ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ | የ29ኛ ሳምንት ምርጥ 11

በ29ኛ የጨዋታ ሳምንት በአንፃራዊነት ምርጥ ብቃት ያሳዩ ተጫዋቾችን ያካተትንበት ምርጥ 11 በሚከተለው መልኩ ተሰናድቷል።

የተጫዋች አደራደር ቅርፅ : 4-3-3

ግብ ጠባቂ


ሮበርት ኦዶንካራ – ወልቂጤ ከተማ

የነጠረ ብቃት ያሳዩ የግብ ዘቦችን እምብዛም ባላየንበት ሳምንት በቦታው በአንፃራዊነት የተሻለውን ኦዶንካራ መርጠናል። ተጫዋቹ በጥሩ ጥሩ ቅልጥፍና ያዳናቸው ኳሶች እንዳሉ ሆነው በ51ኛው ደቂቃ ጅማዎች ወደ ጨዋታው ሊመለሱ የሚችሉበትን የፍፁም ቅጣት ምት አግኝተው ያዳነበት መንገድ ያለ ከልካይ ተመራጭ እንዲሆን አድርጎታል።

ተከላካዮች


ረመዳን የሱፍ – ወልቂጤ ከተማ

ወልቂጤ ከተማ ከሰባት ጨዋታዎች በኋላ ድል አሳክቶ በሊጉ መክረሙን ሲያረጋግጥ ጥሩ ብቃት ካሳዩ ተጫዋቾች መካከል ረመዳን የሱፍ አንዱ ነው። የግራ መስመር ተከላካዩ ዋነኛ ሀላፊነቱ ከሆነው መከላከል ባለፈ የቡድኑ የማጥቃት አጨዋወት የሜዳውን የጎንዮሽ ስፋት እንዲያገኝ ሲጥር ታይቷል። ከእግሩ ሲነሱ የነበሩ ተሻጋሪ ኳሶችም ለጅማ ተከላካዮች ፈታኝ ነበሩ። በመከላከሉ ደግሞ ፈጣኖቹን የጅማ አጥቂዎች በተሻለ አፈፃፀም ሲከላከላቸው ነበር።

ወልደአማኑኤል ጌቱ – ሰበታ ከተማ

በደካማው የሰበታ የመከላከል አወቃቀር በግሉ ተስፋ ሰጪ እንቅስቃሴ ሲያደርግ የሚታየው ወልደአማኑኤል በምርጥ ቡድናችን ውስጥ ተካቷል። ተጫዋቹ ቡድኑ ሰበታ ከባህር ዳር ጋር አንድ ለአንድ ሲለያይ በተጋጣሚ በኩል የነበረውን የማጥቃት ማዕበል ከአጋሮቹ ጋር በመሆን ያዳነበት መንገድ አስደናቂ ነበር። በዋናነት የአንድ ለአንድ ግንኙነቶች ላይ ሲወስናቸው የነበሩ ቅፅበታዊ ውሳኔዎች ቡድኑን እጅግ ሲጠቅም ነበር።

ዋሀብ አዳምስ – ወልቂጤ ከተማ

ግዙፉ ተከላካይ ከግብ ጋር የተገናኘበትን የመጀመሪያ የጨዋታ ሳምንት (በ18ኛ ሳምንት ባህር ዳር ላይ ያስቆጠረው ጎል በፎርፌ ምክንያት ሳይቆጠር እንደቀረ ልብ ይሏል) ሲያሳልፍ ድንቅ ሆኖ ነበር። ተጫዋቹ የቡድኑን መክፈቻ ጎል በግንባሩ ከማስቆጠሩ በተጨማሪ የጅማ የኳስ ቁጥጥር ወደ ግብነት እንዳይቀየር ከፍ ያለ ስራን ሲሰራ አስተውለናል።

