“ከመጀመርያው ጀምሮ ደጋፊዎቻችን በእኛ ዕምነት ጥለውብን ነበር” ጋቶች ፓኖም

ቅዱስ ጊዮርጊስ የ2014 ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ዋንጫን ካነሳ በኋላ የቡድኑ ቁልፍ ተጫዋች ጋቶች ፓኖም ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር ቆይታ አድርጓል።

ትውልዱን በጋንቤላ ያደረገው ጋቶች ፓኖም
በኢትዮጵያ ቡና የእግር ኳስ ህይወቱን ጀምሮ ለዓመታት ቆይታ ካደረገ በኋላ በመቀጠል ወደ ሩሲያው ክለብ አንዚ ማካቻካላ አምርቶ ብዙም ቆይታን ሳያደርግ ወደ ሀገር ውስጥ ተመልሷል። ከዚያም በመቐለ 70 እንደርታ ስድስት ወራትን ከቆየ በኋላ በግብፆቹ ኤል ጎውና እና ሀራስ ኤል ሁዳድ እንዲሁም ወደ ሳውዲ አረቢያ ዲቪዥን ሁለት (ሦስተኛ የሊግ እርከን) ክለብ አል-አንዋር እና ባሳለፍነው ዓመት አጋማሽ በወላይታ ድቻ ተጫውቶ አሳልፏል። በሀገር ውስጥ እና ከኢትዮጵያ ውጪ በመጫወት የምናውቀው ግዙፉ አማካይ ጋቶች ፓኖም በዘንድሮ ዓመት ፈረሰኞቹን በመቀላቀል የመጀመርያውን ዋንጫ ማንሳት ችሏል። ሶከር ኢትዮጵያም ስለ ዘንድሮ ዓመት ፣ በቅዱስ ጊዮርጊስ ስለ ነበረው ጊዜ እና ሌሎች ጉዳዮች ከተጨዋቹ ጋር ቆይታ አድርጋለች።

ስለ ውድድር ዓመቱ

“ከቅድመ ዝግጅት ጀምሮ ዛሬ ሻምፒዮን እንስከሆንበት ቀን ድረስ እንደ ቡድን ስንሰራ ነው የመጣነው። ጥሩ የውድድር ዓመት አሳልፈናል። መጀመርያው ስንነሳ ከስብስባችን አንፃር ፣ ከደጋፊዎች እንዲሁም የክለባችን አመራሮች ከሰጡን ትኩረት አኳያ ዋና ዕቅዳችን የነበረው አስበንም የተነሳነው ከምንም በላይ ዋንጫ ማንሳት እንዳለብን ነበር። ይሄንንም በማሳካታችን በጣም ደስተኛ ነኝ።

የነጥብ መጥበቡ መንስኤ

“ ከሀዋሳ እስከ አዳማ በነበረን ጨዋታዎች የነበረን የሜዳ ላይ ብቃት ፣ ጥንካሬ እንዲሁም በሰፊ ነጥብ ልዩነት እንመራን ነበር። ወደ ባህር ዳር ከመጣን ወዲህ ትንሽ ተዳክመን ነበር። ያው ይሄ የመጣው ከድካም ፣ ከተጫዋቾች ተደጋጋሚ ጉዳትም ነው ብዬ አስባለሁ። ምክንያቱም ብዙ ጨዋታዎች ባለመሸነፍ መጥተናል። አንዳንዴ ተጫዋች ስትሆን ጥሩ ሆነህ በራሱ ጊዜው ተፅኖ አድርጎብህ ልትደክም ትችላለህ ፤ በዚህም ነጥባችን ተቀራርቦ ነበር። ሆኖም የመጨራሻ ጨዋታዎችን ትኩረት በማድረግ ባለ ድል መሆን ችለናል።

የቡድኑ ስኬት ሚስጥር ምንድነው ?

“ለድሉ ትልቁ ሚስጥራችን የቡድን መንፈሳችን እና አንድነታችን እጅግ በጣም ጥሩ መሆኑ ነው። ለአንድ ቡድን ስኬታማ ለመሆን ደግሞ የቡድን መንፈሱ ወሳኝ ነው። ለእኔ ትልቁን ቦታ የምሰጠው አንድ ቡድን አንድ ቤተሰብ መሆናችን ነው ፤ እሱ ውጤታማ አድርጎናል።

