ሪፖርት | የወራጅ ቀጠናው ተጠባቂ ጨዋታ በአቻ ውጤት ተጠናቋል

ለዓይን ሳቢ የነበረው የአዳማ ከተማ እና ድሬዳዋ ከተማ ጨዋታ 1-1 መጠናቀቁን ተከትሎ ባህር ዳር ከተማ እና መከላከያ በሊጉ መቆየታቸውን ሲያረጋግጡ የዛሬዎቹ ተጋጣሚዎች ዕጣ ፈንታቸውን ለማወቅ የመጨረሻ ጨዋታዎቻቸውን ይጠብቃሉ።

አዳማ ከተማ ከመከላከያ ነጥብ ከተጋራበት ጨዋታ አንፃር ጉዳት የገጠመው አማኑኤል ጎበናን ከሦስት ጨዋታዎች ቅጣት በተመለሰው ዳዋ ሆቴሳ ተክቷል።

በድሬዳዋ በኩል ከባህር ዳሩ ሽንፈት በተደረጉ ለውጦች የአምስት ቢጫ ካርድ ቅጣት ያገኘው ፍሬው ጌታሁን በደረጄ ዓለሙ እንዲሁም ማማዱ ሲዲቤ በሙኸዲን ሙሳ ተለውጠዋል።

ተጠባቂነቱን በሚመጥን ውጥረት ያለበት እንቅስቃሴ በጀመረው ጨዋታ አዳማ ከተማዎች የኳስ ቁጥጥሩን ይዘው ድሬዳዋ ከተማዎች ደግሞ በአመዛኙ በሜዳቸው ላይ በመቆየት ተንቀሳቅሰዋል። ሆኖም 11ኛው ደቂቃ ላይ ደስታ ዮሐንስ የሰራውን የቅብብል ስህተት ለመጠቀም ሱራፌል ጌታቸው ያደረገውን ጥረት ለማቋረጥ ሚሊዮን ሰለሞን የሰራውን ጥፋት ተከትሎ የተገኘውን ወደ ቀኝ ያደላ የቅጣት ምት አብዱለጢፍ መሐመድ በቀጥታ በመምታት ድንቅ ግብ አስቆጥሮ ብርቱካናማዎቹን ቀዳሚ አድርጓል።

ከግቡ በኋላ አዳማ ከተማዎች አቡበከር ወንድሙ በተሰለፈበት የቀኝ መስመር ያደላ እና በቅብብሎች ላይ የተመሰረተ ጥቃት ለመሰንዘር ጥረዋል። ሆኖም በግቡ የተረበሹ ከሚመስሉት አዳማዎች እንቅስቃሴ ይልቅ ድሬዳዋ ከተማዎች በመልሶ ማጥቃት የሚወጡባቸው ቅፅበቶች ወደ አደገኛ ዕድልነት ለመቀየር የቀረቡ ነበሩ። ለዚህም ማሳያ የሚሆነው ቡድኑ 24ኛው ደቂቃ ላይ አብዲሳ ጀማል 29ኛው ደቂቃ ላይ ደግሞ አቡበከር ወንድሙ ከግማሽ ጨረቃው አካባቢ ካደረጓቸው ኢላማቸውን ያልጠበቁ ሙከራዎች ውጪ ጠንካራ ሙከራ አለማድረጉ ነው። ጥሩ ቦታዎች ላይ የተገኙ ቅጣት ምቶች ቢኖሩም ዳዋ ሆቴሳ ሳይጠቀምባቸው ቀርቷል።

የአጋማሹ የመጨረሻ ደቂቃዎች የሜዳ ላይ ፍትጊያዎች በርከት ብለውባቸው በጥሩ ፉክክር የቀጠሉ ሲሆን ሁለቱም በመረጡት አጨዋወት ያለቀላቸው የግብ ዕድሎችን ሳይፈጥሩ አንዳቸው የሌላኛቸውን ጥቃት እያቋረጡ የቀጠሉባቸው ነበሩ። 

በአጋማሹ ጭማሪ ደቂቃ ላይ ብቻ ዮሴፍ ዮሐንስ ከርቀት አክርሮ የመታውን ኳስ ደረጄ ዓለሙ መቆጣጠር ሳይችል ቢቀርም በቅርብ የአዳማ ተጫዋቾች ባለመኖራቸው አጋጣሚው ያለፈበት ቅፅበት በአደገኛ ሙከራነት የሚጠቀስ ነበር።

