የሴቶች ፕሪምየር ሊግ | የንግድ ባንክ የድል ጉዞ ቀጥሏል

በኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ የ20ኛ ሳምንት መርሐ-ግብሮች በሁለት ሜዳዎች ተደርገው ኢትዮ ኤሌክሪክ በግብ ተንበሽብሾ ሲያሸንፍ ቅዱስ ጊዮርጊስም ሦስት ነጥብ ያሳካ ሲሆን ንግድ ባንክ አሁንም በማሸነፉ ገፍቶበታል።

3፡00 ላይ በሁለት ሜዳዎች በተደረጉ ጨዋታዎች ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጌዲኦ ዲላን 4-0 ሲረታ ድሬዳዋ ከተማ ከባህር ዳር ከተማ ጋር ያለ ጎል ተለያይተዋል

አዳማ አበበ ቢቂላ ስታዲየም ላይ ሊጉን እየመራ የሚገኘው የአሰልጣኝ ብርሀኑ ግዛው ንግድ ባንክ ዛሬም ከማሸነፍ አልቦዘነም፡፡ ጌዲኦ ዲላን የገጠመው ቡድኑ ገና ጨዋታው በተጀመረ በደቂቃዎች ልዩነት ሁለት ጎሎችን አስቆጥሯል፡፡ 4ኛው ደቂቃ ላይ ሰናይት ቦጋለ ከሳጥኑ ጠርዝ በድንቅ ሁኔታ ግብ አስቆጥራ ቡድኗን መሪ እንዲሆን አስችላለች፡፡ ከአራት ደቂቃዎች ቆይታ በኋላ ልማደኛዋ አጥቂ ሎዛ አበራ የግብ መጠኑን ያሳደገች ግብ በማስቆጠር ልዩነቱን 2-0 አድርጋለች፡፡

ጌዲኦ ዲላዎች ወደ ጨዋታ ለመመለስ በተደጋጋሚ ተሻጋሪ ኳሶችን ለመጠቀም ሲጥሩ ቢታይም የባንክን የመከላከል አደረጃጀት ሰብሮ ለመግባት ተቸግረዋል፡፡ ከዕረፍት መልስ ሎዛ አበራ በተደጋጋሚ በፈጠረችው የሙከራ ሂደት ተሳክቶላት ለራሷ ሁለተኛ ለቡድኑ ደግሞ ሦስተኛ ጎል አክላለች፡፡ 66ኛው ደቂቃ ላይ ከመስመር የተሻገረን አጋጣሚ ተቀይራ በመግባት ፀጋነሽ ወራና ወደ ጎልነት በመለወጥ ጨዋታው 4-0 በንግድ ባንክ አሸናፊነት ተጠናቋል፡፡

በተመሳሳይ ሰዓት በአዳማ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ሜዳ ላይ የተገናኙት ድሬዳዋ ከተማ እና ባህርዳር ከተማን ያገናኘው ጨዋታ ጎል ሳይቆጠርበት 0-0 ተፈፅሟል፡፡

በ8፡00 ጨዋታ ኤሌክትሪክ ከግማሽ ደርዘን በላይ ጎል በማስቆጠር አቃቂ ቃሊቲን ሲረመርም ቅዱስ ጊዮርጊስም ወሳኝ ነጥብ አሳክቷል

በአሰልጣኝ መሠረት ማኔ የሚመራው ኢትዮ ኤሌክትሪክ አቃቂ ቃሊቲ ላይ የጎል ናዳ አዝንቦ 7-0 አሸንፏል፡፡ ከዕረፍት በፊት በአማካዩዋ ንቦኝ የን እና በአጥቂዋ ትንቢት ሳሙኤል አማካኝነት 2-0 ወደ መልበሻ ክፍለ ያመሩ ሲሆን ከዕረፍት በኋላ ትንቢት ሳሙኤል በጨዋታው ሁለተኛዋን ጎል ለራሷ ስታስቆጥር ለቡድኗ ደግሞ ሶስተኛ ግብ አድርጋለች፡፡ 55ኛው ደቂቃ ላይ ሽታዬ ሲሳይ ከሁለት ዓመታት በኋላ ወደ እግር ኳስ ተመልሳ ግብ ያስቆጠረች ሲሆን ፀጋ ንጉሴ ፣ ሰላማዊት ጎሳዬ እና ትዝታ ፈጠነ ተጨማሪ ጎሎች በማስቆጠር ጨዋታው 7-0 ተጠናቋል፡፡

በአዳማ አበበ ቢቂላ ስታዲየም በተመሳሳይ ሰዓት በተደረገ ጨዋታ ፈረሰኞቹ ዕንስቶች ድል ቀንቷቸዋል፡፡ ለዕይታ ሳቢ የሆነ የሜዳ ላይ እንቅስቃሴን ባየንበት የሁለቱ የመዲናይቱ ቡድኖች ጨዋታ በመከላከል ድክመት የነበረባቸው ቦሌዎች በተቆጠረባቸው ግብ ተሽንፈዋል፡፡ ከዕረፍት በፊት ከሰሞኑ ለቅዱስ ጊዮርጊስ ግብ አምራች እየሆነች የምትገኘው እየሩስ ወንድሙ ሁለት ጎሎች ከመረብ ስታሳርፍ በሁለተኛው አጋማሽ አምበሏ ሶፋኒት ተፈራ ከርቀት በማስቆጠር ሦስተኛ ግብ ስታደርግ የመጨረሻዎቹን ሀያ ደቂቃዎች ብልጫ ለመውሰድ ጥረት ያደረጉት ቦሌዎች ከሽንፈት ያልዳኑበትን አንድ ግብ በጭማሪ ደቂቃ ላይ በአጥቂዋ ንግስት በቀለ አማካኝነት ቢያስቆጥሩም ጨዋታው 3-1 በቅዱስ ጊዮርጊስ የበላይነት ተጠናቋል፡፡

የዕለቱ የመጨረሻ ጨዋታዎች ነጥብ በመጋራት ተጠናቀዋል

በአዳማ አበበ ቢቂላ ስታዲየም አዳማ ከተማ ከአዲስ አበባ ከተማ ጋር ነጥብ ተጋርቶ ወጥቷል፡፡ መሀል ሜዳ ላይ ያመዘነ እንቅስቃሴ ረጅሙን ደቂቃ በርክቶ በታየበት የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ 33ኛው ደቂቃ ላይ ከመስመር በኩል ናርዶስ ጌትነት ያሻማቸውን ኳስ ፂዮን ፈየራ የግብ ጠባቂዋን ስርጉት ተስፋዬን ስህተት ተጠቅማ አዳማን ወደ መሪነት ማሸጋገር ብትችልም ከሁለት ደቂቃዎች በኋላ የመስመር አጥቂዋ ያብስራ ይታይህ ለአዲስ አበባ ጎል አስቆጥራ ጨዋታው በዚሁ ውጤት 1-1 ተደምድሟል፡፡

በሌላኛው ሜዳ መከላከያ ወደ ላይ ከፍ ሊል የሚችልበትን ዕድል አምክኗል፡፡ በዚህም በአርባምንጭ ከተማ ብርቱ ፈተና አስተናግዶ ጨዋታውን 1-1 አጠናቋል፡፡ መሳይ ተመስገን ለመከላከያ መሠረት ወርቅነህ ለአርባምንጭ ከተማ ጎሎችን ያስቆጠሩ ተጫዋቾች ሆነዋል፡፡