ከ15 ዓመት በታች የፓይለት ፕሮጀክት ውድድር በአርባምንጭ ከተማ ተጀመረ

ለመጀመሪያ ጊዜ በኢትዮጵያ እግርኳስ ፌደሬሽን አዘጋጅነት በሁለቱም ፆታዎች ከ15 ዓመት በታች የፓይለት ፕሮጀክት የምዘና ወድድር በአርባምንጭ ከተማ በዛሬው ዕለት መካሄድ ጀመሯል።

በዳዊት አቦዬ

በ2014 የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌድሬሽን ከጀመራቸው አዳዲስ የእግርኳስ የሥልጠና መንገዶች መካከል አንዱ ከ15 ዓመት በታች የፓይለት ፕሮጀክቶችን በተለያዩ ክልሎች እና ከተማ አስተዳድሮች ማቋቋም እንደነበር ይታወሳል፡፡ ፌድሬሽኑ ከዓመቱ ጅማሮ አንስቶ ያቋቋማቸውን እነዚህን ፕሮጀክቶች ክትትል እና ድጋፍ ሲያደርግ የቆየ ሲሆን የሥልጠና መንገዱ ምን ላይ ይገኛል የሚለውን ለመገምገም ለመጀመሪያ ጊዜ ውድድር አዘጋጅቷል፡፡ በአርባምንጭ ከተማ አዘጋጅነት ውድድሩ ከሀምሌ 17 እስከ ነሀሴ 1 የሚቆይ ሲሆን በወንዶች አስራ ሰባት በሴቶች ዘጠኝ የፕሮጀክት ቡድኖች ይሳተፉበታል፡፡

ውድድሩ ዛሬ ሲጀመር በአንድ ጨዋታ የተጀመረ ሲሆን በመክፈታቸውም የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌድሬሽን የሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባል አቶ ዘሪሁን ቀቀቦ ውድድሩ በሁሉም ክልሎች ሲሰጥ የነበረውን ሥልጠና ውጤታማነት ለመመዘን በማሰብ እንደተዘጋጀ ገልፀው በተጨማሪነትም በዓለም አቀፍ መድረክ ኢትዮጵያን ከ15 ዓመት በታች የሚወክሉ የብሔራዊ ቡድን ተጫዋቾችን ለመምረጥ በማሰብም ጭምር የተዘጋጀ ነውም ሲሉ ተናግረዋል፡፡ በሥነ ስርአቱ ላይ የደቡብ ክልል እግር ኳስ ፌድሬሽን ፕሬዝዳንት አቶ ደመላሽ ይትባረክ ፣ የጋሞ ዞን ወጣቶች እና ስፖርት መምሪያ የስፖርት ዘርፍ ኃላፊ አቶ ታመነ ተስፋዬ እና ሌሎች የክብር እንግዶች በተገኙበት ውድድሩ በይፋ ተጀምሯል፡፡

ዛሬ ረፋድ ላይ የመክፈቻ ጨዋታ በምድብ ሀ በሚገኙት አርባምንጭ ከተማ ፓይለት ፕሮጀክት የባህርዳር ዩኒቨርሲቲ አቻውን ገጥሞ 4 ለምንም በመርታት የመጀመሪያ ድሉን አሳክቷል። በጨዋታው ላይ ጥሩ ሲንቀሳቀስ የነበረው የአርባምንጩ ናዝራዊ ማትዮስ ይጫኑ የጨዋታው ኮከብ በመባል የኳስ ሽልማት ተበርክቶለታል፡፡

የጨዋታው ኮከብ እና ከ16.50 ውጪ የቅጣት ምት ጎል ያስቆጠረው ታዳጊ ናዝራዊ ማትዮስ ከኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የሥራ-አስፈፃሚ አባል አቶ ዘሪሁን ቀቀቦ እጅ የኳስ ሽልማቱን ተቀብሏል።

የውድድሩ ሙሉ የምድብ ድልድል


በወንዶች

ምድብ ሀ – አርባምንጭ ከተማ ፣ ቤንሻንጉል ጉሙዝ ፣ ኦሮሚያ አጋሮ ፣ ባህርዳር ዩኒቨርሲቲ

ምድብ ለ – አፋር ክልል ፣ ሀላባ ናሺፍ ፣ አማራ ክልል ፣ ኦሮሚያ ጅማ ፣ አዲስ አበባ ከተማ

ምድብ ሐ – አርባምንጭ ዩኒቨርሲቲ ፣ ጋምቤላ ክልል ፣ ሐረሪ ክልል ፣ ሲዳማ ክልል

ምድብ መ – ድሬዳዋ ከተማ ፣ ሶዶ ኮንፊደንስ ፣ ኦሮሚያ ሻሸመኔ ፣ ሶማሌ ክልል

በሴቶች


ምድብ ሀ – ድሬዳዋ ከተማ ፣ ኦሮምያ አዳማ ፣ አርባምንጭ ሻራ ፣ ሲዳማ ክልል ፣ ሐረሪ ክልል

ምድብ ለ ፣ ጋምቤላ ክልል ፣ አዲስ አበባ ከተማ ፣ አርባምንጭ ዩኒቨርሲቲ ፣ አማራ ወልድያ