ወላይታ ድቻ የወሳኝ ተጫዋቾቹን ውል አራዘመ

ከቀናት በፊት ወደ ዝውውር የገቡት የጦና ንቦቹ የአምበላቸውን እና የአማካይ ተጫዋቾቻቸውን ውል ማደሳቸውን አስታውቀዋል።

ደጉ ደበበ በቀጣይ ዓመትም የእግር ኳስ ህይወቱን ለመቀጠል ውሉን አድሷል። አንጋፋው ተከላካይ በ2011 አጋማሽ ክለቡን ከተቀላቀለ በኋላ በአምበልነት ጭምር ቡድኑን እያገለገለ የሚገኝ ሲሆን ለተጨማሪ አንድ ዓመት ውሉች አራዝሟል።

ንጋቱ ገብረሥላሴ ሌላው ውሉን ያራዘመ ተጫዋች ነው። በተጠናቀቀው የውድድር ዓመት ጅማ አባ ጅፋርን ለቆ የጦና ንቦቹን የተቀላቀለው ንጋቱ ወጥ አቋም ካሳዩ የቡድኑ ተጫዋቾች መካከል አንዱ የነበረ ሲሆን እንደ ደጉ ሁሉ ለአንድ ዓመት ለመቆየት ውሉን እንዳደሰ ክለቡ አስታውቋል።

ወላይታ ድቻ በዝውውር መስኮቱ ሳሙኤል ተስፋዬን ሲያስፈርም መሳይ ኒኮልን ውል ማደሱ የሚታወስ ነው።