ከዕረፍት መልስ አዳማ ከተማዎች ሦስት ቅያሪዎች አድርገው ገብተዋል። በጣም ከባድ በሆነ ዝናብ በጀመረው አጋማሽ አዳማዎች ብዙም ሳይቆዩ የአቻነቷን ግብ አግኝተዋል። ከተቀያሪዎቹ መካከል አንዱ የሆነው ወጣቱ ቢኒያም አይተን ከሳጥኑ መግቢያ ላይ በድንቅ ሁኔታ ተጫዋቾችን አልፎ ወደ ግብ ለሌላኛው ተቀያሪ አሜ መሐመድ ያደረሰውን ተንጠልጣይ ኳስ ድሬዳዋዎች ለማራቅ ያደረጉት ጥረት ሳይሳካ አብዲሳ ጀማል 52ኛው ደቂቃ ላይ ጎል አድርጎታል።

ከግቡ በኋላ በቶሎ ወደ ማጥቃት መንፈስ የተመለሱት ድሬዳዋዎች ጫና መፍጠር የቻሉ ሲሆን በአቤል አሰበ እና አቤል ከበደ አማካይነት ወደ ግብ የላኳቸው ኳሶች በአዳማ ተከላካዮች ተደርበዋል።

አዳማዎችም ጫናውን ቀስ በቀስ በማርገብ ቀጥተኛ በሆኑ ኳሶች በድሬ ሳጥን ውስጥ የተገኙባቸውን ጥሩ አጋጣሚዎች መፍጠር ችለው ነበር። ቡድኑ በዮሴፍ ዮሐንስ እና ተፅዕኖው በቀጠለው ቢኒያም አይተን ለጥቂት የወጡ የርቀት ሙከራዎችን ሲያደርግ ከፍ ባለ ጫና መጫወቱን ቀጥሎ የጨዋታውን የኃይል ሚዛን በእጁ አድርጓል። በዚህም 75ኛው ደቂቃ ላይ አዲስ ተስፋዬ በረጅሙ ያሻገረውን የቅጣት ምት ቢኒያም አይተን ጨርፎ እንዲሁም ይህ እንቅስቃሴ በማዕዘን ምት ሲቀጥል ወሰኑ ዓሊ ከግራ አቅጣጫ አክርሮ በመምታት ያደረጓቸውን ለግብ የቀረቡ ሙከራዎችን ደረጄ ዓለሙ አመከናቸው እንጂ አዳማ መሪ ለመሆን ተቃርቦ ነው።

የደረጄ ዓለሙን ብቃት ካየንባቸው ከእነዚህ ሙከራዎች 5 ደቂቃዎች በኋላ ደግሞ ሳኩባ ካማራ ተመሳሳይ ገድል ፈፅሟል። ተጫዋቹ የማማዱ ሲዲቤን ጠንካራ ቅጣት ምት ሲመልስ ሱራፌል ጌታቸው በድጋሚ ያደረገውን ሙከራም አድኗል። በሁለተኛው አጋማሽ እጅግ ተሻሽለው የቀረቡት አዳማ ከተማዎች በማጥቃቱ ሲቀጥሉ የድሬዳዋ ምላሽም እንቅስቃሴውን ከሳጥን ሳጥን የሚመላለስ ለዓይን ማራኪ ፉክክር አድርጎታል። በአየሩ እና በሜዳው ሁኔታ በእጅጉ የተፈተኑት ሁለቱ ተጋጣሚዎች ለመሸናነፍ ያደረጉት ጥረት እስከፍፃሜው ቢዘልቅም ጨዋታው ሌላ ግብ ሳያስተናግድ በ 1-1 ውጤት ተቋጭቷል።

ውጤቱን ተከትሎ ድሬዳዋ ከተማ በ30 ነጥቦች 14ኛ ደረጃ ላይ ሲቆይ አዳማ ከተማ ደግሞ ወደ 32 ነጥብ መጥቶ በግብ ክፍያ ወደ 12ኛ ደረጃ ከፍ በማለቱ ቡድኖቹ ቀጣይ ዕጣ ፈንታቸውን በመጨረሻው ሳምንት ለመጠበቅ ተገደዋል።