አቡበከር ናስር የጎፈሬ ብራንድ አምባሳደር ሆኖ ስምምነት ፈፀመ

👉”ወደ ፊት በእግርኳስ ኢንዱስትሪ እና በበጎ አድራጎት መስራት ላሰብኩት እቅድ ትልቅ መነሳሻ ይሆነኛል” አቡበከር ናስር

👉”ጎፈሬ እና አቡበከር በጋራ በኮ ብራንዲንግ አዳዲስ ምርቶችን እንዲመረቱ ያደርጋሉ” አቶ ሳሙኤል መኮንን

በኢትዮጵያ ቡና እና በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ራሱን በሚገባ ያሳየው አቡበከር ናስር የደቡብ አፍሪካውን ክለብ ማሜሎ ዲ ሰንዳውንስ ለቅድመ ውድድር ዝግጅት ከመቀላቀሉ በፊት ዛሬ ከሀገር በቀሉ የትጥቅ አምራች ተቋም ጎፈሬ ጋር ስምምነት ፈፅሟል። ከሰዓታት በፊት በምስል ባጋራናችሁ መረጃ ላይ እንደጠቀስነውም አቡበከር ናስር የጎፈሬ ብራንድ አምባሳደር ሆኗል።

ቦሌ አካባቢ በሚገኘው የጎፈሬ ቢሮ በተከናወነው የስምምነት እና የጋዜጣዊ መግለጫ መርሐ-ግብር ላይ ለተገኙ የብዙሃን መገናኛ አባላት ገለፃዎች ተደርገዋል። በቅድሚያም አቡበከር ናስር እና የጎፈሬ ሥራ-አስኪያጅ አቶ ሳሙኤል መኮንን የመግባቢያ ሰነዱን ተፈራርመዋል። በመቀጠል ስምምነቱን አስመልክቶ ማብራሪያ መሰጠት ተጀምሯል።

መድረኩን ቀድመው የተረከቡት አቶ ሳሙኤል ስምምነቱ ለሦስት ዓመት እንደሆነ በመግለፅ ቀጣዩን ሀሳብ አጋርተዋል። “ስምምነቱ በቡራንድ አምባሳደርነት ነው። በብራንድ አምባሳደርነቱ ስር ደግሞ ኮ ብራንዲንግ አለ። በዚህም ጎፈሬ እና አቡበከር በጋራ በኮ ብራንዲንግ አዳዲስ ምርቶችን እንዲመረቱ ያደርጋሉ። ከምርቶቹ ደግሞ አቡኪ እንዲጠቀም ይደረጋል። በተጨማሪም የተለያዩ የበጎ አድራጎት ሥራዎችን ማስኬድ እና በታዳጊዎች ላይ የጋራ ሥራዎችን ማከናወን ነው።” ካሉ በኋላ የስምምነቱ ዓላማ ተጨዋቾች ባላቸው አጭር የእግር ኳስ ህይወት በመልካም የገነቡትን ስም ወደ ቢዝነስ ብራንድ የመቀየር አስተሳሰብን በሀገራችን ለማስጀመር እና ለሌሎች ታዳጊ ተጫዋቾች አርአያ እንዲሆን ለማድረግ መሆንን ገልፀዋል።

አቡበከር ናስር በበኩሉ ብዙ ታዳጊዎች እንደ ሮል ሞዴል እየተመለከቱኝ ስለሆነ ለእነርሱ የተሻለ ነገር ለማሳየት መጣር አለብኝ ካለ በኋላ ጎፈሬ ራሴን በዚህ መልኩ እንዳስብ አድርጎኛልና አመሰግነዋለሁ ብሏል። ተጫዋቹ ጨምሮም ወደ ፊት በእግርኳስ ኢንዱስትሪ ውስጥ እና በበጎ አድራጎት መስራት ላሰብኩት እቅድ ትልቅ መነሳሻ ይሆነኛል በማለት ንግግሩን አሰምቷል።
ይህንን ትልቅ ስምምነት ዛሬ የተፈራረመው ጎፈሬ ከሰሞኑን ሌሎች ስምምነቶችን ይፋ እንደሚያደርግ ይጠበቃል።