ዋልያዎቹ ለቻን ማጣሪያ የሚያደርጉትን ልምምድ ቀጥለዋል

ታንዛኒያ ላይ የቻን የአፍሪካ ዋንጫ የማጣሪያ ጨዋታ ከደቡብ ሱዳን ጋር የሚጠብቀው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በአዳማ ከተማ ልምምድ ማድረግ ከጀመረ ሁለተኛ ቀኑ ላይ ይገኛል፡፡

በአልጄሪያ አዘጋጅነት ለሚደረገው የቻን የአፍሪካ ዋንጫ ላይ ተሳታፊ ለመሆን የቅድመ ማጣሪያ ጨዋታውን ከደቡብ ሱዳን ጋር የደርሶ መልስ መርሃግብሩን በታንዛኒያ የሚያከናውነው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ዝግጅቱን እየከወነ ነው።

የብሔራዊ ቡድኑ አሰልጣኝ ውበቱ አባተ ከሳምንታት በፊት ለሀያ ሁለት ተጫዋቾች ጥሪ ማድረጋቸው የሚታወስ ሲሆን ሙሉ የቡድኑ አባላትም በስብስቡ ተካተው ዝግጅታቸውን ማድረግ ጀምረዋል፡፡ አዲስ አበባ ላይ እየጣለ ባለው ዝናብ የተነሳ ወደ አዳማ ያመራው ብሔራዊ ቡድኑ በኤክስኪውቲቭ ሆቴል ማረፊያውን በማድረግ ነው እየሰራ የሚገኘው።

ዛሬ ረፋድ 5፡00 ሰዓት ሲል በአዳማ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ስታዲየም ቡድኑ በልምምድ ላይ እያለ ሶከር ኢትዮጵያ በስፍራው ተገኝታ የተከታተለች ሲሆን አሰልጣኝ ውበቱ አባተ በይበልጥ የቅንጅት ስራዎች ላይ ትኩረት በማድረግ የተጫዋቾች የቦታ አያያዝ እንዲሁም ታክኒክ እና ቴክኒክ ላይ ትኩረት ያደረጉ ልምምዶችን ለተጫዋቾቻቸው ሲሰጡ የተመለከትን ሲሆን በልምምዱ ማገባደጃ ላይም የሜዳውን አጋማሽ በመጠቀም የእርስ በእርስ ጨዋታዎችን አድርገዋል።

በዛሬው ልምምድ ላይ እንዳስተዋልነው ከኢትዮጵያ ቡና የተመረጠው አማካዩ አማኑኤል ዮሐንስ ቁርጭምጪሚቱ አካባቢ በገጠመው ጉዳት መሳተፍ ያልቻለ ሲሆን ሌሎች ቀሪ ተጫዋቾች በሙሉ በዛሬው መርሃግብር ተሳታፊዎች ነበሩ፡፡ በቀጣዮቹ ቀናትም ብሔራዊ ቡድኑ በአዳማ ልምምዱን ከሰራ በኋላ ወደ ታንዛኒያ የሚያመራ ይሆናል፡፡