የአዲስ አባባ እግርኳስ ክለብ አመራሮች በኢትዮጵያ ሆቴል ረጅም ሰዓት የፈጀ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል

👉 “አዲስ አበባ ከተማ ፍትሀዊ ውሳኔ ካልተሰጠው ምን አልባት በኢትዮጵያ እግርኳስ የሚኖረው ተሳትፎ ያበቃል” አቶ ዳዊት ትርፉ – የክለቡ ቦርድ ፀሀፊ 

👉 “ከጊዮርጊስ ጋር የምናደርገው ጨዋታ ብናሸንፍ ጥቅማጥቅማችን በአምስት እጥፍ እንደሚያድግ ፣ የጋራ መኖሪያ ቤት እንደሚሰጠን እና ከአምስት ድርጅት አምስት ዓይነት ሽልማት እንደሚሰጠን ተነግሮናል።” አሰልጣኝ ጳውሎስ ጌታቸው

ከሰሞኑ በእግርኳሱ ማህበረሰብ ዙሪያ መነጋገርያ ርዕስ የሆነው የ2014 ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የመዝጊያ ዕለት የተፈጠረው ክስተት ነው። የዚህ ክስተት ተጎጂ ሆኛለው የሚለው የአዲስ አበባ እግርኳስ ክለብ የቦርድ ፀሀፊ እና የአዲስ አበባ ስፖርት ኮሚሽን ም/ኮሚሽነር አቶ ዳዊት ትርፉ ፣ የክለቡ ሥራ አስኪያጅ አቶ ነፃነት ፣ የክለቡ ዋና አሰልጣኝ ጳውሎስ ጌታቸው እና ቡድን መሪው አቶ መሠረት በተገኙበት በዛሬው ዕለት በኢትዮጵያ ሆቴል ሰፊ ማብራርያ ሰጥተዋል። ሶከር ኢትዮጵያም በዋናነት የተነሱትን ነጥቦች እና ከሚዲያ አካላት የቀረቡትን ጥያቄዎች እና መልሶችን አካታ ተከታዩን መረጃ ወደ እናንተ ታደርሳለች።

የመግቢያ ንግግር በማድረግ ጋዜጣዊ መግለጫውን ያስጀመሩት አቶ ዳዊት ትርፉ ” የተፈጠረውን ሁኔታ ከመከሰቱ አስቀድሞ ብዙ ጉዳዮች እንዳለቁ እና ሊፈጠሩ የሚችሉ ነገሮችን በጠረንጴዛ ዙርያ እንዳለቁ ይሰሙ የነበረበት ሁኔታ ጨዋታው ከተጠናቀቀ በኋላ በተግባር አይተነዋል። ድሬዳዋ ከተማ እና ፋሲል ከነማ ያደረጉት ጨዋታ ከእግርኳስ መርህ ያፈነገጠ ፣ ብዙዎችን ያሳዘነ ፣ የወደፊቱን የኢትዮጵያ እግርኳስን ላይ ጥቁር ጠባሳ ጥሎ ያለፈ ድርጊት ነው። ይህ ድርጊት ህገወጥ በሆነ መንገድ የጨዋታ ውጤትን ማስለወጥ (ሙስና) ተብሎ በተቀመጠው አንቀፅ መሠረት በእኛ እምነት ጨዋታው ሙሉ ለሙሉ በመጨረሻው ደቂቃ ከአቅም በታች የተደረገ ነው ፤ ለዚህም በርካታ ማሳያዎች አሉ። አንደኛ የድሬዳዋ ከተማ እና የፋሲል ከነማ ወቅታዊ አቋማቸው ሁለተኛ ያሉበት ደረጃ ይታወቃል። ግን እንዳያችሁት ፣ እንደሰማችሁት ተመልካቹ ሳይቀር ልቀቁ ልቀቁላቸው ይል ነበር። ይህ የቪዲዮ ማስረጃ ያለው ጉዳይ ነው። ሌላው የፋሲሉ ግብ ጠባቂ በምን መንገድ ለተቃራኒው እንደለቀቀ የሚታይ ነው። በአጠቃላይ ሦስቱም ጎሎች በምን መንገድ እንደገቡ የሚታይ ነው። ምን አልባት ጨዋታው በምስል ባይታይ ኖሮ እንደ ከዚህ ቀደሙ ማስረጃ የለንም ብለን ልንከራከር እንችላለን። አሁን ግን መላው የኢትዮጵያ እግርኳስ ቤተሰብ ተመልክቶታል።

