በከፍተኛ ሊጉ የደመቀው ተከላካይ ቡናማዎቹን ተቀላቅሏል

በከፍተኛ ሊግ ምድብ ሐ ተወዳዳሪ በነበረው ጉለሌ ክፍለከተማ ሲጫወት የነበረው የመሀል ተከላካይ ኢትዮጵያ ቡናን ተቀላቅሏል፡፡

በቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ብርቱ ተፎካካሪ ለመሆን አዳዲስ ተጫዋቾችን እያስፈረመ የሚገኘው ኢትዮጵያ ቡና አሰልጣኝ ተመስገን ዳና የወልቂጤ ከተማ አሰልጣኝ በነበሩበት ወቅት በጥብቅ ሲከታተሉት የነበሩትን የመሀል ተከላካይ ራምኬል ጀምስን የግላቸው አድርገዋል፡፡

በትውልድ ስፍራው ጋምቤላ ከተማ እግር ኳስን በክለብ ደረጃ በመጫወት የጀመረው እና ያለፉትን ዓመታት ጉለሌ ክፍለከተማን በከፍተኛ ሊጉ በአምበልነት እና በመሀል ተከላካይነት ያገለገለው ተጫዋቹ በሦስት ዓመታት ውል ቡናማዎቹን ተቀላቅሏል፡፡

በዛሬው ዕለት ክለቡ የግብ ጠባቂው እስራኤል መስፍንን ውል ለተጨማሪ ሦስት ዓመታት ማደሱን ይፋ አድርጎ እንደነበር ይታወቃል፡፡