የሴቶች ፕሪምየር ሊግ | በተጠባቂው ጨዋታ ንግድ ባንክ ድል አድርጓል

የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ የ19ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ዛሬም በሦስት መርሐ-ግብሮች ሲቀጥሉ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በወሳኙ ጨዋታ ድል ሲቀናው አርባምንጭ ከተማም አሸንፏል፡፡ ኢትዮ ኤሌክትሪክ በበኩሉ በደረጃ ሰንጠረዡ ከፍ የሚልበትን ነጥብ ጥሏል፡፡

ኢትዮ ኤሌክትሪክ 0-0 ድሬዳዋ ከተማ

ረፋድ 3 ሰዓት በአሰልጣኝ መሠረት ማኔ የሚመራው ኢትዮ ኤሌክትሪክ እና በአሰልጣኝ እዮብ ተዋበ የሚመራው ድሬዳዋ ከተማ ያደረጉት ጨዋታ የዕለቱ ቀዳሚ ፍልሚያ ነበር፡፡ ድሬዳዋ ከተማ ደረጃውን ለማሻሻል ኢትዮ ኤሌክትሪክ በአንፃሩ ወደ መሪው ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ለመጠጋት የሚረዳውን ነጥብ ለማግኘት ብርቱ ትግል ያደረጉት ጨዋታ ነበር፡፡ በሁለቱም አጋማሾች ኢትዮ ኤሌክትሪክ በተሻለ የንቃት ስሜት በተጫወተበት በዚህ ጨዋታ ሦስቱን አጥቂዎች ትንቢት ሳሙኤል፣ አይናለም አሳምነው እና ሰላማዊት ጎሳዬን ማዕከል ባደረገ የአንድ ሁለት ቅብብል ጥቃት ለመሰንዘር ሲሞክር ድሬዎች በበኩላቸው ከርቀት በሚደረጉ ሙከራዎች ጎልን ለማግኘት አልመው መንቀሳቀስ ቢችሉም ግብ ሳንመለከት 0ለ0 በሆነ ውጤት ተጠናቋል፡፡

አርባምንጭ ከተማ 3-0 አቃቂ ቃሊቲ

ከቀትር በኋላ 8፡00 ሰዓት ሲል በአርባምንጭ ከተማ እና አቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ መካከል የተደረገው ጨዋታ በአርባምንጮች የበላይነት የተጠናቀቀ ሆኗል፡፡ በመጀመሪያው የጨዋታ አጋማሽ ተመጣጣኝ የሜዳ ላይ ፉክክርን በሁለቱም ቡድኖች መካከል ማየት ብንችልም በመስመር አጨዋወት በሂደት መጠቀም የጀመሩት እና ተሻጋሪ ኳሶች ላይ ትኩረት ያደረጉት አርባምንጭ ከተማዎች ቀስ በቀስ ወደ ጨዋታ ቅኝት በመግባት ጎል ወደ ማስቆጠሩ መጥተዋል፡፡ 34ኛው ደቂቃ ላይም ድንቅነሽ በቀለ ባስቆጠረቻት ጎል መሪ መሆን ችለዋል፡፡

ከዕረፍት ጨዋታው ሲቀጥል በተሻለ ንቃት ዳግም የተመለሱት አርባምንጭ ከተማዎች 67ኛው ደቂቃ ላይ ዳግም ተጨማሪ ጎል አክለዋል፡፡ ከአቃቂ የግብ ክልል በግምት 35 ሜትር ርቀት ላይ የተሰጠውን የቅጣት ምት ወርቅነሽ ሜልሜላ አክርራ በመምታት ሁለተኛ ጎል አድርጋለች፡፡ ከሁለት ደቂቃ በኋላ ድንቅነሽ በቀለ ለራሷ ሁለተኛ ለአርባምንጭ ሶስተኛ ግብን በማስቆጠር ጨዋታው 3ለ0 በዕንስት አዞዎቹ የበላይነት ተደምድሟል፡፡

ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ 1-0 መከላከያ

የሳምንቱ ማሳረጊያ እንዲሁም ተጠባቂ የሆነው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እና መከላከያ ጨዋታ 10፡00 ሰዓት ላይ በበርካታ ተመልካቶች ታጅቦ ተካሂዷል፡፡ ጠንካራ ፉክክር በርትቶ ማየት በቻልንበት እና ተደጋጋሚ የማጥቃት መንገድን በሁለቱም ክለቦች በኩል ማስተዋል የቻልንበት ይህ ጨዋታ በመጨረሻም ንግድ ባንክን አሸናፊ አድርጎ ፍፃሜውን አግኝቷል፡፡ በመጀመሪያው የጨዋታ አጋማሽ ወጥ የሆነ እና መሀል ሜዳ ላይ አማካዮች ተከማችተው ኳስን በመቀባበል ለመጫወት ሲሞክሩ የተመለከትን ሲሆን የመከላከያ ወጥ ያልሆነው የመከላከል ድክመት ግን ለንግድ ባንክ አጥቂዎች ምቹ ነበር፡፡

በዚህም ሂደት ከመስመር በኩል ከዕፀገነት ብዙነህ መነሻውን ያደረገ ኳስ ወደ መከላከያ የግብ ክልል ሲሻማ ሎዛ አበራ ላይ ጥፋት በመሰራቱ የተሰጠውን የፍፁም ቅጣት ምት ራሷ ሎዛ አበራ በአመቱ ሀያ ዘጠነኛ ግቧ አድርጋ ከመረብ አዋህዳ ቡድኗን መሪ አድርጋለች፡፡

ጨዋታው ከዕረፍት ሲመለስ መከላከያ በርከት ያሉ የአጥቂ ስፍራ ተጫዋቾችን ቀይሮ በማስገባት ወደ ጨዋታ ለመመለስ እጅጉን ታትሯል። በተለይ አማካዩዋ ማዕድን ሳህሉ ከገባች በኋላ ላቅ ያለ ብልጫ ሲያሳዩ የታዩበት ንግድ ባንኮችም ተጨማሪ ጎል በመጨመር የግብ መጠናቸውን ከፍ ለማድረግ ቢጥሩም ጨዋታው 1ለ0 በሆነ ውጤት ተቋጭቷል፡፡