“ብዙ የስፖርት ቤተሰብ ከመቼውም ጊዜ በላይ በጉጉት ይጠብቀው የነበረን ጨዋታ የተለየ ነገር ለመፍጠር እና ስማችንን ከፍ ለማድረግ አዲስ አበባ ከተማ ብሎ ፋሲል እንዲያስታውሰው ለማድረግ ፣ የቅዱስ ጊዮርጊስ ደጋፊም ነጥብ አስጣሉን በማለት እንዲያስቡን ለማድረግ እና በአጠቃላይ የእግርኳሱ ቤተሰቡ ወደ ፕሮፌሽናል አስተሳሰብ እግርኳሳችን እየተንደረደረ መሆኑን ለማሳየት በጨዋታው ዕለት ከፍ ያለ ስሜት ነበረን። ለተጫዋቾቻችን የገባንላቸው ቃል ራሱ ይህንን ጨዋታ በራሳቸው ዕድል መወሰን ከቻሉ ዳጎስ ያሉ ሽልማት እንደሚሰጣቸው እዛው ቃል ተገብቶ ነበር። ይሄን ከየትኛውም ተጫዋች ማረጋገጥ ትችላላቹሁ። የራሳችንን ዕድል በራሳችን ለመወሰን ጥንቃቄ ማዕከል ያደረገ አስተላለፍን ይዘን ወደ ሜዳ ገብተናል። በ54ኛው ደቂቃ እስከተሰጠብን ፍፁም ቅጣት ምት ደረስ ጨዋታውን በራሳችን ለመወሰን ታግለናል። ዞሮ ዞሮ የተጫወትነው ሻምፒዮን ለመሆን ዘጠና ደቂቃ ከቀረው ቡድን ጋር ነው። ፍፃሜው በዛ መንገድ ሆኗል። እኛ ኢ ፍታህዊ በሆነ መንገድ መውረድ የለብንም። በሊጉ ውስጥ መቆየት ይገባናል የሚል አቋም ነው ያለን። በቀጣይ በሊጉ ቆይቶ መጫወት እንጂ ወርዶ መጫወት የሚል ፍላጎቱም ተነሳሽነቱም የለንም።

“ አንዳንዶች ከጊዮርጊስ ጋር የአንድ ከተማ ቡድኖች ስለሆኑ ተሞዳምደዋል የሚሉ ነበር። ጊዮርጊስ አራት ማስገባት አያስፈልገውም ነበር። ሦስት ነጥብ እንጂ የሚፈልገው ብዙ ጎል አየደለም አሸናፊ የሚያደርገው ስለዚህ ከጊዮርጊስ ጋር ስለ መለቃቅ ብንነጋገር ተጠባብቀን መጨረሻ ላይ ሌላው ያደረገውን ማድረግ እንችል ነበር። በፍፁም ይሄን አላደረግንም፣ ወደ ፊትም አናደርግም። ምን ለመጨመር፣ ምን ለማምጣት ፣ ምን ለማገዝ ? ድሬዳዋ ፋሲል የእኛ አይደሉ። ሁሉም ክለቦች የኢትዮጵያ ናቸው። ድምር ውጤቱ የሀገራችንን ሊግ ማሳደግ ነው። ለምን የማይሆን አሻጥር ውስጥ እንገባለን። ለዚህ ሁሉ ምክንያቱ ከሚሰሩ አሻጥሮች በኋላ እዚህ ግባ የማይባል ነው። የሆነ ሰሞን አጀንዳ ይሆናሉ። ተረስተው የከርሞ ሰው ይበለን ተብለው ይቀጥላል።

