦችን ካስቆጠረ በኋላ እንደ አብዛኛዎቹ የምዕራብ አፍሪካ እግርኳሰኞች የሚያሳየው የደስታ አገላለፅ እንዲሁ እጅግ አስገራሚ ነው። ከጨዋታ ጨዋታ የተለያዩ ዳንሶችን የሚያሳየው ተጫዋቹ በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት እንዲሁ በዳንሶቹ አስገርሞናል።

የመጀመሪያዋን ግብ ካስቆጠረ በኋላ ከቡድኑ ተጠባባቂ ግብ ጠባቂ ከሆነው ኮክ ኮየት ጋር ደስታውን የገለፀ ሲሆን ከሁለተኛው ግብ መቆጠር በኋላ ደግሞ በተለየ ዳንስ ከሌሎች የቡድኑ አባላት ጋር በመሆን ደስታውን ሲገልፅ ተመልክተነዋል።

👉 እያደር እየጣፈጠ የሚገኘው ሰልሀዲን ሰዒድ

በሁለተኛው ዙር ሲዳማ ቡናን በመቀላቀል ዳግም ወደ ሊጉ የተመለሰው ሰልሀዲን ሰዒድ በፍጥነት የቡድኑ ቁልፍ ተጫዋች ለመሆን በቅቷል።

የመጀመሪያውን ዙር ክለብ አልባ ሆኖ ያሳለፈው እና በኢትዮጵያ እግርኳስ ከተመለከትናቸው የምንግዜም ምርጥ አጥቂዎች አንዱ የሆነው ሰልሀዲን ሰዒድ በሲዳማ ቡና መለያ ወደ ሊጉ ከተመለሰ በኋላ የባከነውን ጊዜውን ለማካካስ ጥረት እያደረገ ይገኛል። በሊጉ በ12 ጨዋታዎች በሲዳማ ቡና መለያ የተመለከትነው ሰልሀዲን ሰዒድ በድምሩ ሰባት ግቦችን ያስቆጠረ ሲሆን በመጨረሻዎቹ ሁለት ጨዋታዎች ደግሞ እጅግ ወሳኝ የነበሩ ሁለት ግቦችንም እንዲሁ ማስቆጠር ችሏል።

ሰልሀዲን በብዙዎች ዘንድ ዕድሜው ገፍቷል ተብሎ ቢታሰብም አሁንም ግን ከተጋጣሚ ሳጥን ፊት ምህረት የሌለው ተጫዋች እንደሆነ ዳግም እያሳየን ይገኛል። ወደ ሲዳማ ቡና ካመራ ወዲህ የቡድኑ አምበል ለመሆን ጊዜ ያልፈጀበት ተጫዋቹ ዕድሜው ገፍቷል ብለው ሀሳብ ሲሰጡበት የነበሩ አካላትን ዝም ማሰኘቱን ቀጥሏል። ሌላኛው አስገራሚ ነገርም ወልቂጤ ከተማ ላይ ቡድኑን ቀዳሚ ያደረገችውን ግብ ካስቆጠረ በኋላ ያሳየው የደስታ አገላለጽ ትኩረትን የሚስብ ነበር። የታዋቂውን የቱርክ የምግብ ባለሙያ “ሶልት ቤይ” መለያ የሆነውን የእጅ ምልክት በማሳየት ሰልሀዲን ደስታውን ገልጿል።

👉 ሰበታዎች በሚገባ ያልተጠቀሙበት ፍፁም ገ/ማርያም

ባለፉት ጥቂት ጨዋታዎች ከደመሞዝ ጋር በተያያዙ ጉዳዮች ከሰበታ የጨዋታ ዕለት ስብስብ ርቆ የቆየው ፍፁም ገ/ማርያም ዳግም ወደ ሜዳ በተመለሰበት የአዲስ አበባ ከተማው ጨዋታ ጥሩ የጨዋታ ቀንን አሳልፏል።

ሰበታ በአዲስ አበባ ተረቶ መውረዱን ባረጋገጠበት ጨዋታ ለወትሮም ቢሆን ሜዳ ውስጥ በሚኖርባቸው ደቂቃዎች ለቡድኑ የተቻለውን ለማድረግ ሲታትር የምናስተውለው ፍፁም ገ/ማርያም ጥሩ የተንቀሳቀሰ ሲሆን በጨዋታውም ሁለት ግቦችን ማስቆጠር ችሏል። በጨዋታው ሁለት ግቦችን ለቡድኑ ያስገኘው ፍፀም በመጀመሪያው አጋማሽ ያስቆጠራት ግብ አብዱልሀፊዝ ቶፊቅ ያቀበለውን ኳስ ከተከላካዮች አፈትልኮ ከሮጠ በኋላ ልመንህ ታደሰን በቀላሉ በማለፍ በተረጋጋ አጨራረስ ያስቆጠረ ሲሆን በሁለተኛው አጋማሽ ደግሞ ከጌቱ ኃይለማርያም የተሻረለትን ኳስ ተቆጣጥሮ ወደ ግብነት የቀየረበት መንገድ የሚያስንቅ ነበር።

በሊጉ በ24 ጨዋታዎች ላይ ተሳትፎን ያደረገው አጥቂው 14 የሚሆኑት ጨዋታዎች ከተጠባባቂነት እየተነሳ ያደረጋቸው ሲሆን በተቀሩት 10 ጨዋታዎች ደግሞ በመጀመሪያ ተሰላፊነት መጀመር ችሏል። በድምሩ በዚህ ሳምንት ያስቆጠራቸውን ሁለት ግቦች ጨምሮ አምስት ግቦችን ያስቆጠረው ፍፁም ገ/ማርያም ቡድኑ መውረዱን ባረጋገጠበት የዚህኛው የጨዋታ ሳምንት ያሳየው ብቃት ምናልባት የተሻለ የመሰለፍ ዕድል ቢያገኝ ቡድኑ ከዚህ በተሻለ ውጤታማ ይሆን ነበር ብለን እንድናስብ የሚያስገድድ ነበር።

በሊጉ ጥሩ አቅም ካላቸው አጥቂዎች አንዱ የሆነው ፍፁም ገ/ማርያም ወደ ከፍተኛ ደረጃ እግር ኳስ ሲመጣ የተጣለበትን ተስፋ እስከአሁን ሙሉ ለሙሉ መኖር የቻለ አይመስልም። ጥሩ የግብ አግቢነት ደመነፍስ እንዳለው አሁንም ያሳየው አጥቂው አሁንም ቢሆን ወደ ተሻለ ክለብ ማቅናት ከቻለ አቅሙን ዳግም ያስመሰክራል ተብሎ ይጠበቃል።