ያሬድ ባዬ ወደ ጣና ሞገዶቹ ያመራ የመጀመርያ ተጫዋች ሆኗል

በአሰልጣኝ አብርሀም መብራቱ የሚመራው ባህር ዳር ከተማ ያሬድ ባዬን ወደ ቡድኑ መቀላቀሉን አሳውቋል።

በዘንድሮ የውድድር ዓመት ሳይጠበቅ ላለመውረድ ሲጫወት የቆየው ባህር ዳር ከተማ በቀጣይ ዓመት ጠንካራ ቡድን ለመስራት ወደ ዝውውሩ መግባት ጀምሯል። የመጀመርያ ፈራሚውም የኋላ ደጀኑ ያሬድ ባዬን መሆኑን አሳውቋል።

በአውሥኮድ የእግርኳስ ህይወቱን የጀመረው ያሬድ በመቀጠል በዳሽን ቢራ ከተጫወተ በኋላ ከ2009 ጀምሮ በፋሲል ከነማ ቤት መንገስ የቻለ ተጫዋች ሲሆን በ2013 የውድድር ዘመን አምበል በመሆን የሊጉን ዋንጫ ማንሳቱ ይታወሳል።

 

ከኋላ ክፍሉ ላይ ከፍተኛ ችግር ይታይበት የነበረው ባህር ዳር ያሬድ ወደ ቡድኑ መቀላቀል ትልቅ ክፍተት ይደፍናል ተብሎ ይጠበቃል።