የአሰልጣኞች አስተያየት | ወላይታ ድቻ 0-2 ወልቂጤ ከተማ

የመጨረሻ ሳምንት የመጀመሪያ ከነበረው ጨዋታ መጠናቀቅ በኋላ የሁለቱ ቡድኖች አሰልጣኞች ተከታዩን ሀሳብ ሰጥተዋል።

ፀጋዬ ኪዳነማርያም – ወላይታ ድቻ

ስለጨዋታው

“ወደ ዛሬው ጨዋታ ስንመጣ እንደአጠቃላይ የእኛ ታዳጊ ተጫዋቾች ምን ይመስላሉ የሚለውን ለመገምገም ሞክረናል ፤ ከዘንድሮ ምን አገኘን በቀጣይ ምን ማሻሻል ይኖርብናል የሚለውን ነገር ተመልክተንበታል።በጨዋታው እንደተመለከትነው አብዛኞቹ ልጆች ከቅድመ ውድድር ዝግጅት አንስቶ ከእኛ ጋር የነበሩ ልጆች ናቸው ፤ ለዚህም ልምድ እንዲያገኙ አስበን በሜዳ ላይ ተጠቅመናቸዋል ስለዚህ ጨዋታውን ከዚህ እቅድ አንፃር ነው የምንገመግመው።”

19 የግብ ሙከራ አድርገው ግብ ስላለማስቆጠራቸው

“ኳሱን በትዕግስት ለመቀባበል ሆነ በአጠቃላይ እንቅስቃሴ ረገድ ጥሩ ነበርን ነገርግን ወደ ማጥቂያው ሲሶ ስንደርስ መጣደፎች እና መቻኮሎች ነበሩ ይህ ደግሞ ከልምድ የሚመጣ ነው።መድረሳቸውን ታደንቃለህ ነገርግን ግብ ፊት መሻሻል ያለባቸው ነገሮች አሉ።”

በወጣት ተጫዋቾች መጠቀሙ በጨዋታው ስላስገኘለት

“ሜዳ ላይ ያሱዩት እንቅስቃሴ ፍንጭ የሚሰጥ ነገር አለው ፤ የዛሬው ጨዋታ ብቻ ሳይሆን የውድድር ዘመኑ ጉዟችን ምን ማሻሻል እንዳለብን በደንብ አሳይቶናል። የውድድር ዘመኑ የማራቶን ውድድር እንደመሆኑ በሁለተኛው ዙር በተለይ ተቸግረን ነበር በተለይ አንዳንድ ተጫዋቾች ሲጉዱብን ተቸግረን ነበር እንጠአጠቃላይ ግን የውድድር ዘመኑ በሰላም እና በፍቅር ብዙ የተማርንበት ጥሩ የውድድር ዘመን ነበር ከዚህ በላይ ማሳደግ እንደምንችል እናስባለን ብዙ ጫና ያለበት ቡድን አይደለም ደጋፊዎቻችን በውድድር ዘመኑ ከከተማ ከተማ እየተጓዙ ለሰጡን ድጋፍ በዚሁ ለማመስገን እወዳለሁ።”

ተመስገን ዳና – ወልቂጤ ከተማ

ስለጨዋታው

“በተወሰኑ ተጫዋቾች ጉዳት ዛሬ በ3-5-2 ቅርፅ ነው የመጣነው እንደሚታወቀው ድቻ በመስመር ለማጥቃት የሚሞክር ቡድን ነው በመሆኑም ይህን ሂደት በመስመር በኩል በማጥቃት ለመከላከል የሞከርነው ነገር በተወሰነ መልኩ ተሳክቷል ብዬ አስባለሁ ነገርግን የመከላከል ሽግግራችን እጅግ ደካማ ነበር የእነሱ የቴክኒክ አፈፃፀም ደካማ ስለነበር እንጂ ግቦችን እናስተናግድ ነበር።”

ስለመሀል ሜዳው እንቅስቃሴ

“ወደ ቡድኑ ከመጣው ወዲህ እጠቀምባቸው የነበሩ ቁልፍ የአማካይ ተጫዋቾች ዛሬ አልነበሩም ፤ ተክተው የገቡት ልጆች መጥፎ ሆነው ሳይሆን ከእንስቃሴ መራቃቸው በተወሰነ መልኩ ራሳቸውን እንዳይገልፁ አድርጓቸዋል ከዚህ ውጭ ግን ጥሩ ነበረ።”

ስለጌታነህ ከበደ

“እሱ በኢትዮጵያ እግርኳስ ታሪክ ከተመለከትናቸው ድንቅ አጥቂዎች አንዱ ነው ፤ ምንም ጥያቄ የለውም ሳጥን ውስጥ ከገባ ጨራሽ ነው ያንንም ነው ዛሬ ያደረገው። እኔ እስከመጣ 3 ጎሎች ብቻ ነው የነበሩት ከመጣሁ 11 ግቦችን አግብቷል ስለዚህ ቡድኑን ካሻሻልንበት መንገድ አንዱ ጌታነህ ነው ከ2011 ወዲህ በግብ አግቢነት ፉክክር ውስጥ ርቆ ነበር ዘንድሮ ግን በግል እሱም እኛም ተሻሽለናል ይህን ያደረገው ጥሩ አጥቂ ስለሆነ ነው።”

የውድድር ዘመኑ ጉዞ

“ለእኔ በተወሰነ መልኩ ፈታኝ ነበር በተለይ ደግሞ ከሜዳ ውጭ ያሉ ጉዳዮች ፈትነውኛል።ከዛ ውጭ ልጆቹ የምትሰጣቸውን የሚቀበሉ ያላቸውን ሁሉ የሚሰጡ ድንቅ ልጆች ነበሩኝ በዚህም በእንቅስቃሴ በጣም ደስተኛ ነበርኩ።”