“አዲስ አበባ ከተማ ፍትሀዊ ውሳኔ ካልተሰጠው ምን አልባት በኢትዮጵያ እግርኳስ የሚኖረው ተሳትፎ ያበቃል ፤ ፍትህ እንፈልጋለን። በመንግሥት እየተደገፉ ያሉ በአስራ አንዱም ክፍለ ከተማ ያሉ ክለቦች ዕጣ ፈንታም በቀጣይ እንደ ከተማ አስተዳደር ራሱን ችሎ የሚታይ ጉዳይ ይሆናል። ስለዚህ ነበረው ሂደት የሊጉ ድምቀት የህዝቡን ትኩረት የሳበ ቢሆንም በመጨረሻው ሰዓት የተደረገው ድርጊት አዲስ አበባ ከተማን በከፍተኛ ሁኔታ ማዘኑን ህዝቡ እንዲረዳን እንፈልጋለን። በቀጣይ አጭር ቀናት ውስጥ ውሳኔ እንዲሰጠን እንፈልጋለን። እስከምንችለው ድረስ እስከ ገላጋይ ፍርድ ቤት ድረስ ሄደን ለኢትዮጵያ እግርኳስ ፍትህ እንታገላለን። ከዚህ ውጪ የሚኖረን ተሳትፎ በሂደት የምናሳውቅ ይሆናል። አሁን ደግመን ደጋግመን የምንናገረው የኢትዮጵያ እግርኳስ ፍትህ ትፈልጋለች።”

በማስከተል አሰልጣኝ ጳውሎስ ጌታቸው ሜዳ ላይ ስለነበረው ታክቲካል ጉዳይ ዙርያ ማብራሪያ ሰጥተዋል።

“ብዙ ነገር መናገር አልፈልግም ትንሽ ነገር ነው የምናገው። ይህ የቡድን አባላት እስከ በላይ ድረስ ያሉ አመራሮች ተማክረው ሰርተዋል። እነርሱንም በዚሁ አመሰግናለው። ሰባት ልጅ አልገባም ይባላል ፤ ሰባት ልጅ አለማስገባት የእኛ መብት ነው። ልምምድ ላይ ልጆቹን የምናሰራው እኛው ነን። ተቀያሪ ተጫዋቾች ገቡ ብሎ ማንም ሰው እንዳይጠራ። በዚህ ጨዋታ ያልገቡት ሮቤል ግርማ ፣ አዩብ በቀታ እና ሙሉቀን አዲሱ ናቸው። ፍፁም ጥላሁን አምስት ቢጫ ያለብት በመሆኑ አልገባም። ሰባት ስምንት ልጅ ቀድሞ የምንጠቀምባቸው ቋሚ ተጫዋቾች ናቸው። ሮቤል ያላስገባንበት ምክንያት በሰበታ እና በሲዳማ ጨዋታ ብዙ ጎሎች የተቆጠሩብን (በሁለት ጨዋታ አምስት ጎል የተቆጠረብን) ከግራ መስመር ስለሆነ ሮቤል ብዙ ሲያገለግለን የከረመ ልጅ ነው። ሮቤል ቋሚ ተጫዋችም አልነበረም። እኔ ከመጣሁ በኋላ ነው መጠቀም የጀመርነው። ሮቤል ረጅም ዓመት የተጫወተ ልጅ ነው። ጉልበት መሰብሰብ ይፈልጋል። በአምስት ቀናት ውስጥ ይሄን ልጅ ገለነዋል። በእርሱ የተካነው ሳሙኤል አስፈሪ ቡድኑን ከታች ጀምሮ ይዞ የመጣ ልጅ ነው። አዩብ በቀታ ህመም ላይ እያለ ነው በግድ ለሲዳማ ጨዋታ ያስገባነው። በእርሱ ምትክ የተሻለውን ዘሪሁን አሼቦን ነው ያስገባነው። በሙሉቀን ቦታ የገባው ብዙዓየሁ ነው። ይሄም የሆነው ጋቶችን ማጥፋት የምንችለው በአጭር ተጫዋች ከእርሱ ሳይርቅ ነው ብለን እስገብተናል። እስከ ሀያ ደቂቃ ድረስ ይሄንን አድርገነው ጋቶችን መቆጣጠር ችለን ነበር። እኔ ራሴን የምቆጥረው አዲስ አበባ ከተማን አላወረድኩትም። በጣም ያሳፍራል አራት ኪሎ ኮንዲሚንየም ተገዛለት ተብሎ ተወርቷል። እኔ በአርባ ሁለት ብር የቀበሌ ቤት ነው የምኖረው። ብዙ ነገር ለመሸፈን የተወራ ወሬ ነው። በኢትዮጵያ እግርኳስ ብዙ ነገር አልፈናል ሁሉንም ነገር እናውቃለን። አዲስ አበባ ፋውል ልስራ ቢል ኖሮ የጊዮርጊስን ጨዋታ አይጠብቅም ነበር። ምንም ዕድል ከሌለው ኢትዮጵያ ቡና ጋር በአመራር ደረጃ ቢሰራ የአዲስ አበባ ክለብ ስለሆነ ማስለቀቅ ቢፈለግ ይችል ነበር። ሌላው ከሲዳማ ቡና ጋር መሞዳሞድ ቢፈልግ ለሲዳማ ቡና ምንም የሚያስፈልገው ጨዋታ አልነበረም። ግን አመራሮቻችን የማደንቀው ለክብር እና ለህልውና ተነጋግረን መጥተው እያዩን ወደ ሜዳ ገብተናል። ከጊዮርጊስ ጋር የምናደርገው ጨዋታ ብናሸንፍ ጥቅማጥቅማችን በአምስት እጥፍ እንደሚያድግ ፣ የጋራ መኖሪያ ቤት እንደሚሰጠን እና ከአምስት ድርጅት አምስት ዓይነት ሽልማት እንደሚሰጠን ተነግሮናል። እኛ ብዙ ነገር ነው ያጣነው። ስለዚህ ሌላውን ነገር ለመሸፈን ቋሚ ተሰላፊ ሳይሰለፉ ተብሎ የሚነሳው አሉባልታ መሰረተ ቢስ ነው። ያለፈውን አመት ውጤት አስታውሱት ወልቂጤ ወርዶ ማን ለቆ ለማን ተለቆለት እንደነበር ለእናተ እተወዋለው። ግን ስትወርድ በአግባቡ መውረድ አለብህ ፣ እኔ ስመጣ ዘጠኝ ጨዋታ ይቀር ነበር። ወረደ የተባለውን ቡደኑን ውጤታማ በማድረግ ለሰባት አሰልጣኞች እንቅልፍ እንዲያጡ በማድረጌ በራሴ ኮርቻለው።

