ከ17 እና ከ15 ዓመት በታች ውድድሮች የሚደረጉበት ቦታ እና ቀን ይፋ ሆኗል

የ2014 ከ17 ዓመት በታች እና ከ15 ዓመት በታች የፓይለት ፕሮጀክት ውድድሮች የሚደረጉበት ከተማ እና ቀን ታውቋል፡፡

በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌድሬሽን አዘጋጅነት ከዚህ ቀደም ከ17 ዓመት በታች ፕሪምየር ሊግ በሚል ስያሜ ሲደረግ የነበረው ውድድር አብዛኛዎቹ ተወዳዳሪ ክለቦች ውስጥ የሚገኙ ተጫዋቾች ተማሪዎች በመሆናቸው ከተጠናቀቀው የ2013 የውድድር ዘመን ጀምሮ የስያሜ ለውጥ በማድረግ በክረምት ወራት ሀገር ዓቀፍ የክለቦች እና የክልሎች ውድድር በሚል መደረግ መጀመሩ ይታወሳል፡፡ የዘንድሮውም ውድድርም በዚሁ ስያሜ ከሐምሌ 16 እስከ ነሐሴ 1 ድረስ በሀዋሳ ከተማ እንዲደረግ መወሰኑን ፌድሬሽኑ ገልጿል፡፡

በተያያዘ ዜናም የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌድሬሽን በየክልሉ ያቋቋመውን ከ15 ዓመት በታች ፕሮጀክት የምዘና ውድድርን ለመጀመሪያ ጊዜ በአርባምንጭ ከተማ ከሐምሌ 10 – 24 ድረስ እንዲደረግ መወሰኑን ፌድሬሽኑ አያይዞ ገልጿል፡፡