ጎፈሬ ከአዲስ አበባ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ጋር ስምምነት ፈፀመ

ሀገር በቀሉ የትጥቅ አምራች ተቋም ጎፈሬ ከመዲናው የእግር ኳስ ፌዴሬሽን ጋር ለቀጣዮቹ ሦስት ዓመታት አብሮ ለመስራት ተፈራረመ።

በሀገር ውስጥ ያለውን የስፖርት ትጥቅ አቅርቦት ክፍተት ለመድፈን እየጣረ የሚገኘው ጎፈሬ ከክለቦች ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት በመፍጠር ሥራዎችን ከመስራቱ በተጨማሪ ከተለያዩ የክልል እግር ኳስ ፌዴሬሽኖች ጋር ስምምነት በመፍጠር ለስፖርቱ እድገት የተለያዩ ክንውኖችን እያደረገ የሚገኝ ሲሆን በዛሬው ዕለትም ከአዲስ አበባ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ጋር አብሮ ለመስራት የፊርማ ስምምነት ፈፅሟል።

በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ወጣቶች እና ስፖርት ቢሮ አዳራሽ በተከናወነው የስምምነት መርሐ-ግብር ላይ የአዲስ አበባ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት አቶ ደረጄ አረጋ እና የጎፈሬ ባለቤት አቶ ሳሙኤል መኮንን ተገኝተዋል።

ለሦስት ዓመታት እንደሚዘልቅ በተገለፀው ስምምነት ሀገር በቀሉ የትጥቅ አምራች ተቋም ጎፈሬ የእግር ኳስ ፌዴሬሽኑ ከሲቲ ካፕ ጀምሮ በስሩ የሚያከናውናቸው የውስጥ ውድድሮች በጋራ እንደሚያከናውን እና ትጥቅ እንደሚያቀርብ ተገልጿል። ውድድሮቹ የከተማውን ገፅታ በሚመጥን መልኩ እንዲከናወኑም የጋራ ጥረት እንደሚደረግ ተመላክቷል። በተለይ አቶ ሳሙኤል በየዓመቱ የሚጠበቀውን የከተማው ዋንጫ ጥራት እና ደረጃ ለማሳደግ እንዲሁም በምስራቅ አፍሪካ ተወዳጅ ለማድረግ እንደሚሰራ ሲናገሩ ተደምጧል።

የፌዴሬሽኑ ፕሬዝዳንት አቶ ደረጄ በበኩላቸው ከጎፈሬ ጋር መስራታቸው በስራቸው የሚያደርጓቸውን 8 የተለያዩ ውድድሮች እንደሚያደምቅ ገልፀዋል። በዋናነት ደግሞ የሲቲ ካፕ ውድድሩ በደማቅ ሁኔታ እንዲከናወን ከስፖንሰር አፈላለግ ጀምሮ የተለያዩ ስራዎች በጋራ እንደሚከወኑ አመላክተዋል።

ከሲቲ ካፑ ጋር ተያይዞ ቀጣዩ ውድድር ከኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን እና የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ አክሲዮን ማኅበር ጋር በመነጋገር ቀኑ እንደሚወሰን ሲገለፅ በጊዜያዊነት ግን ከነሐሴ ወር መጨረሻ ጀምሮ የሀገር ውስጥ እና ተጋባዥ የውጪ ክለብ በመጨመር እንደሚደረግ ተጠቁሟል።