አዲስ አበባ ከተማ ለሊግ አክስዮን ማህበሩ ደብዳቤ አስገባ

በወቅታዊ ጉዳይ ዙርያ አዲስ አበባ ከተማ ለሊጉ አክስዮን ማኅበር ደብዳቤ ማስገባቱ ታውቋል።

ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የ2014 የውድድር ዘመን የመጨረሻው ጨዋታ በቅዱስ ጊዮርጊስ 4-0 የተሸነፈው አዲስ አበባ ከተማ ወደ ከፍተኛ ሊግ መውረዱን ተከትሎ ፋሲል ከነማ ከድሬዳዋ ከተማ ጋር ያደረጉት ጨዋታ ከአቅም በታች የተካሄደ ነው በማለት ከሳምንት በፊት ቅሬታውን ለአወዳዳሪው አካል በደብዳቤ፣ በጋዜጣዊ መግለጫም የክለቡን አቋም ሲያንፀባርቁ ቆይተዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ እግርኳስ ክለብ በዛሬው ዕለት ለሊግ አክስዮን ማኅበር ተጨማሪ ደብዳቤ አስገብቷል። እንደ ክለቡ ገለፃ ከሆነ “ሰኔ 24/2014 በተመሳሳይ ሰዓት በተካሄዱ ሦስት ጨዋታዎች በተፈጠረው ከአቅም በታች መጫወት ተመርምሮ ፍትህ እንዲሰጠን በተለያዩ ቀናት በተፃፈ ደብዳቤ መጠየቃችን ይታወቃል። ስለሆነም ክለባችን በቀጣይ ስራዎችን ለመስራት ይረዳን ዘንድ ውሳኔውን እንድታሳውቁን እንጠይቃለን።” በማለት ውሳኔ እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል።

አወዳዳሪው አካልም በ30ኛ ሳምንት በተመሳሳይ ሰዓት በተካሄዱ ጨዋታዎች የተፈጠሩ ክስተቶችን ተከተሎ ለጨዋታ ታዛቢዎች፣ ዳኞችና የቡድን መሪዎች በአጠቃላይ ይመለከታቸዋል ያለውን አካላት በመጥራት ማናገሩ ይታወሳል።