መከላከያ ከአሠልጣኙ ጋር አይቀጥልም

በቀጣይ ዓመት መቻል የሚለው የቀደመ ስያሜውን ይዞ ብቅ የሚለው መከላከያ ከአሠልጣኝ ዮሐንስ ሳህሌ ጋር እንደማይቀጥል ተረጋግጧል።

በዘንድሮ ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ዳግም መሳተፍ የጀመረው መከላከያ ወደ ዋናው የሀገሪቱ የሊግ እርከን ካሳደጉት አሠልጣኝ ዮሐንስ ሳህሌ ጋር መለያያቱን ይፋ ሆኗል። ቡድኑን 2013 ላይ የተረከቡት አሠልጣኝ ዮሐንስ በኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ምድብ ሀ 38 ነጥቦችን በመያዝ ማጠናቀቃቸው ይታወሳል።

ዘንድሮ ደግሞ በፕሪምየር ሊጉ በ37 ነጥቦች 9ኛ ደረጃን ይዘው አጠናቀው ነበር። አሠልጣኙ በክለቡ ያላቸው ውል ሰኔ 30 መጠናቀቁን ተከትሎም ከክለቡ ጋር እንደማይቀጥሉ ሶከር ኢትዮጵያ ከህጋዊ ጠበቃቸው ብርሃኑ በጋሻው ያገኘችው መረጃ ያመላክታል።