የሴቶች ፕሪምየር ሊግ | ንግድ ባንክ በጎል ተንበሽብሾ ሲያሸንፍ አርባምንጭ እና ባህር ዳር ነጥብ ተጋርተዋል

የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ የ17ኛ ሳምንት ሁለት ቀሪ ጨዋታዎች ዛሬ ሲከወኑ መሪው ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በግማሽ ደርዘን ጎል ድሬዳዋን ሲያሸንፍ አርባምንጭ ከተማ በጭማሪ ደቂቃ ያስተናገደው ግብ ከባህር ዳር ከተማ ጋር ነጥብ እንዲጋራ አድርጎታል፡፡

ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ 6-0 ድሬዳዋ ከተማ

8፡00 ላይ በአዳማ አበበ ቢቂላ ስታዲየም ሊጉን እየመራ የሚገኘው ኢትዮጵያ ንግድ ባንክን ከድሬዳዋ ከተማ ባገናኘው ጨዋታ በመጀመሪያው አጋማሽ ሦስት አስር ደቂቃዎች በራሳቸው የሜዳ ክፍል ተወስነው የቆዩት ሁለቱ ቡድኖች በሂደት ግን ደቂቃዎች እየገፉ ሲመጡ በአንድ ሁለት የቅብብል ፍሰት መውጣት ጀምረዋል። ከመሀል ክፍሉ ሰናይት ቦጋለ እና ትዕግስት ያደታን መሠረት ካደረገ መነሻ እንዲሁም ደግሞ በቀኝ በኩል በተሰለፈችው ዕፀገነት ብዙነህ አማካኝነት ጥቃት ለመሰንዘር የታተሩት ንግድ ባንኮች በመከላከሉ ረገድ ደካማ አልፎም ደግሞ የወጥነት ችግር በሚታይባቸው ድሬዳዋ ከተማ ላይ የበላይነት መውሰድን ጀምረዋል፡፡

በዚህም 35ኛው ደቂቃ ላይ ሰናይት ቦጋለ በድሬዳዋ ተከላካዮች መሀል ለመሀል ያሾለከችላትን ልማደኛዋ አጥቂ ሎዛ አበራ ከመረብ ጋር አገናኝታው ቡድኗን መሪ አድርጋለች፡፡ ከግቧ በኋላ ጨዋታውን ለመቆጣጠር ድሬዳዋዎች በሚጥሩበት ቅፅበት ዳግመኛ ግብ ተቆጥሮባቸዋል፡፡ 

ከማዕዘን መነሻውን ካደረገ ኳስ የተገኘን አጋጣሚ ሁለገቧ ተጫዋች ዕፀገነት ብዙነህ ወደ ጎልነት ቀይራው ንግድ ባንክን ወደ 2-0 መሪነት አሸጋግራለች፡፡ አጋማሹ ሊገባደድ ሁለት መደበኛ ደቂቃዎች ሲቀሩ ከግራ በኩል ከሰናይት ቦጋለ ጣጣውን የጨረሰ ኳስ ያገኘችው መዲና ዐወል ውጤቱን 3-0 ያደረገ ጎል በማስቆጠር ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል፡፡

ጨዋታው ከዕረፍት ሲመለስ ድሬዳዋ ከተማዎች በተከታታይ የተጫዋች ለውጥ በማድረግ ወደ ጨዋታ ቅኝት ለመመለስ ቢጥሩም አሁንም ልክ እንደ መጀመሪያው አጋማሽ ከሰላሳ ደቂቃዎች በኋላ እንደ ተቆጠረባቸው ሁሉ ዳግም ግብ ሊያስተናግዱ ተገደዋል፡፡ 70ኛው ደቂቃ ላይ መዲና ዐወል ለራሷ ሁለተኛ ለቡድኗ አራተኛ ጎል ከ11 ደቂቃዎች በኋላ ተቀይራ የገባችው ዮርዳኖስ ምዑዝ እንዲሁም የጨዋታው የመጨረሻ ደቂቃ ላይ ማራኪ ግብን ሎዛ አበራ ለጨዋታው ስድስተኛ ለራሷ ደግሞ ሁለተኛ ጎል አክላ ጨዋታው በ6-0 ውጤት ፍፃሜን አግኝቷል፡፡

ባህርዳር ከተማ 1-1 አርባምንጭ ከተማ

የሳምንቱ የመጨረሻ ጨዋታ በባህር ዳር ከተማ እና አርባምንጭ ከተማ መካከል ተደርጎ አርባምንጭ ከተማ 87 ደቂቃዎች ሲመራ ቆይቶ በጭማሪ ደቂቃ ሽርፍራፊ ሰከንድ ውስጥ የተቆጠረበት ጎል ሁለት ነጥብ እንዲያጣ አድርጎታል፡፡ በአሰልጣኝ ዮሴፍ ገብረወልድ የሚመሩት አርባምንጮች በጨዋታው የመጀመሪያው አጋማሽ ሀያ አምስት ደቂቃዎች ውስጥ በነበራቸው የሜዳ ላይ የእንቅስቃሴ ብልጫ መሠረት ቀዳሚ የሆኑበትን ግብ ገና በጊዜ ነበር ማግኘት የቻሉት፡፡ 5ኛው ደቂቃ ላይ የቀድሞዋ የሀዋሳ ከተማ አማካይ ትውፊት ካዲኖ በባህርዳር ተከላካዮች መሀል ለመሀል ፊቷን ወደ ጎል አዙራ ተዘጋጅታ ለነበረችው ድንቅነሽ በቀለ ሰጥታት የባህርዳር ተከላካዮች ስህተት ታክሎበት ዕንስት አዞዎቹን መሪ ያደረገች ጎል አስቆጥራለች፡፡

ጎል ከተቆጠረባቸው በኋላ ወደ ጨዋታው ቀስ በቀስ ለመግባት የሞከሩት የአሰልጣኝ ሰርካአዲስ ዕውነቱ ባህርዳር ከተማዎች በተደጋጋሚ በምስር ኢብራሂም አማካኝነት ዕድሎችን ለመፍጠር ቢጥሩም ኳስ እና መረብን ለማገናኘት አልታደሉም፡፡ በአንፃሩ ጨዋታውን በሚገባ በመቆጣጠር ተጨማሪ ግብ ለማስቆጠር ጥቂት የማይባል ዕድሎችን የፈጠሩት አርባምንጮች በሁለተኛው አጋማሽ የመጨረሻዎቹ ሀያ ደቂቃዎች የነበራቸው ደካማ የመከላከል ብቃት በተቃራኒው ብልጫ ወስደው ሲጫወቱ በነበሩት ባህርዳር ከተማዎች ግብ ተቆጥሮባቸው አቻ ሊሆኑ ተገደዋል፡፡ በጭማሪ ደቂቃ ሽርፍራፊ ሰከንድ 90+3 ላይ ከቅጣት ምት ሊዲያ ጌትነት የምህረት ተሰማን የቦታ አጠባበቅ ስህተት ተጠቅማ ያስቆጠረችው ጎል ባህርዳር ከተማ በመጨረሻም አንድ ነጥብ ይዞ እንዲወጣ አድርጋለች።