በቡድኑ ውስጥ ስለፈጠረው ተፅዕኖ

“በእርግጥ ዘንድሮ ነው ፈረሰኞቹን የተቀላቀልኩት ሆኖም እዚህ ከመምጣቴ በፊት ብዙ ልምድ አግኝቻለው። በውጪም በሀገር ውስጥም ፣ በብሔራዊ ቡድንም ተጫውቼ አልፌአለሁ። ስለዚህ አዲስ የሚሆነው መምጣቴ ነው እንጂ ሜዳ ላይ የምታደርገው ነገር አዲስ አይሆንብህም። ጊዮርጊስ ስመጣ በብሔራዊ ቡድን አብረውኝ የሚጫወቱት ልጆች መሆናቸው እና አብዛኛውን ጊዜ እንገናኝ ስለነበረ እዚህ ከመጣው በኋላ ለመግባባት አልተቸገርኩኝም። እያንዳንዱ ተጫዋች ለቡድኑ የሚያስፈልገውን ያውቃል ያንን አስተዋፆኦ ሲሰጥ ቆይቷል። እኔም በግሌ የምችለውን ሁሉ ለማድረግ ጥረት ሳደርግ ቆይቻለው።

ስለ አስገራሚው ወቅታዊ ብቃቱ

“ እንደ ተጫዋች ከዚህ በፊት ከብሔራዊ ቡድን ወጥቼ ነበር። ከዛም ተመልሼ ወደ ብሔራዊ ቡድን መጣው። ሆኖም በአፍሪካ ዋንጫ የመሰለፍ ዕድል አላገኘሁም። አንዳአንዴ የምታሳልፈው መጥፎ ጊዜ አለ። ግን መጥፎውን ጊዜ ከማስታወስ ይልቅ ራስህን የሚያወርድህን ነገር መስራት የለብህም። ጠንክረህ በመስራት አለብህ። ምክንያቱም ጠንክረህ ከሰራህ የማይደረስበት ቦታ የለም። ጠንክሬ ስለሰራሁ ነው የተሻለ ነገር የሰራሁት ፤ ለዚህም ደረጃ የደረስኩት። ምክንያቱም ዕድልም ባታገኝ ዕድሉን ባገኘህ ጊዜ መጠቀም እንድትችል ከመጀመርያው ጀምሮ ጠንክሮ መስራት ያስፈልጋል።

በቡና እና በጊዮርጊስ ስለመጫወቱ

“ ኢትዮጵያ ቡና ቤት ውስጥ ነው ያደኩት ፣ በቡና በነበረኝ ቆይታ የውጭ ዕድል አግኝቼ ወጣሁ። ስመለስ ለድቻ እና ለቅዱስ ጊዮርጊስ መጫወት ችያለው። እዚህም በመጣሁበት ዓመት ጥሩ ጊዜ እያሳለፍኩኝ ነው። ያው በሁለቱም ቡድኖች አሪፍ ጊዜ አሳልፌያለው። ቡና ሆኜ ያላሳካሁትን የሊጉን ዋንጫ እዚህ መጥቼ አሳክቻለው። በዚህም በጣም ደስተኛ ነኝ።

ስለ ኮከብ ዕጩነቱ

“ምርጫው በዓመት ውስጥ ባሳየህው ብቃት ነው። የህዝቡ ዕይታ ነው። እኔ ምንም ልናገር አልችልም። እኔ የሚጠበቅብኝ ጠንክሮ መስራት ፣ ለቡድኔ ከእኔ የሚፈልገውን አገልግሎት መስጠት ነው። ሌላው ደግሞ ከዛ በኋላ የሚመጣ ነው።

ስለደጋፊዎች

“የቅዱስ ጊዮርጊስ ደጋፊዎች እንደሚታየው ከሀገር ወደ ሀገር ተዟዙረው እኛን ሲደግፉ ሲያበረታቱ ቆይተዋል። እንደ ድሮ አዲስ አበባን መቀመጫ አድርጎ ውድድሩ ቢካሄድ ከዚህ በላይ የደጋፊው ድባብ ልዩ ይሆን ነበር። አዳማ በነበረን ውድድር ላይ በከፍተኛ ሁኔታ ወደ ዋንጫ ለምናደርገው ጉዞ አግዘውናል። ከመጀመርያው ጀምሮ ደጋፊዎቻችን በእኛ ዕምነት ጥለውብን ነበር። ሀዋሳ ላይ እንኳን ነጥብ እየጣልን እኛ ነን የምንበላው እያሉ ያበረታቱን ነበር። እነርሱ እኛ ላይ ዕምነት በጣሉ ቁጥር እኛ እየበረታን እናደርገዋለን ወደ ሚል ጥረት ውስጥ ገብተን መጨረሻ ላይ ደስታችን አብረን ማጣጣም ችለናል።

ዋንጫውን ለማን ታበረክታለህ ?

“ዋንጫውን ለባለቤቴ እንዲሆን እፈልጋለው። ምክንያቱም በጥሩም በመጥሮ ጊዜ ሁሌም ከጎኔ በመሆን ስታበረታታኝ ስለቆየች ለእርሷ ይሁንልኝ። እንዲሁም ለትንሿ ለሁለት ዓመት ልጄ ዋንጫውን አበረክታለሁ።”