ከዚህ በማስከተል በዕለቱ በተገኙ የሚዲያ አካላት በርከት ያሉ ጥያቄዎች የተነሱ ቢሆንም ከወቅታዊ ጉዳይ ጋር ተያይዞ አቶ ዳዊት የሰጡትን ምላሾችን ወደ እናንተ እናቀርባለን።

ላቀረባቹሁት ቅሬታ ከአወዳዳሪው አካል የተሰጣቹሁ ምላሽ አለ ?

“ጉዳዩን በልዩ ሁኔታ እናየዋለን። የሰጣቹሁንን ጥቆማ በእርግጠኝነት ተቀብለነዋል። እናንተም ግን እንደውም ሁለቱ የከተማ ክለቦች ስለሆኑ እስከ መጨረሻው ድረስ ተያይዘው መላቀቅ ያደርጋሉ የሚል ጥቆማ መጥቶልን ነበር ፤ ብለዋል። የእኛን ትመለከቱታላቹሁ ፣ እንዳውም አዲስ አበባን አጀግነን በሁሉም ልብ ውስጥ የማያቁትን አዲስ አበባ ሁሉም እንዲያውቅ አድርገን። በማለት እንዲያውም እስካሁን ማለፋችንን አላረጋገጥንም ብለን አቋም ይዘን ነበር።”

ከአቅም በታች መጫወት በብዙ መንገድ ለማረጋገጥ ጊዜ ይወስዳል እናንተ በምን አረጋገጣችሁ ?

