ሙጂብ ቃሲም በይፋ ለሀዋሳ ከተማ ፈረመ

ከሀዋሳ ከተማ ጋር ስለ መስማማቱ በትላንትናው ዕለት ዘግበን የነበረው የሁለገቡ ተጫዋች ሙጂብ ቃሲም ዝውውር ተጠናቋል፡፡

በትላንትናው ዕለት ወደ ዝውውር ገበያው በመግባት ተከላካዩ በረከት ሳሙኤል እና የመስመር አጥቂው እዮብ አለማየሁን የግላቸው ያደረጉት ሀዋሳ ከተማዎች ሁለገቡን ተጫዋች ሙጂብ ቃሲምን በሁለት ዓመት ውል ማስፈረማቸውን ሶከር ኢትዮጵያ አረጋግጣለች፡፡

በሲዳማ ቡና የአማካይ ስፍራ ተጫዋች በመሆን የእግር ኳስ ህይወቱን የጀመረው ሙጂብ ቃሲም በመቀጠል ወደ ሀዋሳ ከተማ በኋላም ወደ ሦስተኛ ክለቡ አዳማ ከተማ ተጉዞ ለክለቦቹ በተከላካይነት እና አሁን እየተጫወተ በሚገኝበት የአጥቂ ስፍራ ላይ በመሰለፍ ተጫውቶ አሳልፏል፡፡

በፋሲል ከነማ ጥሩ ቆይታን ያደረገው ሙጂብ ዓምና ወደ አልጄሪያ ሊግ በማምራት የወራት ቆይታን አድርጎ መመለሱም አይዘነጋም። ግማሹን የውድድር ዓመት በፋሲል ያሳለፈው ግዙፉ አጥቂ አመሻሽ ላይ ወደ ሀይቆቹ ያደረገውን ዝውውር በይፋ አገባዶ አብሮት ከተጫወተው አሠልጣኝ ዘርዓይ ሙሉ ጋር ለመስራት ፊርማውን አኑሯል።