አናጋው ባደግ – ወላይታ ድቻ

በግራም ሆነ በቀኝ የመስመር ተከላካይ ሚና የመጫወት ብቃት ያለው አናጋው የውድድር ዓመቱ የመጀመሪያ ግቡን የስሆሆ ሜንሳ መረብ ላይ በድንቅ ሁኔታ አሳርፏል። እንብዛም ከጎል ጋር የማይገናኘው ተጫዋቹ ከአዲስ ህንፃ በመቀጠል ብዙ ለግብ የሆኑ ኳሶችን አመቻችቶ ያቀበለ ሲሆን በመከላከሉ ግን የተሻለ ለቡድኑ ትልቅ ጥቅም ይሰጣል። በጨዋታውም ሀዲያ ሜዳውን ለጥጦ ለማጥቃት ሲያደርግ የነበረውን ጥረት በተቻለው መጠን ለማምከን ሲሞክር ነበር።

አማካዮች


ሙሉዓለም መስፍን – ሲዳማ ቡና

ከ2 ሺ ደቂቃዎች በላይ ከተጫወቱ 7 የሲዳማ ተጫዋቾች መካከል አንዱ የሆነው ሙሉዓለም “ቆሻሻውን ስራ” ከመስራቱ በተጨማሪ በአዲስ አበባው ጨዋታ የቡድኑን የመክፈቻ ጎል የመዓዘን ምትን መነሻ ባደረገ አጋጣሚ አስቆጥቷል። በዋናነት ለተከላካዮች በአግባቡ ሽናፍ ሲሰጥ የነበረ ሲሆን ቡድኑም ከተጋጣሚ የተሻለ የኳስ ቁጥጥር እንዲኖር ትልቁን ድርሻ ሲወጣ አይተናል።

ሱራፌል ዳኛቸው – ፋሲል ከነማ

ተዐምረኛው አማካይ ቡድኑ ኢትዮጵያ ቡናን ሦስት ለምንም ሲረታ ሦስት ጎሎች ላይ ተሳትፎ አድርጓል። በጨዋታው ያሳየውን ብቃት ተከትሎም ለሦስተኛ ተከታታይ ጊዜ የሶከር ኢትዮጵያ ምርጥ ቡድን ውስጥ ገብቷል። ከኳስ ጋር ምቾት ያለው አማካዩ በተለይ የመጀመሪያው የሙጂብ ጎል እንዲገኝ የተከላካዮች እንዲሁም የአጋሩን አቋቋም ተመልክቶ ልኬቱን የጠበቀ ኳስ ማቀበሉ በብዙዎች ዘንድ አድናቆት ሲያስገኘው ነበር። በተጨማሪም በፍፁም ቅጣት ምትም ቢሆን ከ28 ወራት በኋላ ግብ አስቆጥሯል።

ከነዓን ማርክነህ – ቅዱስ ጊዮርጊስ

13ኛው ለቅዱስ ጊዮርጊስ ብዙ ደቂቃዎችን የተጫወተ ተጫዋች የሆነው ከነዓን በዚህም ሳምንት ወሳኝ ሦስት ነጥብ እንዲገኝ ግብ አስቆጥሯል። የአጥቂ አማካዩ የቡድኑ የኳስ ቁጥጥር እድገት እንዲኖረው ለማድረግ ሲጥር ይታያል። ዋና ሀላፊነቱ ከሆነው ለግብ የሆኑ ኳሶችን ከማቅበል ባለፈ ራሱ የዘገዩ ሩጫዎችን በማድረግ ግቦችን ያስቆጥራል። ተቀይሮ እስከወጣበት ጊዜ ድረስም ከኳስ ውጪ ለቡድኑ የኋላ መስመር ጥሩ ድጋፍ ለማድረግ ሲታትር አስተውለናል።

