የሴቶች ፕሪምየር ሊግ | ንግድ ባንክ ያለ መሸነፍ ጉዞውን ሲያስቀጥል ተከታዩ ኤሌክትሪክ ነጥብ ጥሏል

የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ የ18ኛ ሳምንት የሁለተኛ ቀን ጨዋታዎች ዛሬም ቀጥለው መሪው ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አስደንጋጭ ሁነት በነበረበት ጨዋታ አቃቂ ቃሊቲን 7-0 ሲረታ ድሬዳዋም ድል ቀንቶታል ኢትዮ ኤሌክትሪክ በአንፃሩ ከባህር ዳር ከተማ ጋር 2-2 ተለያይቷል፡፡

አቃቂ ቃሊቲ 0-7 ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ

3፡00 ሰዓት ሲል አንድም ጨዋታ ሽንፈት ያልገጠመው እና ፕሪምየር ሊጉን እየመራ የሚገኘው ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በጎል ተንበሽብሾ አቃቂ ቃሊቲን ረምርሟል፡፡ ለአስር ደቂቃዎች ያህል ብዙም ሳቢ ያልነበረው የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ ከደቂቃ ደቂቃ የንግድ ባንክ የበላይነት መታየት ጀምሯል፡፡ በዚህም 12ኛ ደቂቃ ላይ አጥቂዋ ሎዛ አበራ ከታሪኳ ዴቢሶ የተሻገረላትን ኳስ ወደ ጎልነት በመለወጥ ቡድኗን መሪ አድርጋለች፡፡ አጋማሹ ሊገባደድ በጭማሪ ደቂቃ ላይ የአቃቂዋ ግብ ጠባቂ በመዲና ዐወል ላይ በሳጥን ውስጥ የሰራቸውን ጥፋት ተከትሎ የተሰጠውን የፍፁም ቅጣት ምት ሎዛ አበራ ከመረብ በማሳረፏ ውጤቱ ወደ 2-0 ከፍ ብሏል።

ከዕረፍት ጨዋታው ልክ እንደተመለስ መዲና ዐወል ለንግድ ባንክ ተጨማሪ ጎል አክላለች፡፡ 57ኛው ደቂቃ ላይ እመቤት አዲሱ 60ኛው ደቂቃ ላይ ሎዛ አበራ በዓመቱ ሦስተኛ ሀትሪኳን የሰራችበትን ጎል በማስቆጠር ጨዋታው 5-0 ሆኗል፡፡ 67ኛ ደቂቃ ላይ ጨዋታው ሲደርስ ግን በርካቶችን ያሳዘነ ድርጊት ተከስቷል፡፡ ዮርዳኖስ ምዑዝ ተቀይራ በገባች በአንድ ደቂቃ ውስጥ ስድስተኛ ጎል ለኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ስታስቆጥር ኳሱን ለመያዝ ጥረት በማድረግ ላይ የነበረችው የአቃቂዋ ግብ ጠባቂ ሳሳሁልሽ ስዩም የምላስ መታጠፍ አደጋ አጋጥሟት በርካቶችን ያሳዘነ ድርጊት ሜዳ ላይ ተመልክተናል፡፡ ግብ ጠባቂዋ የገጠማት ጉዳት ቀላል ቢመስልም ተዝለፍልፋ በመውደቋ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የህክምና ባለሙያ ሥንታየው ተሾመን ጨምሮ ሌሎች የህክምና አካላት ፣ ዳኞች ፣ ተጫዋቾች እና በስታዲየሙ የተገኙ የስፖርት ወዳድ ተመልካቾች ባደረጉት ጥረት ተጫዋቿን ነብስ ለማዳን ጥረዋል፡፡

በሰዓቱ በስታዲየሙ አምቡላንስ አለመኖሩን ተከትሎ ተጫዋቿ በቶሎ ወደ ህክምና ተቋም መሄድ ባትችልም የኋላ ኋላ አምቡላንስ ደርሶ ወደ ሲስተር አቅሌሲያ መታሰቢያ ሆስፒታል አምርታለች፡፡ ከሀያ ደቂቃዎች መቋረጥ በኋላ ጨዋታው ከቆመበት ሲቀጥል ፀጋነሽ ወራና ተጨማሪ ጎል ለንግድ ባንክ ከመረብ አዋህዳ ጨዋታው 7-0 ተጠናቋል፡፡

ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላ ሶከር ኢትዮጵያ ተጫዋቿ ወደ ምትገኝበት ሆስፒታል በማምራት እንደተመለከተችው ግብ ጠባቂዋ ጥቂት ብትዘገይ ኖሮ በህይወት የመኖሯ ዕድል የጠበበ ቢሆንም በህክምና ርብርብ ወደ መልካም ጤንነቷ ተመልሳለች፡፡

ኢትዮ ኤሌክትሪክ 2-2 ባህርዳር ከተማ

ንግድ ባንክን እግር በእግር ሲከተል የነበረው ኢትዮ ኤሌክትሪክ ነጥብ የጣለበትን ውጤት አስመዝግቧል። 8፡00 ሰዓት ሲል ባህርዳር ከተማን የገጠመው የአሰልጣኝ መሠረት ማኔው ኢትዮ ኤሌክትሪክ አወዛጋቢ ከሆነ የዳኝነት ውሳኔዎች ጋር ጨዋታውን 2-2 አጠናቋል፡፡ በመጀመሪያው አጋማሽ የመጀመሪያዎቹን ሀያ ደቂቃዎች ተመጣጣኝ የሚመስልን ፉክክር በሁለቱም ቡድኖች በኩል ማየት ብንችልም በሂደት በአጥቂዎቻቸው ዕገዛ ፈጣን የማጥቃት ሽግግርን ለመጠቀም ሲታትሩ የነበሩት ኤሌክትሪኮች ቀዳሚ የሆኑበትን ጎል አግኝተዋል፡፡

27ኛው ደቂቃ ላይ በአንድ ሁለት ቅብብል ወደ ሳጥን ውስጥ የሄደን ኳስ ዓይናለም አሳምነው ወደ ጎልነት ቀይራዋለች፡፡ ከሦስት ደቂቃዎች በኋላ ትንቢት ሳሙኤል ሁለተኛ ጎል ከመረብ በማሳረፍ ክለቧን 2-0 አድርጋለች፡፡ ጎል ካስተናገዱ በኋላ ጫናን ለማሳደር ረጃጅም ኳስ ላይ ያዘነበሉት የጊዮን ንግስቶቹ በምስር ኢብራሂም አስደናቂ ጎል 2-1 ተሸጋግረዋል፡፡

ከዕረፍት መልስ 66ኛው ደቂቃ ላይ ምስር ኢብራሂም ባህርዳርን አቻ ያደረገች ግብ ከመረብ አሳርፋለች፡፡ በቀሩት ደቂቃዎች ኃይላቸውን በመጠቀም ወደ አሸናፊነት ለመመለስ የበረቱት ኤሌክትሪኮች 79ነኛ ደቂቃ ላይ ሽታዬ ሲሳይ ከቅጣት ምት አክርራ ወደ ጎል ስትመታው ትንቢት ሳሙኤል ነፃ አቋቋም ላይ ሆና የተመለሰውን ኳስ ብታስቆጥረውም የዕለቱ ዋና ዳኛ ፀሀይነሽ አበበ እና ረዳቷ ልደት ዋልተንጉስ በወሰኑት ውሳኔ በመሀል ዳኛዋ ጎሉ አለመፅደቁን ተከትሎ የኤሌክትሪክ የቡድን አባላት በዳኛዋ ላይ ከፍተኛ ተቃውሞን ያሰሙ ሲሆን ጨዋታውም ለአምስት ያህል ደቂቃዎች ሊዘገይ ችሏል፡፡ በዳኛዋ ላይ ኤሌክትሪኮች ክስ ካስያዙ በኋላ ጨዋታው ቢቀጥልም ተጨማሪ ጎል ሳንመለከት 2-2 ፍፃሜን አግኝቷል፡፡

ድሬዳዋ ከተማ 1-0 አርባምንጭ ከተማ

የሳምንቱ የማሳረጊያ ጨዋታ የነበረው የድሬዳዋ ከተማ እና አርባምንጭ ከተማ ጨዋታ ጠንካራ ፉክክርን አስመልክቶን በመጨረሻም በምስራቁ ክለብ አሸናፊነት ተደምድሟል፡፡ የአርባምንጭ ከተማ የበላይነት በታየበት እና በአንፃሩ በፈጣን የመልሶ ማጥቃት የአርባምንጭን የመከላከል ስህተት ለመጠቀም የሚጥሩት ድሬዎች 50ኛው ደቂቃ ላይ ቤዛዊት ንጉሴ ያስቆጠረቻት ብቸኛ ጎል ድሬዳዋን 1-0 አሸናፊ አድርጋለች፡፡