ባህር ዳር ከተማ ሁለት ተጫዋቾችን አስፈርሟል

የጣና ሞገዶቹ የአዲስ ፈራሚዎቻቸውን ቁጥር ስድስት አድርሰዋል።

ከሰሞኑ አዳዲስ ተጫዋቾችን ወደ ስብስቡ እየቀላቀለ የሚገኘው ባህርዳር ከተማ በዛሬው ዕለት የመስመር ተከላካይ ቦታውን ያጠናከረባቸውን ሁለት አዳዲስ ተጫዋቾችን አስፈርሟል፡፡

ከአዲሶቹ ፈራሚዎች አንዱ የሆነው ተስፋዬ ታምራት ዛሬ ዝውውሩን አጠናቋል፡፡ ከሰሞኑ ቅድመ ስምምነት ፈፅሞ የነበረው የቀድሞው የኢኮስኮ ፣ ገላን ከተማ እና ኢትዮጵያ መድን የግራ መስመር ተከላካይ ተስፋዬ በሁለት ዓመት ውል ነው በይፋ የፈረመው፡፡

ሌላኛው የግራ መስመር ተከላካይ ፍራኦል መንግሥቱ ስድስተኛው የጣና ሞገደኞቹ ፈራሚ ሆኗል፡፡ የቀድሞው የሀድያ ሆሳዕና ፣ ኢትዮ ኤሌክትሪክ እና ሀላባ ከተማ ተጫዋች ከወራቶች በፊት ከሀላባ አዲስ አበባን በውሰት በመቀላቀል በአንድ ጨዋታ ላይ ብቻ በፕሪምየር ሊጉ ተሰልፎ መጫወት የቻለ ሲሆን በዛሬው ዕለት አዲሱ የባህር ዳር ፈራሚ መሆን ችሏል፡፡