ወልቂጤ ከተማ እግድ ተላልፎበታል

ወልቂጤ ከተማ ከቀጣዩ የተጫዋቾች የዝውውር መስኮት ጀምሮ እንዳይሳተፍ እግድ ተላልፎበታል።

በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ እየተሳተፈ የሚገኘው ወልቂጤ ከተማ በተጫዋች አዳነ በላይነህ “ለ2 ዓመት የሚቆይ ውል እያለኝ ክለቡ በሚያደርገው ቅድመ ዝግጅት ላይ ባለመጠራቴ ክለቡን ብጠይቅም መልስ ያልሰጠኝ በመሆኑ ፌዴሬሽኑ ውሳኔ እንዲሰጠኝ” በማለት አቤቱታ ቀርቦበት እንደነበር ይታወቃል። የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የዲሲፕሊን ኮሚቴም የቀረበውን ክስ በመመርመር ወደ ክለቡ እንዲመለስ እና ያልተከፈለው ደሞዙ እንዲከፈለው ውሳኔ ቢያስተላልፍም ክለቡ ውሳኔው ፍትሀዊ አይደለም በማለት ይግባኝ ጠይቆ ነበር።

የይግባኝ ሰሚ ኮሚቴ ጉዳዩን መርምሮ የዲሲኘሊን ኮሚቴን ውሳኔ ያፀና መሆኑን በቀን 09/06/2014 ቢያሳውቅም ወልቂጤዎች ውሳኔውን ተግባራዊ ባለማድረጋቸው ተጫዋቾቹ በድጋሜ አቤቱታ አቅርቧል። ይህንን ተከትሎ በተሰጠው ቀነ ገደብ መሰረት ውሳኔው ተግባራዊ ባለመሆኑ ከቀጣዩ የተጫዋቾች የዝውውር መስኮት ጀምሮ እንደታገዱ መወሰኑን የተጫዋቹ የህግ ጠበቃ እና ወኪል አቶ ብርሃኑ በጋሻው ለዝግጅት ክፍላችን ገልፀዋል።