“አዎ በጨዋታ መላቀቅ ለማረጋገጥ ብዙ ጊዜ ይወስዳል። በገንዘብ ልውውጥ ፣ በተለያዩ መረጃ ቅብብሎሽ የድምፅ ልውውጥ ሌሎችም ጉዳዮችን ለማወቅ ጊዜ ይወስዳል። አሁን እኛ ያየነው ከአቅም በታች መጫወት እጅግ የወረደው ለመወሰን ቀላል የሆነውን ነው። ብዙ በገንዘብ ቅብብል ያለውን ሳይሆን እዛው ሲታይ ውርድ ያለውን ነው ከአቅም በታች መጫወት ያየነው። ማንም ተራ ሰው የሚመለከተውን ይሄን ያህል ፕሮፌሽናል ምርመራ የማያስፈልገው ነው ያየነው። ስለዚህ ድሬዳዋ እና ፋሲል 30ኛ ጨዋታቸውን እያደረጉ ነው። ወቅታዊ አቋማቸው ይታወቃል። ጨዋታው እስከ 70ኛ ደቂቃ የነበረው ውጤት፣ የአጨዋወት አካሄድ የግብ ጠባቂው አቋም ይታወቃል። የደጋፊውም አቋም ይታወቃል። ይህ ሁሉ በእነዛ አስራ አምስት ደቂቃ ውስጥ ምንደነው የተለወጠው። አንዳንዴ ተፈጥሯዊ በሆነ መንገድ ነው ችግር ሲያጋጥም ወቅታዊ አቋም ይወርዳል። ለምሳሌ የአየር ሁኔታው ከአቅም በላይ ሲሆን ፣ ምን አልባት ከባድ ዝናብ ዘንቦ የተጫዋቾች አቋም ሊወርድ ይችላል። ይህ በሌለበት ሁኔታ ከ75 ደቂቃ በኋላ ይህ መፈጠሩ ለባለቤቱ እንተዋለን።”

ለተፈጠረው ነገር ማንን ነው በባለቤትነት ተጠያቂ የምታደርጉት ?

“ኃላፊነት መውሰድ ያለበት አወዳዳሪው አካል ነው። ማንም ሌላ አለ ብዬ አላስብም። አወዳዳሪው አካል ጥሩ ሲሰራ ተመስግኗል። የሀገሪቱን እግርኳስ በዚህ ደረጃ እንዲያድግ የሰሩት ሥራ የሚደነቅ ነው። ለተፈጠሩ ችግሮች ደግሞ ዘምባባውን ብቻ ሳይሆን አርጩሜውንም ማየት እንፈልጋለን። ይህ ለአዲስ አበባ ብቻ አይደለም። ብዙ ሰው ከሰሞኑ መረዳት ከቻላቹ የጨዋታ ቅሌት መደረግን ቤተሰባዊ አድርጎታል። ‘ከዚህ በፊት የዕከሌ ተደርጎ የለ ? ይህ ምን ይገርማል’ እያለ ነው። ታዲያ መች ነው ከዚህ የምንወጣው ። ቀጣይ ደግሞ ከዚህ በሚቀጥለው ዓመት እየደመርን ነው የምንሄደው። በአዲስ አበባ ዘንድሮ ተደረገ ቀጣይ ደግሞ ማነው ተረኛ ? መባል አለበት። የቱ ጋር እናቁመው ሰው የጨዋታ ማጭበርበር መደረጉን አምኖ እኛም ላይ ተደርጎ ነበር እያለ ነው። ስለዚህ ወዴት እየሄድን ነው ? መቼ ነው ከዚህ አዙሪት የምንወጣው ? እዚህ ላይ በቃ ልንል ይገባል። እግርኳሳችን በዚህ መንገድ መቀጠል የለበትም። አይጠቅምም።”

ምን ዓይነት ውሳኔ ትጠብቃላቹሁ ?

“በህጉ በደንቡ የተቀመጠ ውሳኔ ይወሰናል ብለን እንጠብቃለን። አንቀፅ 68 ላይ ቁልጭ ብሎ ተቀምጧል። እዚህ አንቀፅ ላይ የተቀመጡት ይተገበራሉ ብለን እንጠብቃለን።”

ውሳኔው አሉታዊ ቢሆን ክለቡን እስከ ማፍረስ ለመወሰን ስለማሰባቸው

“በአሁን ሰዓት ለማስፈራራት ሳይሆን አዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የሚደግፈው ክለቡን ብቻ አይደለም በክፍለ ከተማ ደረጃ ያሉ የሴትም የወንዶችም ቡድኖችን ጨምሮ ነው። እውነት ለመናገር አንጋፋ ቡድኖቻችንንም ስንደግፍ ነበር። የከተማ አስተዳደሩ ከየትኛውም ክልል በተሻለ እግርኳሱ ላይ ድጋፍ እያደረገ ነው። ይህን ለእግርኳሱ ድጋፍ እያደረገ ነው። እንደዚህ ለሚለፋ አመራር እና ካቢኔን ለእግርኳሱ ጠር እንደሆነ አድርጎ ማሰብ ትክክል አይደለም። ይሄንን ድጋፍ ወደ ኋላ ይጎትተዋል የሚል አቋም ነው የያዝነው።”