አፄዎቹ የአማካዮቻቸውን ውል አራዝመዋል

ፋሲል ከነማ ከነባር ተጫዋቾቹ ጋር ያለውን ውል በማራዘም ሲቀጥል ሁለት ቁልፍ ተጫዋቾች ከክለቡ ጋር እንደሚቀጥሉ እርግጥ ሆኗል።

ዋና አሰልጣኙን ከሰሞኑ ይፋ እንደሚያደርግ የሚጠበቀው ፋሲል ከነማ ከሽመክት ጉግሳ በመቀጠል የሁለት ወሳኝ ተጫዋቾቹን ውል ለተጨማሪ ሁለት ዓመታት ማራዘሙን ሶከር ኢትዮጵያ አረጋግጣለች፡፡

ከእነዚህ መሀል ሱራፌል ዳኛቸው አንዱ ነው፡፡ ከአዳማ ከተማ ወጣት ቡድን እስከ ዋናው ግልጋሎት የሰጠው እና ከ2011 ጀምሮ በፋሲል ከነማ እየተጫወተ የሚገኘው አማካዩ ውሉ መጠናቀቁን ተከትሎ ተጨማሪ ዓመታትን በክለቡ ዳግም ለመቆየት ከሰዓታት በፊት ውሉን አድሷል፡፡

በዛብህ መለዮ ሌላው በቡድኑ ውስጥ መቆየቱ ዕርግጥ የሆነው ተጫዋች ነው፡፡ የቀድሞው የሀዲያ ሆሳዕና እና ወላይታ ድቻ የአማካይ ስፍራ ተጫዋች ያለፉት አራት ዓመታት በአፄዎቹ መለያ ያሳለፈ ሲሆን አሁንም በክለቡ ተጨማሪ ጊዜን ለማሳለፍ ፊርማውን አኑሯል፡፡