ዋልያዎቹ የቻን የማጣሪያ ጨዋታቸውን የሚያደርጉበት ሀገር ታውቋል

የካፍ የስታዲየም መመዘኛ መስፈርት አለማሟላቱን ተከትሎ የሜዳ ላይ ጨዋታዎቹን ከሀገር ውጪ እያደረገ የሚገኘው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ከደቡብ ሱዳን ጋር የቻን ማጣሪያ ጨዋታውን የሚያደርግበት ሀገር ይፋ ሆኗል፡፡

በሀገር ውስጥ ተጫዋቾች ብቻ በካፍ አዘጋጅነት በየሁለት አመቱ የሚደረገው የቻን የአፍሪካ ዋንጫ የቅድመ ማጣሪያ ጨዋታዎች በያዝነው ዐመት ነሀሴ ወር ላይ ይከውናሉ፡፡ በማጣሪያው ከደቡብ ሱዳን ጋር የተደለደለችው ሀገራችን ኢትዮጵያ ሜዳዋ የካፍን የመመዘኛ መስፈርት አለማሟላቷን ተከትሎ በተጣላባት ዕገዳ ልክ እንደ አፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ጨዋታዎቿ ሁሉ ይህንንም ጨዋታ ከሜዳዋ ውጪ እንደምታደርግ ይታወቃል። ይህ ጨዋታ ደግሞ የት እንደሚከናወን የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የጽሕፈት ቤት ሀላፊ አቶ ባህሩ ጥላሁን ለሶከር ኢትዮጵያ ተናግረዋል።

እንደ ዋና ፀሀፊው ገለፃ ከሆነ ታንዛኒያ በሀገሯ ማጣሪያውን ኢትዮጵያን እንድታደርግ ፍቃደኛ መሆኗን ተከትሎ ነሀሴ ወር ላይ ጨዋታው በዳሬሰላም ይደረጋል፡፡ የመልሱም ጨዋታ ደቡብ ሱዳን በካፍ ሜዳዎቿ የዕገዳ በትር ስላረፈበት በተመሳሳይ የታንዛኒያን ስታዲየም ምርጫዋ በማድረጓ እዛው ይከናወናል።