አጥቂዎች


ዑመድ ኡኩሪ – ሀዲያ ሆሳዕና

ሀዲያ ከስምንት ጨዋታዎች በኋላ ከአንድ በላይ ግብ እንዲያገኝ የዑመድ ብቃት ወሳኝ ነበር። ዓምና ከግብፅ ከተመለሰ በኋላ በሊጉ እጅግ ሲቸገር የነበረው ዑመድ በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት ስል ግራ እግሩን ተጠቅሞ የውድድር ዓመቱ ሁለተኛ እና ሦስተኛ ግቡን አስመዝግቧል። በጨዋታው የሚገርም እርጋታ፣ ፈጣን ውሳኔዎች፣ ጥብቅ ምቶች እና አስደናቂ የቦታ አያያዝ ሲስተዋልበት የነበረው ተጫዋቹ በምርጥ ቡድናችን ቦታ አግኝቷል።

ሙጂብ ቃሲም – ፋሲል ከነማ

ፋሲል ከነማ የሊጉን መሪ ቅዱስ ጊዮርጊስ እግር በእግር እየተከተለ ራሱን በዋንጫ ፉክክሩ እንዲያዘልቅ ባለፉት ሦስት ጨዋታዎች የተመዘገቡት ውጤቶች ወሳኝ ናቸው። በእነዚህ ወሳኝ ጨዋታዎች ድንቅ የሆነው ሙጂብ ባሳለፍነውም ሳምንት ኳስ እና መረብን አገናኝቷል። ተጫዋቹ ተለምዷዊውን አስገራሚ የቦታ አጠባበቅ እና አጨራረስ ብቃቱን ያሳየበትን ጨዋታ በመንተራስ የቡድናችን አጋፋሪ አድርገነዋል።

በረከት ደስታ – ፋሲል ከነማ

ፈጣኑ የመስመር አጥቂ ቡድኑ ከኢትዮጵያ ቡና ሦስት ነጥብ እና ጎል ሲያገኝ በቀጥታ ጎሎች ላይ ባይሳተፍም በእንቅስቃሴ ረገድ ምርጥ ነበር። ፍጥነቱን ተጠቅሞ የቡና ተከላካዮችን ሲፈትን የነበረው በረከት ሁለተኛው የሙጂብ ጎልም እንዲቆጠር አበርክቶ ነበረው። ከኳስ ውጪ ደግሞ የተጋጣሚን የኳስ ምስረታ ለማቋረጥ ሲጥርበት የነበረበት መንገድ ድንቅ ነበር።

አሠልጣኝ


ዘሪሁን ሸንገታ – ቅዱስ ጊዮርጊስ

በጨዋታ ሳምንቱ ትልቅ ግምት ተሰጥቷቸው ከነበሩ መርሐ-ግብሮች መካከል አንዱ የጊዮርጊስ እና አርባምንጭ ጨዋታ ተጠቃሽ ነው። የጨዋታውን ግለት እና ውጥረት ተከትሎም የፈረሰኞቹን አለቃ ዘሪሁን ጥሩ ቡድን ካሳዩን ኃይሉ ነጋሽ እና ተመስገን ዳና እንዲሁም በተሻለ የእረፍት ሰዓት የተጫዋች እና የፎርሜሽን ለውጥ ቡድናቸውን ካሻሻሉት ይታገሱ እንዳለ በላይ መርጠናል። ጊዮርጊስ ግብ ካገኘ በኋላ አቻ ሊሆንባቸው የተቃረቡ ቅፅበቶች ተፈጥረው የነበረ ቢሆንም የአርባምንጭን ወሳኝ ተጫዋቾች በመቆጣጠሩ ረገድ ግን የተሻለ ነበር። ድሉም እጅግ ብዙ ትርጉም ያለው ስለሆነ ዘሪሁን የምርጥ ቡድናችን አሠልጣኝ አድርገናቸዋል።

ተጠባባቂዎች

ይስሀቅ ተገኝ
አዲስ ተስፋዬ
ግሩም ሀጎስ
አንዱዓለም አስናቀ
ኢማኑኤል ላርዬ
ጌታነህ ከበደ
ብሩክ በየነ
ኦሴ ማውሊ